POWr Social Media Icons

Saturday, November 1, 2014


ሐዋሳን እንዳየኋት
በአገራችን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ ካሉ ከተሞች ውስጥ አንዷ ሐዋሳ ናት፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን ከተማ ከሆኑትም አንዷ ናት፡፡ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ጎብኝዎች በስፋት የሚስተናገዱባት በሆነችነችው ሐዋሳ ከተማን በጎበኘሁ ጊዜ  የሚከተሉትን ችግሮች መመልከት ችያለሁ፡ 
ይኸውም እንዲሰጣቸው የሚፈልጉትን የገንዘብ መጠን ወስነው ካልሰጣችሁኝ የሚሉ ለማኞች እንዲሁም የቆሙ መኪናዎች ዕቃ ሥርቆት እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጊት በጊዜ ቁጥጥር ሥር ካልዋለ፣ ለከተማዋ ዕድገትና መሻሻል እንዲሁም የተሻለ ገቢ ለማግኘት መሰናክል ስለሚሆን የተከማው አስተዳደር እነዚህን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ ፈጣን መፍትሔ  መስጠት ወይም ዕርምጃ መውሰድ ይገባዋል እላለሁ፡፡
(አማን ኑሪ፣ ከአዲስ አበባ)

ቤቶች ኤጀንሲ ለሹማምንት ቤት የሚሰጠው ከማን ወስዶ ነው?

‹‹የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ለተሿሚዎች ቤት እንዲያቀርብ ታዘዘ፤ የሚያቀርበው ቤት ባለመኖሩ ደንበኞች ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡›› በማለት የሪፖርተር የእሑድ መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትም፣  የውስጥ ዜና አስነብቧል፡፡
ይህንን ዜና ተንተርሼ ከፍትሕ አካላት ራሱን ነጥሎ ኢፍትሐዊ የሆነ ዕርምጃን በመውሰድ የሚታወቅን ተቋም ይባስ ብሎ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በራሱ አስፈጻሚዎች ነዋሪውን ከቤቱ እንዲያስወጣ ሥልጣን ስለተሰጠው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የማውቃቸውን እውነታዎችና እንደዚህ ዓይነቶቹ ኢፍትሐዊ አካሄዶች በዜጎችና በመንግሥት ላይ የሚያሳድሩት ጥሩ ያልሆኑ ተፅዕኖዎችን ለማሳየት ግድ ብሎኛል፡፡
የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ከከተማ ትርፍ መሬትና ቤት አዋጅ ጋር በተገናኘ የተወረሱ ቤቶችን ማለትም ኪራያቸው ከመቶ ብር በላይ የሆኑትን ቤቶች እንዲቆጣጠርና የቤት አቅርቦት ችግሮች እንዲቀረፉ ግንባታ በማካሄድ በርካታ ቤቶችን ገንብቶ ለውጭና ለአገሬው ዜጎች በዶላርና በብር እንዲያከራይ፣ እንዲያስተዳድር የተቋቋመ ግዙፍ ተቋም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ግንባታ አቁሟል፡፡ ካሉት ቤቶች ውስጥም በልማትና በሙስና ሰበብ ለግለሰቦች ተሰጥው ወደ ግል ይዞታነት በመዞራቸው፣ በይዞታው ሥር የቀሩት እየተመናመኑ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ችግሩን ለመቅረፍ ምንም ዓይነት ጥረት ሳይደረግ ለተሿሚዎች ቤት ስለሚያስፈለግ ብቻ ዜጋን ለማፈናቀል ማሰብ ሌላ ችግርን ይፈጥራል እንጂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡
ክቡር አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ኤጀንሲውን በቦርድ ሰብሳቢነት ይመሩ በነበረ ጊዜ ተቋሙ በሙስና ውስጥ መዘፈቁን ተረድተው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ያሉ ነዋሪዎች በስማቸው ውል እንዲዋዋሉ በማለት ወስነው ነበር፡፡ ውሳኔው ግን ተግባራዊ የተደረገው ለጥቂቶች ብቻ ነበር፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብለው ሲጠየቁም ሌላ መመርያ ይመጣል ጠብቁ የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡ ነዋሪዎች ይወጣል ጠብቁ የተባሉትን መመርያ እየተጠባበቁ ሳለ ግን ኤጀንሲውን እንዲያስተዳድሩ ወ/ሮ እንወይ ገብረመድህን ተሸመው መጡ፡፡ በዚህ ጊዜም ተቋሙ ይበልጡን ለተሿሚዎች ቤት ለመስጠት ሲባል ሕገወጥ በሚል ሽፋን ሕጋዊውንም ነዋሪ ሰለባ የሚያደርግ ያልተጣራ ዘመቻ ማድረግ ተጀመረ፡፡ የቤቱን የይዞታ አግባብ ሳያጣሩ ዜጋን አስወጥቶ ተሿሚን ማስገባት ሕግንና ሰብዓዊነትን አይቃረንም ወይ?
ከስህተት መማር ሲገባ አሁንም ሌላ ስህተት ለመሥራት የመኖሪያ ቤት ችግር  አደገኛ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት፣ መንግሥት ለሚሾማቸው ኃላፊዎች ራሱን ችሎ መገንባት ይገባው ነበር:: ይህንን ማድረግ እየቻለ ከዜጎች ጋር መሻማት ያለበት አይመስለኝም፡፡
ኤጀንሲው በሕግ የማይጠየቅበት የሕግ አግባብ በፓርላማ ፀድቆለት ዜጎችን እንዲያፈናቅል ሥልጣን የሚሰጠው ለምንድን ነው? በዶላር የሚከራዩት ቤት ያላቸው ግለሰቦችና የመንግሥት አካላትን የመለየት ሥራ ለምን አልተሠራም? ተሿሚዎች ሕዝቡን ሊያገለግሉ እንጂ በሕዝቡ ላይ ምሬትን እንዲያመጡ ለምን መንገድ ይከፈትላቸዋል?
ይህ ተቋም ካሁን በፊት ነዋሪዎችን ለውኃ አገልግሎት እያለ በወር ለአንድ ቤት እስከ 1,000 ብር ድረስ ያስከፍል ነበር፡፡ ነዋሪውም ተማሮ ‹‹ለቤንዚን እንኳ ይህን ያህል አናወጣም፤ እባካችሁ ችግራችንን ስሙን፤›› እያለ ይማፀን ነበር፡፡ በከተማ ልማት ቢሮ አማካይነት ለእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት የውኃ ቆጣሪ እንዲገባ ተደርጎ ችግሩ በጊዜያዊነት ተፈቷል፡፡ ‹‹በጊዜያዊነት›› ያልኩትበት ምክንያት የውኃ ቆጣሪው በመኖሪያ ቤቶች ኮሪደር አካባቢ መሆን ሲገባው መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመደረጉ የፈጠረው ችግር ስላለ ነው፡፡ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቆጣሪ አንባቢ ሠራተኞች፣ ቆጣሪው ያለበት ቦታ ለንባብ ምቹ ስላልሆነ አናነብም በማለታቸው ብዙ ገንዘብ ሳይከፈል ቆየ፡፡ መሥሪያ ቤቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ውዝፍ የውኃ አገልግሎት ዕዳ ይከፈለኝ በማለት ውኃውን በማቋረጥና ነዋሪዎችን በውኃ ዕጦት በማስጮህ ገንዘቤን አምጡ ዓይነት መደራደሪያ በማድረጉ፣ የውኃ ችግር በዘላቂነት አልተፈታም ልል አስችሎኛል፡፡ 
አላግባብ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ ግን ከመውጣት አልተገታም፡፡ የተቋሙ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ መጥተዋል፡፡ እንደውም ነዋሪውን በቅን የሚያገለግሉ፣ የአካባቢውን የፅዳትና የጥበቃ እንዲሁም የልማት ሥራዎችን የሚያካሂዱ፣ በነዋሪው የተመረጡ የነዋሪዎች ኮሚቴዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ኮሚቴዎች ኤጀንሲው ዕውቅና ከመስጠት ውጪ ግዴታውን የማይወጣ ነዋሪን ጠርቶ በማነጋገርም ይሁን በሌላ መንገድ ግዴታውን እንዲወጣ ባለማድረጉ ብዙ መሥራት የሚችለውን ኮሚቴ የተፈለገውን ያህል እንዳይሠራ አድርጎታል፡፡
በዚህ ችግር የተተበተበን ተቋም ተይዞ፣ አብረውት የከረሙት ችግሮችም ባልተፈቱበት ወቅት፣ ቤት ለተሿሚዎች ለመስጠት በሚንስትር ዴኤታ የሚመራ ኮሚቴ ማቋቋም ባልተገባ ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ ቤት የሚገነባ፣ ችግር የሚፈታ ኮሚቴ ነበር የሚያስፈልገው፡፡ ከዚህ ቀደም የቤት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ተብለው የተሠሩትን ቤቶች ለተሿሚዎች በሚል ሰበብ፣ ከደንበኞች በመውሰድ ለማደል ማሰብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣልና መንግሥት ነገሩን በጥሞና ይየው እላለሁ፡፡
(ከካሌብ ደረጀ መሸሻ፣ ከአዲስ አበባ) 
******
የአዲስ አበባን ነዋሪ ላለማፈናቀል የወጣው ረቂቅ ሕግ በቶሎ ይተግበር 
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በልማት ምክንያት ከነበሩበት አካባቢ የማይፈናቀሉበት የሕግ ረቂቅ በዝግጅት ላይ እንደሆነ መገለጹ አስደሳች ብሥራት ነው፡፡
ጳጉሜ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. የወጣው የረቡዕ ዕትም ሪፖርተር በፊት ገጹ፣ ለአዲስ አበበ ከተማ ነዋሪ አስደሳች ሊባል የሚችል ዜና ይዞ ብቅ ማለቱን አንብበን ነበር፡፡ 
መንግሥት የሚመራውን ሕዝብ የልብ ትርታ ተከታትሎ ከለካ፣ የልኬቱ ውጤትም ቀይ መስመር ውስጥ ሳይገባ የዕርምት ዕርምጃ ከወሰደ ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ያስጠብቃል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ለመግባት ቀዳዳ ፈላጊውን አነፍናፊ ሰይጣን ያስወግዳል፡፡
በሚቀጥሉት የመልሶ ግንባታ ሒደቶችም መንግሥት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከመሐል ከተማ የማይፈናቀሉበት የሕግ ረቂቅ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እንዲደረግ ማቀዱ፣ በእያንዳንዱ የከተማው ነዋሪ ስሜት ውስጥ ሲጉላላ ለነበረው የመፈናቀል ሥጋት እፎይታ ያስገኘ ስለሆነ የሚደገፍ ዕምርጃ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪ በኑሮ ብዙ ዓመታትን ካሳለፈበትና ከቆየበት አካባቢ የማይፋቅ የማይረሳ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን አካብቷል፡፡ በመሆኑም ኖሮ ካረጀበት መሐል ከተማ ለቆ መሄዱን አይፈልገውም፡፡
ይህ የሕዝብ ስሜት በመንግሥት ትኩረት ማግኘቱና ለወደፊቱ የከተማው ሕዝብ ከመሐል አካባቢዎች እንደማይፈናቀል፤ ይልቁንም እዚያው ባለበት አካባቢ ተረጋግቶ እንዲቆይ የሚያስችል የሕግ ረቂቅ እንዲዘጋጅ ማቀዱ መልካም ነው፡፡
አብሮ በልቶ አብሮ መኖርን፣ በዕድር፣ በዕቁብ፣ በሰንበቴና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ መረዳጃ ማኅበራት አማካይነት ተቆራኝቷል፡፡ በመኖሪያ መንደር ውስጥ ጠብና ውከት ቢነሳ፣ በአካባቢው የታመመ ነዋሪ መታከሚያ ቢያጣ፣ ነዋሪው  ተሰብስቦ በመወያየት ለችግሩ እልባት ይሰጣል፡፡ እንዲህ ያለውንና ሌላውንም ማኅበራዊ መስተጋብር፣ በአንድ አካባቢ ለረዥም ዓመታት አብሮ በመኖር የተገኘውን ባህላዊ ቅርርብ አናግቶ በአዲስ መንደር በአዲስ አካባቢ ከማይተዋወቀው፣ አብሮ ካልኖረው ኅብረተሰብ ጋር መደባለቅ ላልኖረበት ላላደገበትና ላለመደው ሕዝብ ይከብዳል፡፡ የትራንስፖርት፣ የሕክምና የመገልገያ ፍጆታዎችና ሌሎችም በለመዱትና ብዙ ዘመን እንደኖሩበት አካባቢ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ 
የአዲስ አበባ ነዋሪ ለብዙ ዓመታት ከኖረበት መንደር ሲፈናቀልና ርቆ ሲሄድ፣ ልጅ ወልዶ ካሳደገበት ቀዬ ሲፈናቀል ወደማያውቀው አዲስ ሠፈርና መንደር ሲሄድ ውስጡ ይጎዳል፡፡ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንደለመዱት አካባቢ አይሆኑም፤ ሸክሙ ይከብዳል፡፡
በዚያ ላይ የትምህርት ቤት፣ እንደየ ዕምነቱ የአምልኮ ሥፍራዎች ቅርበትና ርቀት ሁኔታ ወጣ ብሎ አብሮ ከኖረና ከቆየ ወዳጅ ዘመድ ጋር ተገናኝቶ ስለ ማኅበራዊ ችግሮች የሚወያይና መፍትሔ የሚያፈላልግ ማጣት በኑሮ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡
በጠቅላለው የአዲስ አበባ ነዋሪ በመሐል ከተማ አብሮ ነዋሪነቱ ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ መሠረታዊ እሴቶችን ቢገነባም እነዚያን ትቶ ሲፈናቀል፣ የሠፈር የመንደሩ፣ የጎረቤቱ፣ የልጅ፣ ያዋቂው መሠረታዊ ቁሶችና ሁለመናው ያባባዋል ሆድ ያስብሰዋል፡፡
ስለዚህ አሁን በመንግሥት የታቀደው አዲስ የሕግ ረቂቅ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከመሐል ሳይፈናቀል ባለበት የሚሰፍርበት እንዲሆን ሕጉ በመልሶ ግንባታ ሒደት ጭምር እንዲተገበር በናፍቆት ይጠበቃል፡፡
(ከታምሩ ሩንዳሳ፣ ከአዲስ አበባ)
******
ሐዋሳን እንዳየኋት
በአገራችን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ ካሉ ከተሞች ውስጥ አንዷ ሐዋሳ ናት፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን ከተማ ከሆኑትም አንዷ ናት፡፡ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ጎብኝዎች በስፋት የሚስተናገዱባት በሆነችነችው ሐዋሳ ከተማን በጎበኘሁ ጊዜ  የሚከተሉትን ችግሮች መመልከት ችያለሁ፡ 
ይኸውም እንዲሰጣቸው የሚፈልጉትን የገንዘብ መጠን ወስነው ካልሰጣችሁኝ የሚሉ ለማኞች እንዲሁም የቆሙ መኪናዎች ዕቃ ሥርቆት እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጊት በጊዜ ቁጥጥር ሥር ካልዋለ፣ ለከተማዋ ዕድገትና መሻሻል እንዲሁም የተሻለ ገቢ ለማግኘት መሰናክል ስለሚሆን የተከማው አስተዳደር እነዚህን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ ፈጣን መፍትሔ  መስጠት ወይም ዕርምጃ መውሰድ ይገባዋል እላለሁ፡፡
(አማን ኑሪ፣ ከአዲስ አበባ)
******
የእግር ኳስ ሕልም አጨናጋፊዎች 
በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብን ቀልብ ከሚስቡ በጣት የሚቆጠሩ፣ በድርጊት የተሞሉ ክንውኖች አንዱ የእግር ኳስ ጨዋታ ስለመሆኑ በርካታ ሰው እንደሚስማማበት መገመት አያዳግትም፡፡
ይህ የቡድን ስፖርት ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ በግልና በቡድን፣ የተናጠልና የጋራ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቅንጅትና ውህደትን በመፍጠር ቁርጠኝነት፣ መስዋትነትና ፅናትን አክለውበት ችሎታቸውን ተጠቅመው ወደ ውጤት መቀየር የሚችሉበት ነው፡፡
በእግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ተጫዋቾች በሚያሳዩት ልዩ ክህሎትና አስገራሚ ቴክኒክ፣ የተመልካችን ስሜት ከማርካታቸውም በላይ በማንኛውም ሰኮንድና ደቂቃ በሚፈጥሩት ያልተጠበቀ ድርጊት ያልተጠበቀ ውጤት እንዲመዘገብ ተፅዕኖ ማሳደር ያስችላቸዋል፡፡
ማንኛውም ክለብ ለታላቅ ውጤት የሚበቃው በስሜት በመነሳሳት ሳይሆን፣ አሠልጣኞችና ስፖርተኞች በሚያደርጉት ጠንካራ የአካልና የአዕምሮ ዝግጅት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ዓመታዊ የዝግጅት ወቅት ታልፎ ውድድር ሲጀመር ደግሞ ሥነ ልቦናዊ ግንባታ ተጨምሮበት በሚገኘው የልቀት ደረጃ ነው ውጤታማነታቸውን የሚወስነው፡፡
እግር ኳስ የቡድን ስፖርት በመሆኑ ውጤት ሊመዘገብ የሚችለው ሁሉም የሚፈጥሩት መስተጋብር፣ ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነት፣ መስዋትነት፣ ጽናትና ሞራላዊ እሴቶች ተጣምረው ሲተገበሩ ነው፡፡
የእግር ኳስ ተፈጥሯዊ ሒደቶች የሚጠይቋቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው በቡድኑ ውስጥ ሳያውቁም ሆነ በማወቅ በሚፈጸሙ የተሳሳቱ ድርጊቶች ሳቢያ ክለቦች ሊተገብሯቸው የተነሷቸው ሕልሞች በአጨናጋፊዎች ሲከሽፉ በተደጋጋሚ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች አልፎ አልፎ ዓይን ባወጣ መንገድ ከተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ለተጫዋች፣ አሠልጣኝ ለአሠልጣኝ፣ አሠልጣኝ ከተጫዋች ወይም በቡድን መሪዎች ደረጃም ሆነ በሌላ መንገድ ከዳኞች ጋር በሚደረግ መሞዳሞድ ባልታሰበና ባልተጠበቀ መንገድ ክለቦች ሽንፈት ይደርስባቸዋል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ በተለይ በእግር ኳስ ስፖርት ውስጥ የክለቦችን ሕልውና በሚፈታተን አካሄድ በአሠልጣኞች፣ በተጨዋቾች፣ በቡድን መሪዎችና በደላሎች አማካይነት ሕልሞች እየተጨናገፉ ወደ ቀን ቅዠትነት እየተለወጡ ነው፡፡ ይህ ወንጀል ተስፋፍቶ ሰብዓዊ ቀውስ ከመፍጠሩና ውድመቶችም ከማስከተሉ በፊት ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ከወዲሁ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶት እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሕልም አጨናጋፊዎች ከወዲሁ በሚፈጥሯቸው ውጤት የማስቀየር ወንጀሎች ዙሪያ መረጃ በመሰብሰብና በማጠናቀር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እንዲሁም በአገሪቱ የወንጀል ሕግ መዳኘት ይገባቸዋል፡፡ 
የሕልም ቀበኛ ስፖርተኞች፣ ዳኞች፣ አሠልጣኞች፣ ቡድን መሪዎች፣ ደጋፊዎችና ሌሎችም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ ሁላችንም በንቃትና በትጋት መከታተልና ማጋለጥ እንዳለብን እንመን፡፡ በስፖርት ውስጥ ሙስናን እናስቁም፡፡ ሕልም አጨናጋፊዎች ፈጣሪን እንፍራ፡፡
(አባ ሻረው፣ ከጎንደር)

0 comments :