ሴት ተማሪዎችን የማብቂያ መንገዶች... እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ቋንቋ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ንጋቷ ዮሐንስ ኣስተያየት

አዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ፣ አካባቢ ቀይሮ፣ ከቤተሰብ ርቆ መሄድ ትልቅ ፈተና ነው። በተለይ ደግሞ ሴትነት ሲጨመርበት ፈተናው እጥፍ ድርብ ይሆናል። የዩኒቨርሲቲ ህይወት ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጪ የሚኮንበት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚጀመርበት ወቅት በመሆኑ፣ በዚያ ላይ ወጣትነት ተዳምር ሁኔታዎቹ ሁሉ ለጥፋት የተመቻቹ ይሆናሉ። እናም አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከዓላማቸው ውጪ ሆነው ሲሰናከሉ ይታያሉ - በተለይ ሴቶች።
ተማሪ ንጋቷ ዮሐንስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ቋንቋ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ናት። ሴት ተማሪዎች የሚሰናከሉበትን ዘመን እሷ ጠንክራ ተወጥታዋለች። ወደ ዩኒቨርሲቲው ከተቀላቀለችበት ካለፈው ሶስት ዓመት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ብዙ ለውጦችን ማየቷን ትናገራለች። በአካዳሚም ሆነ በግቢው ውበት ዩኒቨርሲቲው እጅግ ብዙ ለውጥ አሳይቷል። በተለይ ደግሞ ሴት ተማሪዎችን ለማብቃት የሚሰራው ስራ አበረታች ነው ስትል ትገልፀዋለች።
ተማሪ ንጋቷ ተወልዳ ያደገችው በሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ ውስጥ ነው። ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማረችውም በተወለደችበት አካባቢ ሲሆን፤ ከቤተሰብ ተለይታ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጣችው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ያኔ የተለያዩ ስጋቶች ነበሯት። ሆኖም ግን በዩኒቨርሲቲው ያገኘችው የተለያየ ድጋፍ በትምህርቷ በጥሩ ነጥብ እንድትቀጥል አስችሏታል።
«ዩኒቨርሲቲው ለሴት ተማሪዎች የተለያየ ድጋፍ ነው የሚያደርገው። በተለይ የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ሴቶች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። ለሴት ተማሪዎች ብቻ መገልገያ በባለሙያ የተሟላ ክሊኒክ፣ ማደሪያ ቤታችን አካባቢ ደግሞ ቤተመጻሕፍት ተከፍቷል። እንዲሁም በተለያዩ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣል » በማለት በዩኒቨርሲቲው የሚደረገውን ድጋፍና እገዛ ትናገራለች።
«ፒጃማ ናይት» የሴት ተማሪዎች በጋራ የመወያያ የምሽት ፕሮግራም ነው። ሁሉም ሴት ተማሪዎች ፒጃማቸውን ለብሰው ይሰባሰባሉ። በዚህም ወቅት በሥርዓተ ፆታ፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣በወሊድ መከላከያ፣ በኤች አይቪና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በነፃነት የሚመክሩበት መድረክ ነው። ሁሉም ተሰብሳቢዎች ሴቶች በመሆናቸው የሚነጋገሩትም በሚመለከታቸው የህይወት ልምድ ዙሪያ ነው። ለምሳሌ ትላለች ተማሪ ንጋቷ «አንድ ተማሪ ኮንዶም እንዴት መጠቀም እንዳለባት፣ ብትደፈር ወይም ሌላ የተለየ ነገር ቢገጥማት በ72 ሰዓት ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባት ሁሉ ግልፅ የሆነ ውይይት ይደረጋል። እርስ በርስ መማማር ይኖራል። በራሪ ፅሁፎች ይሰጣሉ። እነዚህ ነገሮች የእውቀት አድማሳችንን ያሰፋሉ።»
ተማሪ ንጋቷ የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት ሴቶች መካከል አንዷ ናት። በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ድጋፎች ባይደረግላት ኖሮ ምናልባት ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ ላትደርስ እንደምትችል ታስባለች። አሁን ግን ትምህርቷን በደንብ በመከታተል በራሷ የመተማመን መንፈስ እንድትፈጥር ምክንያት ሆኗታል። በአሁኑ ወቅት ውጤቷ ከሶስት ነጥብ በላይ መሆኑን አጫውታናለች። «ካምፓስ ስንመጣ ለእኛ ሁሉም ነገር አዲስ ነው። የሥርዓተ ፆታ ክፍሉ ባያግዘን ኖሮ ምናልባት ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ይህ መሆኑ ከመጥፎ ነገር እንድንታቀብ ራሳችንን እንድንጠብቅ ምክንያት ሆኖናል» ትላለች።
ሌላዋ ተማሪ ፌቨን አብርሃም ትባላለች። የአራተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ናት። በሥርዓተ ፆታ ክበብ ስራ አስፈፃሚ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች። ተማሪ ፌቨን ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ሁለተኛ ምርጫዋ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስለነበር በዩኒቨርሲቲው የህግ ተማሪ ሆና መመደቧን ትናገራለች። በዩኒቨርሲቲ ህይወት ውስጥ ከአንደኛ ዓመት ጀምሮ ትምህርቱ እየጠነከረ የሚሄድ ነው። በመሆኑም የተማሪ ጠንክሮ መስራት አብዛኛውን ጊዜውን ለጥናት መስጠትን ይጠይቃል የሚል ሃሳብ አላት።
«በየዓመቱ የሴት ተማሪዎች ቁጥር እየበዛ መጥቷል። ሴት ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ይህ ድጋፍ የሚሰጠው በዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት አማካይነት ነው። በስሩ የሥርዓተ ፆታ ክበብ ተቋቁሟል። በዩኒቨርሲቲው ኢኮኖሚያዊ ድጋፍም ይደረጋል። በትምህርት ዘርፍ ድጋፍ አለ። የጤና እንዲሁም የሥነ ልቦና ድጋፍ ይደረጋል። በተለያየ ማህበራዊ ጉዳዮች ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች ምክር ይሰጣል» ስትል የዩኒቨርሲቲውን ጥረት ታደንቃለች።
«ተማሪዎች ከተለያየ የህብረተብ ክፍል የመጡ ናቸው። ከተማረ፣ ካልተማረ፣ የኢኮኖሚ አቅሙ ደህና ከሆነ ደግሞ ምንም ገቢ ከሌለው፣ ከከተማ ከገጠር የተሰባሰብን ነን። በትምህርቱ ደከም ያለ ይኖራል። አብዛኛው ከቤተሰቡ ወጥቶ የማያውቅ ነው። ይሄ ሁሉ ነገር በትምህርቱ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ከኢኮኖሚ አቅም እንኳን ሃንድ አውት(የትምህርት መርጃ) ኮፒ ለማድረግ የማይችሉ ተማሪዎች አሉ። አሁን ቢሮ ሄደው ያንን አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ጀምሮ የኪስ ገንዘብ እስከ መስጠት የሚደርስ ድጋፍ የሚያገኙ 750 ያህል ተማሪዎች አሉ » ስትል ጥሩ ማበረታቻ ያለቸውን ታብራራለች።
ዩኒቨርሲቲው በራሱ እና እርዳታ ሰጪዎችን በማስተባበር ጭምር ነው ድጋፍ የሚያደርገው። ከዚህም በተጨማሪ በትምህርታቸው ደከም ያሉትን በተለይ በቋንቋ ረገድ ብዙዎች የሚቸገሩበትን ለማስተካከል መምህራን ተመድበው እንዲያስተምሩ ያደርጋል።
ሴቶች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከገቡ በኋላ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ስነልቡናዊ ድጋፍ ባያገኙ ምናልባትም አሁን በሁሉም ነገር ብቁ ሆነው የሚመረቁ በርካታ ሴት ተማሪዎችን ማግኘት ይከብድ ነበር። ሴቶች የገንዘብ ችግር ሲገጥማቸው ራሳቸውን ለመለወጥ ብለው በማይፈልጉት የገንዘብ ማግኛ ባሏቸው ዘዴዎች ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ።
«ተማሪዎች በየአመቱ ሲመጡ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይደረጋል። እኔም አዲስ ሆኜ እንኳን ደህና መጣሽ መባሌ በውስጤ የነበረውን ፍርሀት አስወግዶልኛል። የዩኒቨርሲቲን ህይወት እንዳውቀው ረድቶኛል። የተማሪዎቹ አቀባበል ጨልሞብኝ የነበረውን ትንሽ ብርሀን ፈንጥቆልኛል። ብርሀኑ ደግሞ እያደር ይፈካል። እኔም ለሌላው ተማሪ የማደርገው አቀባበል ውለታን የመመለስ ያህል ነው የሚሰማኝ»ትላለች።
በካምፓስ ውስጥ ይበልጥ መሻሻል አለባቸው በማለት ተማሪ ፌቨን የጠቀሰችው እስካሁን ሴት ተማሪዎችን በተለያየ መልኩ ለመደገፍ የሚሰራው ስራ ይበልጥ ቢጠናከር የሚል ነው። እንዲሁም ሴት ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ስራ ሰርተው ራሳቸውን የሚደጉሙበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ነው የሚል ሃሳብ አንስታለች።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲስተር ትዕግስት ከበደ ሴት ተማሪዎችን በማብቃት ረገድ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ትናገራለች። ለሴት ተማሪዎች ውጤታማነት በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ከወላጅ ያልተናነሰ ነው ስትል። ከሁሉም በላይ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ የመጡበትን ትምህርት በብቃት መወጣት እንዲችሉ በማድረግ ስራ ላይ ተጠምዷል። የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ሲመጡ የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ይዘጋጃል። በዚህ ላይ ሁሉም ኃላፊዎች ተገኝተው ስለዩኒቨርሲቲው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋሉ።
ተማሪዎቹ እንደመጡበት አካባቢ የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። ሆኖም ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ ያላቸውን ባህሪ ትተው አሁን በሚቆዩበት ዩኒቨርሲቲ በእውቀትና ሥነምግባር ታንፀው በሚወጡበት ሁኔታ ላይ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣቸዋል።
«ሴት ተማሪዎች ችግር ቢያጋጥማቸው ወዴት መሄድ አለባቸው? የሚለውን እንዲያውቁ ይደረጋል። ትምህርት ሲጀምሩ የሚከብዳቸውን ሁለት ትምህርት እንዲመርጡና የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ ነው የሚደረገው። ለዚህ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ገንዘብ ለመምህራን በመክፈል ነው ተማሪዎችን የማብቃት ስራ የሚሰራው» በማለት የዩኒቨርሲቲውን ጥረት ታስረዳለች።
ሌላው ደግሞ የህይወት ክህሎት ትምህርት ነው። ይሄ የዩኒቨርሲቲውን ህይወት እንዲያውቁና ወዳልሆነ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የወላጅን ሚና ተክቶ መስራት ነው። በመሆኑም የአቻ ለአቻ ትምህርት ይሰጣል። በሥነ ምግባርና በትምህርት አርአያ የሆኑ ሴት ተማሪዎችን በመምረጥ አዲሶቹን እየኮተኮቱ አስቸጋሪውን ወቅት እንዲያልፉ ይደረጋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት በቀን ለአንድ ሰዓት በቢሮ ውስጥ እንዲጠቀሙ እድል ተሰጥቷቸዋል። ይህ ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚጠቅሙ አጋዦችን እንዲያገኙ የሚደረግበት አንዱ መንገድ ነው። ኢንተርኔትን ለሌሎች አገልግሎት መጠቀም ግን አይፈቀድም።
«የመጀመሪያ ዓመት ተማሪነት፣ ሴትነት፣ የመጡበት ማህበረሰብ ሁኔታና ባህል ተጨምሮ ሴቶቹ ይፈራሉ። በዚህ መሀል ተሰናክለው እንዳይቀሩ በሚል ነው የማንበቢያ ቦታ በማዳሪያቸው አካባቢ እንዲቋቋም የተደረገው። ነባር ወንድ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን በማታላል ጭምር ነው የሚጎዷቸው። ለምሳሌ በምሽት ሰዓት ቤተመጻሕፍቱ የቱጋ ነው ብለው ሲጠይቋቸው መፀዳጃ ቤት ድረስ የወሰዷቸው ልጆች አጋጥመውናል። በመንገድ ላይም ትንኮሳ ይገጥመቸዋል። ይህን ለመከላከል ሲባል ነው ቤተመጻሕፍቱ፣ክሊኒኩና የመዝናኛ ስፍራው በመኝታቸው አካባቢ እንዲከፈት የተደረገው። የመዝናኛ ማዕከሉ ዳማ ፣ቴኒስ፣ ዳርት፣ ቼዝ አለው። በጥናት የደከመ አእምሮአቸውን በመዝናኛዎች ዘና ያደርጋሉ። ይህ መሆኑ ሴቶቹ በራሳቸው የመተማመን ባህልን እንዲያጎለብቱ አስችሏቸዋል» ባይ ናት።
ሴት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከገቡም በኋላ ወደፈለጉበት ደረጃ እንዳይደርሱ የሚያደርጋቸው የስነተዋልዶ ጤና ችግር ነው። ስለዚህ ችግሩ እንዳይደርስባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ያም ሆኖ አስቸጋሪ ነገር ከገጠማቸው ወደመጥፎ ችግር እንዳይገቡ አገልግሎት የሚያገኙበት የስነ ተዋልዶ ጤና ክሊኒክ ተከፍቷል። በክሊኒኩ ውስጥ መጽሐፍ፣ ፊልምና ሌሎች የመዝናኛ አይነቶችን ጨምሮ የተሟላ የክሊኒክ አገልግሎት ይሰጣል። ይህ ሁሉ ሴት ተማሪዎችን ለማብቃት የተደረገ ነው።
የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለመደገፍ በሚሰራው ስራም ዩኒቨርሲቲው 750 ሴት ተማሪዎችንና አካል ጉዳተኛ ወንዶችን ያግዛል። ከእነዚህ መካከል የ500ያህሉ ወጪ በዩኒቨርሲቲው የሚሸፈን ሲሆን ለ250 ዎቹ ደግሞ ከውጭ እርዳታ ሰጪዎች የሚገኝ ነው። ለእያንዳንዳቸው ሴት ተማሪዎች በየወሩ 250 ብር ይሰጣቸዋል። ገንዘብ ለማይሰጣቸው ከቤተሰብ ትንሽም ቢሆን ገንዘብ ለሚላክላቸው ደግሞ የትምህርትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው ሲስተር ትዕግስት የምትጠቅሰው።
ሴት ተማሪዎች ለውጤት እንዲበቁ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በየትኛውም ዩኒቨርሲቲ ያልተሞከረ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ ተሞክሮ በማለት የነገረችን ደግሞ «የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በ2001 ዓ ም ባደረገው ስምምነት አንደኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች በመጀመሪያው ሴሚስተር በውጤት ማነስ ምክንያት ተባረው ከግቢው እንዳይወጡ የማቆያ አገልግሎት ይሰጥ የሚል ነው። ሌላው ደግሞ እነዚያው ተማሪዎች የትምህርት ክፍላቸውን ቀይረው (ከተመደቡበት ውጪ) በሚፈልጉት የትምህርት መስክ እንዲገቡ ዕድል ተመቻችቷል። በዘንድሮ አመትም ከመቶ በላይ ሴት ተማሪዎች የዲፓርትመንት ለውጥ አግኝተው ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል።»

ዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎችን ለማብቃት የሚያደርገው ጥረት የሚያስመሰግነው ነው። ሴትን ማስተማር ቤተሰብን ማስተማር ነውና ለሴቶቹ የሚደረገው ድጋፍ ከኋላቸው ያሉትን በርካቶችንም ያግዛል። የዩኒቨርሲቲው ጥረትም ለሌሎች በአርአያነት የሚጠቀስ ጭምር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባዋል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር