POWr Social Media Icons

Thursday, October 23, 2014

የባለፈው ዓመት የሊጉ ችግሮች አይደገሙም- ፌደሬሽኑ

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን  ውበት ያሳጡት ችግሮች እንዳይደገሙ  ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታወቀ፡፡
የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ጥቅምት 15 መጀመራቸውን ተከትሎ ነው ከወድሁ ፌደሬሽኑ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን እየተናገረ ያለው፡፡
ፌደሬሽኑ በሊጉ ጨዋታዎች ወቅት የሚከሰቱ የዳኝነት ችግሮች፣ የጨዋታዎች ረዘም ላለ ጊዜ መቋረጥና የክልል ስታዲዮሞች ደረጃ ችግርን ለመፍታት ሰፊ ስራ መስራቱን ገልጿል፡፡
የፌደሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት  የዳኞችንና የኮሚሽነሮችን አቅም ለማሻሻል ሰፊ የሙያ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ዳኞችና ኮሚሽነሮች የባለፈውን ዓመት አፈጻጽም በመገምገምም ክፍትቶቻቸውን የሚሞሉበትን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡
ፌደሬሽኑ የዳኞችን  የስራ ተነሳሽነት ለማሳደግም  ክፍያቸውን አሻሽሏል፡፡
የ2007 የሊጉ የጨዋታ መርሃ ግብር ከዚህ በፊት እንደሚከሰተው በብሔራዊ ቡድን ዝግጅትና በሌሎች ምክንያቶች በመቋረጥ ውበቱን እንዳያጣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ መዘጋጀቱን አቶ ወንድምኩን ገልጸዋል፡፡
በክልሎች የሚገኙ ክለቦች ደረጃውን የጠበቀ ስታዲዮም  እንዲያዘጋጁ  በማሳሰቡ፣ሁሉም የክልል ክለቦች ስታዲዮሞቻቸውን ለማሻሻል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዳቶ ምንድምኩን ገለፃ ፌደሬሽኑ የ2006 ዓ/ም አፈፃፅምን በመገምገም የነበሩበትን ክፍተቶች ለማሻሻል በመስራቱ የባለፈው ዓመት ችግሮች በዚህ ዓመት እንዳይደገሙ በጥንቃቄ ለመምራት ተዘጋጅቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2007 የጨዋታ መርሃ ግብር በመጪው ቅዳሜ ና እሁድ በሚደረጉ 7 ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
የሊጉ መክፈቻ ጨዋታ የካስትል ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዎች ኢትዮጵያ ቡና ከንግድ ባንክ አዲስ አበባ ስታዲዮም ቅዳሜ የሚገናኙበት ጨዋታ ይሆናል፡፡
ቀሪ 6 ጨዋታዎች እሁድ የሚካሄዱ ሲሆን፣ ደደቢት ከአዲስ አዳጊው ወልዲያ ከነማ፣ ሌላው አዲስ አዳጊ አዳማ ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከነማ ከአርባ ምንጭ ከነማ፣ መከላከያ ከመብራት ሀይል እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከሙገር ሲሚንቶ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
ምንጭ፦ EBC

0 comments :