የተሻሻለው የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መመርያ ተቃውሞ ገጠመው

ሰሞኑን ተሻሽሎ በቀረበው የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መመርያ ላይ ከአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር የተወያዩት ቤት ፈላጊዎች ተቃውሞአቸውን ገለጹ፡፡ 
የማኅበራቱ ተወካዮች ቅሬታቸውን የገለጹት፣ ከአንድ ዓመት መጉላላት በኋላ ተሻሽሎ የቀረበው መመርያ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትልና የተሻረው መመርያ የሰጠውን ጥቅም የሚያስቀር ነው በሚል ነው፡፡ 
ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸውና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ከማኅበራቱ ተወካዮች ጋር በከተማው ምክር ቤት አዳራሽ ለግማሽ ቀን ውይይት አድርገዋል፡፡ 
በተካሄደው ድንገተኛና ያልተጠበቀ ስብሰባ የማኅበራቱ ተወካዮች ከባለሥልጣናቱ ጋር ባካሄዱት ስብሰባ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የማኅበራቱ ተወካዮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ መመርያ ቀደም ሲል ተስፋ ጥለው የተደራጁበትን  የሚሸረሽር ነው፡፡ 
አዲሱ መመርያ ቀደም ሲል ወጥቶ ከነበረው መመርያ ጋር በመሠረታዊ ሐሳቦች ላይ ልዩነት አምጥቷል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው መመርያ ለፕሮግራሙ የሚቀርበው መሬት ከሊዝ ነፃ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በመልሶ ማልማት ቦታዎች ነዋሪዎች የሚነሱ ከሆነ ማኅበራቱ ካሳ እንሚከፍሉ ተገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አሠራር ቀርቶ መሬት በሊዝ እንደሚሰጥ በመጥቀሱ አዲሱ መመርያ የሐሳብ ለውጥ አምጥቷል፡፡ 
ሌላኛው ለውጥ መኖሪያ ቤቶቹ የሚገነቡት በሁለት አግባብ ነው፡፡ የመጀመሪያው በማስፋፊያ ቦታዎች ‹‹ታውን ሐውስ›› የተሰኘ የመኖሪያ ቤት ዓይነት እንደሚገነባ፣ በመልሶ ማልማት ቦታዎች ደግሞ ባለአምስት ፎቅ አፓርታማ እንደሚገነባ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣናቱ እንዳስረዱት፣ መሬት የሚቀርበው በመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ቀደም ሲል በመኝታ ክፍሎች ስፋት ክፍያው የተሰላ ሲሆን፣ ለአንድ ሰው የሚደርሰው መኖሪያ ቤት መጠን በዚሁ ሥሌት መሠረት ነበር፡፡ 
ነገር ግን በአዲሱ መመርያ ለእያንዳንዱ የማኅበር አባል 50 ካሬ ሜትር መሬት እንደሚሰጥና የማኅበር አባላቱ የተሰጣቸውን መሬት በማዋሀድ ግንባታቸውን እንዲያካሂዱ የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል ወጥቶ በነበረው መመርያ ማኅበራቱ የሚፈልጉ ከሆነ፣ መንግሥት የመኖሪያ ቤት ግንባታውን በራሱ ኢንተርፕራይዝ እንደሚያካሂድላቸው ነበር፡፡ አዲሱ መመርያ መንግሥት ከዚህ እጁን በማውጣት ግንባታውን ማኅበራቱ ራሳቸውን ችለው እንዲያካሂዱ የሚያደርግ ነው፡፡ 
የማኅበራቱ ተወካዮች ይህንን ጉዳይ ያልተጠበቀ ‹‹ዱብ ዕዳ›› ሲሉ በአስተዳደሩ አዲስ መመርያ ማዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጉዳያቸውን የሚከታተልላቸው ኮሚቴ መርጠዋል፡፡ ከተመረጡት ኮሚቴ አባላት መካከል አቶ ገዛኸኝ ጌታቸው ይገኙበታል፡፡ 
አቶ ገዛኸኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ መመርያ ብዙ ነገሮችን የሚያፋልስና ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ቀደም ሲል በወጣው መመርያ በተለይም የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ባደረጉት ገለጻ አብዛኛዎቹ ቤት ፈላጊዎች በማኅበራት ለመደራጀት ማሰባቸውን አቶ ጌታቸው አስታውሰዋል፡፡
ምክንያቱም ፕሮግራሙ የመኖሪያ ቤት ችግር ከመቅረፉ በተጨማሪ አባላቱን የቤት ባለቤት ሊያደርግ የሚችልበት አሠራር በመኖሩ ነው፡፡ ነገር ግን የማኅበራቱ ተወካዮች ከላይ ባቀረቡት የመመርያው ለውጦች ባለመስማማት ለባለሥልጣናቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ 
አቶ ሰለሞን በሰጡት ምላሽ ማኅበራቱ ቦታ መምረጥ እንደማይችሉና ያላግባብ ሀብት ለማፍራት የሚያደርጉትን ጥረት አቁመው አስተዳደሩ በሚሰጣቸው ቦታ ቤታቸውን እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ 
ይህ ካልሆነ ግን መንግሥት ባቀረባቸው ሦስት አማራጮች (10/90፣ 20/80 እና 40/60) መዞር፣ ወይም ካልሆነም በዝግ ያስቀመጡትን ገንዘብ ከነወለዱ መውሰድ እንደሚችሉ ገልጸውላቸዋል፡፡ በእነዚህ አማራጮች አልስማማም ካሉም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደሚችሉ ኃላፊዎቹ ገልጸውላቸዋል፡፡ 
በጉዳዩ ላይ መስማማት ያልቻሉ የማኅበራቱ ተወካዮች በቀጣዩ ዕጣ ፈንታቸው ላይ ከጠቅላላ የማኅበራት አባላት ጋር ለመነጋገር ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ስብሰባቸውን ለማካሄድ ቀን ቆርጠዋል፡፡ 
የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራም ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ቢደረግም ፕሮግራሙ ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ የቀረበውም መመርያ አወዛጋቢ በመሆኑ፣ በአዲሱ መመርያ የሚስማማ ማኅበር አስተዳደሩ ዘንድ ቀርቦ ቦታ መውሰድ እንደሚችል አቶ ሺሰማ በስብሰባው ላይ ማስታወቃቸውን ተወካዮቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር