ኢሕአዴግ ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ቁርጠኛ አይደለም ሲል ኢዴፓ ከሰሰ

ኢዴፓ ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ሊያደርግ የነበረው ስብሰባ የተደናቀፈው በሕጋዊ መንገድ አለመሆኑን ያረጋገጠውን የአጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት ያልተቀበለው ብቸኛው የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ኢሕአዴግ በመሆኑ፣ ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት መጠናከር ቁርጠኛ እንዳልሆነ ያረጋግጣል ሲል ከሰሰ፡፡

መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኢዴፓ እንደገለጸው፣ በመብራት ኃይል አዳራሽ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ አስቦ ሲንቀሳቀስ በፀጥታ ኃይሎች ከተደናቀፈ በኋላ፣ በጉዳዩ ላይ በወቅቱ ለሕዝቡ በመገናኛ ብዙኃን መረጃ ቢሰጥም ጉዳዩን ለጋራ ምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡ 
የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ቅሬታ ያጣራው ኮሚቴም በደረሰበት መደምደሚያ የአዲስ አበባ የሰላማዊ ሠልፍና የሕዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ክፍል የስብሰባ ጥሪ ዕውቅና ፈቃድ እንጂ የስብሰባ ጥሪ ፈቃድ ሰጥቶ እንደማያውቅ፣ የስብሰባ ጥሪ ለማድረግ የሚያስችል የመኪና ቅስቀሳ ፈቃድ ለመስጠትም ሆነ ለመከልከል የሚያስችል ሕጋዊ ማዕቀፍ የሌለ መሆኑን፣ የስብሰባ ጥሪው እንዲደናቀፍና አባላቱም እንዲታሰሩ መደረጉ ተገቢ ያለመሆኑን፣ በስብሰባ ጥሪው ላይ ፓርቲው ሲጠቀምበት የነበረው የኪራይ መኪና መቀጣቱ አግባብ ያለመሆኑን ማተቱንም ጋዜጣዊ መግለጫው ይገልጻል፡፡
ይሁንና በሪፖርቱ ላይ በቂ ውይይት ከተደረገ በኋላ ድምዳሜውን ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ሲቀበሉት ኢሕአዴግ ብቻ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን እንደቀረ፣ የኢዴፓ ጋዜጣዊ መግለጫ ያመለክታል፡፡ ይህ ድርጊትም ኢሕአዴግ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ቁርጠኝነት እንደሚጎድለው ያረጋገጠበት ድርጊት ሆኖ እንዳገኘውም ጠቁሟል፡፡ 
የምክር ቤቱ አቋም በመገናኛ ብዙኃን ተዛብቶ መቅረቡም ሚዲያው በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ኢዴፓ፣ ‹‹ፓርቲያችን ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት መጠናከር እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ በገዥው ፓርቲ መሰናክል እየገጠመው ቢሆንም፣ አሁንም ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ ይወዳል፤›› ሲልም አትቷል፡፡
ኢዴፓ በጋራ ምክር ቤት ተሳትፎው ይቀጥላል ወይ ተብለው በሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ጉዳዩ በፓርቲው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ወይም በአስቸኳይ ስብሰባ የሚወሰን ቢሆንም ገዥው ፓርቲ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመጣ ጫና ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ጥፋተኛ ናቸው የተባሉት የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ኢሕአዴግ ፈቃደኛ አለመሆኑ ከስብሰባው መከልከል ጀርባ እጁ እንዳለበት እንድንጠራጠር አድርጎናል፤›› ያሉት ዶ/ር ጫኔ፣ ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጠው ለፓርቲው ብቻ ሳይሆን ለመራጩ ሕዝብ ጭምር እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ጫኔ በተጨማሪም ድርጊቱ ምርጫ 2007ን በጥርጣሬ እንዲየዩት ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ 
በቅርቡ በብሔራዊ መግባባት ላይ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ለማዘጋጀት አስታውቆ የነበረው ኢዴፓ ዝግጅቱ ከምን እንደደረሰ የተጠየቁት ዶ/ር ጫኔ፣ ሥራ አስፈጻሚው ሲምፖዚየሙ እንዲደረግ ከቀናት በፊት የወሰነ በመሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎችን የሚያቀርቡ ገለልተኛ ምሁራንና ርዕሶችን የመለየት ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር