ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የመንግሥት ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ብሏል 
የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ለምን ወጣ መባሉ ተገቢ አይደለም - ምርጫ ቦርድ

ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥና የምርጫ አፈፃፀም ችግሮች ሳይወገዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማወጅ መዘጋጀቱ ተገቢ አይደለም ሲል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ኢማዴ-ደህአፓ ተቃወመ፡፡ መንግስት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ሲልም ፓርቲው ኮንኗል፡፡ 
የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ ሰሞኑን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባስገባው ግልፅ ደብዳቤ፤ ያለፉት አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫዎች ከመካሄዳቸው በፊት በምርጫ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚወያይበት መድረክ እንዲዘጋጅ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ከቦርዱ የተሰጠ ተግባራዊ ምላሽ የለም ብሏል፡፡ 
ሃገሪቱ “በአንድ አውራ ፓርቲ” ብቸኛ ቁጥጥር ስር መውደቋ አደገኛና አሳሳቢ ነው ያለው ፓርቲው፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአት የመገንባት ተስፋችን ጨርሶ እንዳይከስም ቦርዱ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ገዥው ፓርቲና ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚወያዩበት መድረክ እንዲያመቻች በህግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ የገባውን ቃል በማጠፍ መድረኩን ሳያመቻች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱ ፋይዳ የለውም ብሏል - ፓርቲው፡፡ 
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተሻሻለው የምርጫ ህግ፣ ለቦርዱ የተሰጠውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ የማስተባበር ስልጣን ለመቀማት ታማኝ ፓርቲዎችን በተቃዋሚ ስም አሰባስቦ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ” በመፍጠር የምርጫ ውድድር አሯሯጭ አሰልፏል ሲል ፓርቲው ተችቷል፡፡ገዥው ፓርቲ ያልተገደበ መንግስታዊ ስልጣኑን በመጠቀም የተለያዩ ጫናዎችን እያሳረፈ፣ ተቃዋሚ በሌለበት በአፈናና በጉልበት ሃገሪቱን በአምባገነንነት እየገዛ ነው ያለው ፓርቲው፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ስልጠና የምርጫ ህግን የጣሰ የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ብሏል፡፡ ለስልጠናው በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ማባከኑም አግባብ አይደለም ሲል ፓርቲው ተቃውሟል፡፡ ምርጫ ቦርድ ከስነምግባር ደንቡ ውጪ የሆነውን የኢህአዴግን አካሄድ ማስቆም ሲገባው እርምጃ አለመውሰዱ ቦርዱ በፓርቲው ተፅዕኖ ስር መውደቁን ያሳያል ብሏል - ፓርቲው፡፡ 
የኢማዴ-ደህአፓ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጠናው በመንግስት ፖሊሲዎች ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥና መንግስታዊ ኃላፊነትን የመወጣት ስራ ነው ቢሉም ለስልጠና በተሰራጩ ሰነዶች ላይ “ፓርቲያችን ኢህአዴግ” የሚሉ አገላለፆች መስፈራቸውን ጠቁመው ይሄም በቀጥታ የመንግስት መዋቅርንና ሃብትን በመጠቀም የፓርቲን አጀንዳ የማስረፅ (ኢንዶክትሪኔሽን) ስራ ነው ብለዋል፡፡ 
በስልጠናው ወቅት የተበተነው ሰነድ ስለኢህአዴግ መስመር የሚተነትን ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ሰነዱ የፓርቲ እንደሆነ እየታወቀ ስልጠናው የመንግስት ነው ማለት ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ 
“መንግስት ፖሊሲውን ለማስገንዘብና የፈፀማቸውን ተግባራት ለማሳወቅ ስልጠና ማዘጋጀት አይጠበቅበትም፤ በሴሚናርና በዎርክሾፕ መልክ መድረኮችን ማዘጋጀት ይችላል” ብለዋል ፕ/ር በየነ፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ “በምርጫ አሸንፎ ስልጣን የያዘ ፓርቲ የመንግስትን ፖሊሲ የማስረፅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልፀው ለምን ይሄን አደረጋችሁ ብሎ መጠየቅ ህዝቡ ለምን መረጣችሁ እንደማለት ነው ብለዋል፡፡ የኢማዴ-ደህአፓ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት መድረሱን ያረጋገጡት የፅ/ቤቱ ም/ዋና ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ፤ ሁሉም ፓርቲዎች በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ያላቸውን አስተያየት በፅሁፍ እንዲያቀርቡ በተጠየቀው መሰረት የቀረበ ደብዳቤ ነው፤ ቦርዱ ተሰብስቦ የሚያየው ይሆናል ብለዋል፡፡ 
ፓርቲው ለፅ/ቤታቸው ባስገባው ደብዳቤ፤ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር የሚወያዩበት መድረክ እንዲዘጋጅ ተጠይቆ ምላሽ ሳይሰጥ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት መጣደፍ አግባብ አይደለም ማለቱን የጠቀስንላቸው አቶ ወንድሙ፤ ለምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመው፤ የጊዜ ሰሌዳ ለምን ይወጣል መባሉ ተገቢ አግባብ አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡ ምክትል ዋና ኃላፊው፤ የውይይት መድረክ የተባለውን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በቀጣይ የሚያዘጋጀው ይሆናል ብለዋል፡፡ በጊዜያዊነት በወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፓርቲዎች አስተያየት ከተሰበሰበ በኋላ በቦርዱ ውይይት ተደርጎበት ሲፀድቅ፣ ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግም አቶ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ 
ወሬኛው፦ የኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ ነው

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር