በቡና ላይ የተመሠረተው ህልውና

ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ሆኗል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ትይዩ የተገነቡት ካፌዎችና ሬስቶራንቶች በረንዳቸው በደንበኞች ተጨናንቋል፡፡ ካንዱ ካፌ ፊትለፊት ሰፋ ባለ ረከቦት የተደረደሩ ሲኒዎች ስር ሳር ተጎዝጉዞ፣ እጣን ሲጨስ ይታያል፡፡
ለቡና ቁርስም በስፌት ፈንዲሻ ቀርቧል፡፡ የዕጣኑ መዓዛ ቤቱን አውዶታል፡፡ የአገር ባህል የለበሰች ኮረዳም ቄንጠኛ በሆነ መልኩ የምትቀዳው ቡና ቀልብ ይስባል፡፡
የቡናው ሥርዓት የሚጀምረው ከረፋዱ 5፡30 አካባቢ ሲሆን፣ ስምንት ሰዓት ማብቂያው ነው፡፡ ስለዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ደግሞ ወጣቶችና በአቅራቢያው በሚገኝ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሰዎች ምሳቸውን ከበሉ በኋላ ቡና ለመጠጣት ጎራ ይላሉ፡፡ ደንበኞችም ብዙ በመሆናቸው በካፌዎቹ የሚገኙ መቀመጫዎች ሁሉ ይያዛሉ፡፡ ስለዚህም በርካታዎቹ ቆመው ለመጠጣት ይገደዳሉ፡፡ በዚህ አካባቢ ጨዋታውም ይደራል፡፡
በየካፌውና ሬስቶራንቱ በባህላዊ ሥርዓት የሚቀርበው ቡና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እናም የቡና ሰዓት ከማለፉ በፊት ለመድረስ ይጣደፋሉ፡፡ ሀብታሙ አዲሱንም ያገኘነው የቡና ደንበኛው ወደ ሆነው ካፍቴሪያ ለመሄድ ሲዘጋጅ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በየቀኑ ቤተሰቦቹ ቡና ቢያፈሉም የዘወትር ደንበኛው ወደ ሆነው ሬስቶራንት ጎራ ብሎ ከቅርብ ጓደኛው ጋር ቡና እየተጎነጨ መጫወት ልምድ ሆኖበታል፡፡ በቡና ሰዓት በሬስቶራንቱ ውስጥ የሚኖረው ድባብም ደስ ያሰኘዋል፡፡ የቡና ሱስ ባይኖርበትም ሰዓቱን ጠብቆ የመጠጣት ልምድ አለው፡፡ ‹‹አንዳንድ ሰዎች የቡና ሥርዓቱን እያዩ ለመጠጣት ሲሉ ብቅ ይላሉ፡፡ ምናልባትም አቀራረቡ የተለየ መስህብነት ስላለው ደንበኞች መቀመጫ ቦታ ቢያጡ እንኳ ቆመው እንዲጠጡ አድርጓቸዋል፡፡ ዋጋውም ሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም በመሆኑ ኪስ አይጎዳም፤›› ይላል፡፡
አብዛኛው ቡና ተጠቃሚ በቡድን ስለሚመጣም ጨዋታው የደራ ነው፡፡ ሰብሰብ ብለው ከሚታዩት ቡና ጠጪዎች መሀልም ‹‹በክብር ዘበኛ ሲኒ ካልተቀዳልኝ አልጠጣም›› የሚሉ ግለሰቦች ማየቱን ይናገራል፡፡ የቡና ባህል ምን ያህል ተቀባይነት እንዳለው ያሳያል ሲል ይገልጻል፡፡
ባማረ ሥርዓት የሚቀርበው ቡና በገበሬውና በነጋዴው ላይ ምን ለውጥ አምጥቶ ይሆን ስንል በጅማ ዞን ቡናን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያመርቱ ወረዳዎች መሀል አንዷ ወደ ሆነችው ሊሙገነት ጎራ አልን፡፡ 
ወደ ወረዳዋ እስኪደርሱ ድረስ ያለው መንገድ ግራና ቀኙን በሰፋፊ የቡና እርሻ የተከበበ ነው፡፡ የወረዳው ነዋሪም በየጓሮው ቢያንስ አንድ እግር የቡና ዛፍ አለው፡፡ ይህም በጅማ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ወቅቱን ጠብቆ ከሚመጣው የቡና ንግድ ጋር በአመዛኙ የተቆራኘ ነው፡፡ 
የቡና ምርት ወቅቱን ጠብቆ በዓመት አንዴ የሚደርስ ነው፡፡ ስለዚህም አብዛኛው የቡና እርሻ ያለው ገበሬ ተጓዳኝ ሥራዎችን የመሥራት ባህሉ ዝቅተኛ ስለሆነ የቡና ወቅት እስኪደርስ ድረስ ሥራ ፈቶ ይቦዝናል፡፡ ከገበሬው ረከስ ባለ ዋጋ ቡና ገዝተው የሚያቀርቡ ነጋዴዎችም እንደዚሁ የቡና ወቅት እስኪመጣ ሥራ ይፈታሉ፡፡ ስለዚህም የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ አብሮ ይደበዝዛል፡፡ ‹‹ቡና የለማ!›› የአብዛኛዎቹ ነጋዴዎች የገቢያቸውን መቀዛቀዝ ምክንያት የሚገልጹበት መንገድ ነው፡፡
የቡና ገበሬዎች ተጓዳኝ የእርሻ ሥራ ስለማይኖራቸው በቡና ወቅት በሰበሰቡት ገንዘብ ይጠቀማሉ፡፡ ለኑሯቸው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ግብር ከመክፈል አንስቶ አልባሳትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚያሟሉትም በቡና ወቅት ቡና ሸጠው ከሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ያገኙትን ገንዘብ አባክነው እንደሚቸገሩ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎችም እንቅስቃሴያቸው ወቅት ጠብቆ ከሚመጣው ቡና ጋር በመሆኑ ለረዥም ጊዜ ሥራ ፈትተው ይቀመጣሉ፡፡
ከድር ሸሪፍ ከዚህ ቀደም ከገበሬ ቡና እየገዛ የሚያከማችበት ሦስት መጋዘን ባዶ ቀርቷል፡፡ ወደ አካባቢውም ዝር ብሎ ስለማያውቅ መጋዘኑ ያለበት ቦታ በአረም ተውጧል፡፡ በመጋዘኑ አካባቢ ያለው የቡና መገበያያ ሥፍራ ባዶ ሚዛን ይዘው ከተቀመጡ ሁለት ሰዎች በቀር ምንም አይታይበትም፡፡ እሱም ሆነ መሰሎቹ ቡና እንደልብ በሚሆንበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ወደ ጣቢያው ብቅ ማለት አይሆንላቸውም፡፡
በቡና ወቅት በሥራ የሚጠመደው ከድርም ዛሬ ላይ ቤት ወስጥ መቀመጥ ግድ ሆኖበታል፡፡ ምንም እንኳ ቤቱ ሙሉ ቢሆንም በእጁ ያለው ገንዘብ ያሻውን እንዲያደርግ ስለማይፈቅድለትም ደስተኛ አይደለም፡፡
እንደ እሱ ገለጻ፣ የቡና ንግድ በሚጧጧፍበት ከኅዳር ወር ጀምሮ የመገበያያ ስፍራው በገበሬና በነጋዴ ይሞላል፡፡ በዚህ ጊዜ የገበሬውም ሆነ የነጋዴው ኪስ ይዳብራል፡፡ የአብዛኛው ሰዎች ኑሮም የቡና ምርት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የተለያዩ አልባሳት፣ የቤት ቁሳቁስ እንዲሁም ሌሎች መገልገያ ዕቃዎችን መሸመትና ዘና ማለት የተለመደው በቡና ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ገበያው ላይ የተለየ መነቃቃት  ይታያል፡፡
‹‹የቡና ወቅት ሲያበቃ አብዛኛው ሰው ባዶ እጁን ይቀራል›› የሚለው ከድር፣ ‹‹እንደ እኔ ያለው የቤተሰብ ኃላፊ ደግሞ ቆጥቦ ይይዝና ኑሮውን ለመግፋት ይሞክራል፤›› ይላል፡፡
 በአካባቢው የሚገኙ አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች ሊሙገነት ከሚገኘው የቡና መገበያያ ጣቢያ ብቅ ማለት ቢተውም ገበሬዎች ለክፉ ቀን ብለው ያስቀመጡትን ቡና በማዳበሪያ ቋጥረው በማምጣት ስለሚሸጡ፤ አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉትን ገበሬዎች የሚጠባበቁ ነጋዴዎች አሉ፤ ከእነዚህም አንዱ ዮሐንስ አዱኛ ነው፡፡ 
‹‹ከዚህ ቀደም ስፍራው የሞቀ ነበር›› የሚለው ዮሐንስ ወደ ተዘጉት ቤቶች በአገጩ እየጠቆመ ‹‹ይህ ሁሉ ተዘግቶ የሚታየው ቤት ተከፍቶ በራፉ ላይ ሚዛን ሲደረደር ደስ ያሰኛል›› በማለት የቡና ወቅት ባለመሆኑ ነጋዴዎች በራቸውን እንደዘጉ    ይገልጻል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ምንም እንኳን ወደ መገበያያ ጣቢያው ብቅ እያለ ቡና የሚያመጡ ገበሬዎችን ቢጠባበቅም ገበሬዎች ሊመጡም ላይመጡም ስለሚችሉ የሚቦዝንበት ሰዓት እንደሚበዛ ይናገራል፡፡ በርካታ ነጋዴዎችም በዚህ ምክንያት ከአንድ ወቅት በላይ እንደማይገኙ ጠቅሶ፣ ነገር ግን ከግብይት ስፍራው የጠፉ ሁሉም ነጋዴዎች በሥራ ዕጦት ብቻ እንዳልሆነ፣ በየመንደሩ እየዞሩ መንግሥት ካስቀመጠው የግብይት ዋጋ ጨምረው በኮንትሮባንድ እንደሚገዙ ይህ ደግሞ ለቡና ነጋዴው ሥጋት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩልም ምንም እንኳ የቡና ወቅት ቢሆንም አንዳንዴ ገበሬዎች የቡና ዋጋ ከፍ እስኪል ድረስ ምርቱን በማስቀመጣቸው በርካታ ነጋዴዎች ሥራ ይፈታሉ፡፡  አልፎ አልፎም የሚያገኙትን የቡና ምርት በመተማመን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገቡ ጥቂት አይባሉም፡፡ አንዳንድ ገበሬዎች በቂ ገንዘብ ስለማያስቀምጡ ‹‹የዛሬ ዓመት ቡና ሸጬ እከፍላለሁ›› በማለት አስቀድመው ገንዘብ ይበደራሉ፡፡ 
ይሁን እንጂ የቡና ዋጋ በሚወርድበት ሰዓትና ዝናብ በሚበዛበት ጊዜ የቡና ምርታቸው በበሽታ ይጠቃል፡፡ ተስፋ ያደረጉትን ገንዘብ ማግኘት ያዳግታቸዋል፡፡ በዚህም የአብዛኛው ገበሬ ሕይወት ችግር ውስጥ የሚገባ ሲሆን፣ ነጋዴውም የገፈቱ ቀማሽ ይሆናል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ሥራ ፈትቶና ምርቱን ተስፋ አድርጎ ሲጠባበቅ የቆየውን ገበሬና ነጋዴ ቤት ንብረት ያሸጣል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ እንደተናገሩት፣ አብዛኛው ቡና አምራች ገበሬ ተጓዳኝ እርሻ አይሠራም፡፡ ስለዚህም ምርቱን በሽታ በሚያጠቃበት ጊዜ ያለውን ንብረት ሁሉ ለመሸጥ ይገደዳል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ወደ ሌላ የእርሻ ማሳ በመሄድ ለግለሰቦች ተቀጥረው የሚሠሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንድ ችግሩ የጠናባቸው ወጣቶችም ከየገበሬው ማሳ የቡና ችግኞች በመዝረፍ ሸጠው በሚያገኙት ገቢ ሕይወታቸውን ለመምራት ይጥራሉ፡፡ 
ግለሰቡ የአካባቢውን ነዋሪ አስተባብረው የተከሉት 500 የቡና ችግኝ በነጋታው መነቀሉን ተከትሎ ያጋጠማቸውንም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ ‹‹እንደገና ሌሎች ችግኞች መልሼ ተከልኩ፡፡ ምሽት ላይም በድጋሚ እንዳልዘረፍ ለጥበቃ ወጣሁ፡፡ በትሬዬን ይዤ ጢሻ ስር ቁጭ ብያለሁ፡፡ ከዚያም ሁለት ወጣቶች የኔ ማሳ ውስጥ ገቡ፣ ችግኝ መነቃቀልም ጀመሩ፡፡ ፈጥኜ ደረስኩኝ፡፡ የአካባቢውን ሰውም እንዲተባበረኝ አድርጌ ሌቦቹን አስያዝኩኝ፡፡››
በጉዳዩ የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ጃፈር አወልን አናጋግረናቸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በቡና ላይ ብቻ የተመሠረተው የነዋሪው ሕይወት የረዥም ጊዜ እውነታ ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ዕቅድ ተይዞበት እየተተገበረ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ለሕዝቡ ስለ ገንዘብ ቁጠባ ሥልጠና እየተሰጠ ሲሆን፣ ገንዘብ መቆጠብ የማይችለውን ደግሞ ቡናውን አንዴ ሸጦ ከመጨረስ እየቀነሱ በመሸጥ እስከ ዓመት ድረስ የሚዘልቁበት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ ስለዚህም ቀደም ሲል በወረዳው ከነበረው ብቸኛው የንግድ ባንክ በተጨማሪ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ሕብረት ባንክና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ገብተዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡን እየመከርን የቁጠባ ባህሉ እንዲዳብር እናደርጋለን›› የሚሉት አስተዳዳሪው አበረታች ለውጥ ከወዲሁ በመመዝገብ ላይ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር