ግራ ያጋባው የኢትዮጵያ የአዘጋጅነት ጥያቄ

ከሰሞኑ የአብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ መነጋገሪያ የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት አለመቻል እንደ አንድ አገራዊ አጀንዳ እያነጋገረ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አዲስ አበባ ላይ ጠቅላላ ጉባኤውን ማሰናዳቱን ተከትሎ አብዛኛው የስፖርት አፍቃሪ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የአስተናጋጅነቱ ዕድል እንዲሰጣት ለካፍ ያቀረበችው ጥያቄ እንድትጠቀምበት ይረዳታል ተብሎ ቢጠበቅም፣ የኋላ ኋላ ግን ‹‹አቅም የለንም›› በሚል ምክንያት ፍላጐቷን ወደ ጎን ማድረጓ ከፌዴሬሽኑ ተሰምቷል፡፡
‹‹ሲጀመር ምን ያህል አቅም ኖሮን ነበር?›› ሲል የሚጠይቀው የእግር ኳስ ቤተሰብ አገሪቱ የ2017ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ዕድሉ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ አገሮች አንዷ ሆና መቅረቧ አስገራሚና በዕቅድ ያለመመራት አሠራር መኖሩን በግልጽ እንደሚያመለክት ያወሳሉ፡፡
ካፍ ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ባደረገው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከተመለከታቸው አጀንዳዎች የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ለካሜሮን፣ የ2021 ለአይቨሪኮስት፣ የ2023 ለጊኒ የአስተናጋጅነቱን ዕድል የሰጠበት ይጠቀሳል፡፡ የ2017ቱን ቀደም ሲል የአስተናጋጅነቱን ዕድል ለሊቢያ የተሰጠ መሆኑ ቢታመንም፣ ወደ ኋላ ላይ ግን በአገሪቱ በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ካፍ ዕድሉን ለሌሎች አገሮች አሳልፎ እንደሚሰጥ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ አልጄሪያና ዚምባቡዌ የ‹‹እናዘጋጃለን›› ጥያቄያቸውን ለካፍ አስገብተዋል፡፡ የመጨረሻው ቀን ገደብም መስከረም 30 ቀን መሆኑም ይታወቃል፡፡
ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ማስተናገዷን በመጥቀስ፣ በአህጉር ደረጃ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የ2017ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በዚህ እየተጠናቀቀ በሚገኘው ወር መጀመርያ ለካፍ ያቀረበችውን ጥያቄ ማንሳቱን በይፋ አስታውቋል፡፡ በማያያዝም በ2020 የሚደረገው የቻንና በ2025 የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ዕድሉ እንዲሰጣት ጠይቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የቻለው ከፌዴሬሽኑና ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም ዝርዝር ግምገማና ጥናት ካደረገ በኋላ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተሟላና አስተማማኝ ሰነድ አቅርቦ ከመወዳደር አንፃር የመሠረተ ልማትና ተዛማጅ የግብዓት እጥረት መኖሩን በማረጋገጡ ነው፡፡
የእግር ኳስ ቤተሰቡም ፌዴሬሽኑ ግራ የሚያጋባ የአስተናጋጅነት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት አመራሮቹ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር መክረው ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸው እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ 
ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ካነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች አምባሳደር ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሒ ይጠቀሳሉ፡፡ አምባሳደሩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዲህ ዓይነቱን አህጉራዊ የውድድር ዝግጅት ለማሰናዳት ሲያስብ በቅድሚያ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በጥሞና ማጥናትና ከሚመለከተው አካል ጋር መምከርና ከስምምነት መድረስ ነበረበት፡፡
ካፍ ለውድድር አዘጋጅነት ለሚመርጣቸው አገሮች የሚያበቁ መስፈርቶች ምን ምን እንደሆኑ ጠንቅቆ ማወቅ፣ አውቆም ፍላጎቱን አጣጥሞ ለመሄድ ከባለድርሻ አካላት ማለትም ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በሐሳቡ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሐሳቡ መቅረብ እንደነበረበትም ይገልጻሉ፡፡ አሁን ግን የተሠራው ሥራ በተቃራኒው ከመሆኑም በላይ አካሄዱም ለአገሪቱም ሆነ ለእግር ኳሱ እንደማይበጅ ጭምር አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አሁን ያደረገው ዓይነት በዕቅድ ያልታገዘ አካሄድ ሲፈጸም ይህ የመጀመርያው እንዳልሆነ የሚገልጹት አምባሳደሩ፣ የቀድሞው አመራሮች አምና ሐዋሳ ላይ በተደረገው አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት የምክክር መድረክ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ የ2017 አፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን ነግረውናል፡፡ ይሁንና ባሳለፍነው ሳምንት የ2017 አስተናጋጅ አገር ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ አልተካተተችም፡፡ ይህም እንደዚህ ዓይነት ያሉ ትልልቅ አጀንዳዎች ምንም እንኳን የእግር ኳስ ውድድር ቢሆንም፣ ግን ደግሞ በጊዜ ሰሌዳ በዕቅድ ተይዞና የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ሳይቀር ይሁንታን ያገኘ መሆን ይጠበቅበት ነበር፤›› ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ ሌላው ያከሉት፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አባል አገሮች ብዛት 52 ሲሆን፣ ነገር ግን አፍሪካውያን ይህን ያህል ድምፅ ይዘው በፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እንዴትና በምን አኳኋን ሊጠቀሙበት አለመታየታቸው የተረዱት ላለመሆኑ ማሳያዎችን ያቀርባሉ፡፡
በሚቀጥለው የፈረንጆች አዲስ ዓመት የፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚኖር የሚገልጹት አስተያየት ሰጪው፣ ሁሉም የካፍ አባል አገሮች አሁን በሥልጣን ላይ ለሚገኙት ሴፕ ብላተር ድምፃቸውን ለመስጠት ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ በተደረገው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ ከስምምነት መድረሳቸውን ማረጋገጣቸውን ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ግን ይህ ተፈጻሚ ለመሆኑ ሥጋት እንደሚፈጥርባቸው ለዚህም እ.ኤ.አ. በ1998 ፈረንሳይ ላይ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ማግሥት አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሴፕ ብላተር ዕጩ ሆነው ከመቅረባቸው አስቀድሞ ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት በብቸኝነት የቀረቡት ሲዊድናዊው ጆሃንሰን እንደነበሩ፣ የካፍ አባል አገሮችም ለጆሃንሰን ድምፃቸውን ለመስጠት መጀመርያ ቡርኪና ፋሶ ላይ ተስማምተው ካበቁ በኋላ ሚስተር ብላተር መጨረሻ ላይ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ ሲያሳውቁ፣ አፍሪካውያኑ የተከፋፈሉበትና በኋላም ጥቂቶቹ ቀደም ሲል በወሰዱበት አቋም መሠረት ለጆሃንሰን ድምፃቸውን ሲሰጡ በርካታዎቹ ግን አሁን በሥልጣን ላይ ለሚገኙት ብላተር መስጠታቸውን ያስታውሳሉ፡፡
አፍሪካውያን ባላቸው ድምፅ አቋም ይዘው ቢዘልቁ ግን ባላቸው ድምፅ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ ይህ ተፅዕኖ ለአህጉሪቱ እግር ኳስ መሠረተ ልማት ሳይቀር የጎላ ድርሻ እንደሚኖረውም ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨምሮ በእንደዚህ ዓይነቶቹ መድረኮች በአቋማቸው ሊፀኑ እንደሚገባ ጭምር ይመክራሉ፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተርጋዜጣ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር