በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ፒቪኤች ግሩፕ በሐዋሳ ከተማ የራሱን ፋብሪካ የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው ተሰማ

በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ፒቪኤች ግሩፕ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመክፈትና ሩቅ ምሥራቅ የሚገኙ ደንበኞቹም ፋብሪካዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዛውሩ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር እየተደራደረ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡ 
ቶሚ ሂልፊገር፣ ካልቪን ክሊን፣ ቲምበርላንድና አይዞድ በሚባሉ የልብስ ብራንዶች የሚታወቀው ይህ ግዙፍ ኩባንያ፣ የደቡብ ክልል መቀመጫ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ የራሱን ፋብሪካ የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡ ኩባንያው ራሱ ከሚያቋቁመው ፋብሪካ በተጨማሪ፣ ሩቅ ምሥራቅ በሚገኙ አገሮች ልብስ አምራች ደንበኞቹ ፋብሪካቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዛውሩ ፍላጎት አሳይቷል፡፡ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየመከረ መሆኑ ታውቋል፡፡
የኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ በመምጣት ድሬዳዋ፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ዞኖችን ጎብኝተዋል፡፡ በቆይታቸው ወቅት የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ከመጎብኘታቸውም በተጨማሪ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ጋር በወደፊት ዕቅዶች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ፒቪኤች ግሩፕ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የአልባሳት ገዥና ሻጭ ነው፡፡ ኩባንያው ለደንበኞቹ የገንዘብ አቅርቦት ያመቻቻል፡፡ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ያሬድ መስፍን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው 60 ሺሕ ሔክታር መሬት ለጥጥ ልማት ጠይቋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በጥጥ ልማት የሚሆን መሬት በደቡብ ክልል በማፈላለግ ላይ ነው ብለዋል፡፡ 
እ.ኤ.አ. በ2012 በወጣ መረጃ ኩባንያው በዓመት 6.04 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስመዝግቧል፡፡ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተፈላጊ የአልባሳት ብራንዶች ባለቤት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ባደረጋቸው ስምምነቶች አማካይነት በርካታ ታዋቂ ብራንዶችን ያስተዳድራል፡፡ 
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ መንግሥት ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ገቢ የማግኘት ዕቅድ ስላለው ብዙ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች መግባታቸው ወሳኝ ነው፡፡ 
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፒቪኤች ግሩፕ አሥር ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ያለው ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ የዚህ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በግብይት፣ በቴክኒክና በአመራር ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላል፡፡ ለአገሪቱም የወደፊት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 230 ኩባንያዎች በጨርቃ ጨርቅና በጋርመንት ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለጥጥ ምርት አመቺ ከመሆኗም በተጨማሪ፣ መንግሥት ለዘርፉ የቀረፃቸው የማበረታቻ ፕሮግራሞች በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን እየሳበ በመሆኑ ከዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ አቅዷል፡፡
ባለፈው ሳምንት በዘርፉ ባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው እንዳሉት፣ የጨርቃ ጨርቅና የጋርመንት ዘርፍ ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው 21.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር፣ በ2006 ዓ.ም. ትልቅ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚጠናቀቅበት በዚህ ዓመት ከዘርፉ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በጥጥ አቅርቦትና በሌሎች አነስተኛ ችግሮች ዕቅዱን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ እየተቀረፉ በመሆናቸው በዘርፉ ከፍተኛ ተስፋ መኖሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የጨርቃ ጨርቅና ፋብሪካዎች ምርት ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ፣ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም 90 በመቶ የማድረስ ዕቅድ ነበር፡፡ ነገር ግን ሽያጩ በዚህ ደረጃ ካለመገኘቱም በላይ ፋብሪካዎቹ የማምረት አቅማቸውን 50 በመቶ ያህል እየተጠቀሙ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች በዓለም ላይ ትልልቅ የሚባሉ ገዥዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ በመሆናቸው፣ በሽያጭ በኩል ያለው ችግር እንደሚፈታ እምነታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ዜናው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር