ሳንሻይን ኮንስትራክሽን የሞሮቾ፧ዲምቱና ቢታና መንግድ ልገነባ ነው

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሙሉ በሙሉ መንግሥት በሚመድበው ወጪ ይገነባሉ የተባሉ የሁለት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን ለሁለት አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ እንዲገነቡ ሰጠ፡፡ 
ሁለቱ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የሚገነቡዋቸውን የሁለት መንገዶች ፕሮጀክት ኮንትራት ስምምነት ባለፈው ዓርብ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የሚገኙትን ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራዎችን የተረከቡት ደግሞ ማክሮ ጀኔራል ኮንትራክተር ትሬዲንግና ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ናቸው፡፡ ሁለቱም ኮንትራክተሮች በመንገድ ሥራ ዘርፍ ላይ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ በእጃቸው ያለውን ሥራ በአግባቡ ገንብተው በማጠናቀቃቸው ተጨማሪ ሥራ ሊሰጣቸው መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው ማክሮ ኮንስትራክሽን እንዲገነባ የተሰጠው የመንገድ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞንና የባሌ ዞንን የሚያገናኘውን የአዳባ አንገቱ መቶ ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ማክሮ ኮንስትራክሽን ይህን መንገድ ለመሥራት የተዋዋለው 1.25 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ግንባታውም በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለተኛውን የመንገድ ፕሮጀክት ኮንትራት የተፈራረመው ደግሞ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተሰጠው የመንገድ ፕሮጀክት በደቡብ ክልል የሞሮቾ፣ ዲምቱና ቢታና የ60.8 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተዋዋለበት ዋጋ 995.01 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታው በሁለት ዓመት ከአምስት ወራት የሚጠናቀቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሰንሻይንና ማክሮ የሚገነቡዋቸው ሁለቱ መንገዶች ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የመንገድ መሠረተ ልማት ያልነበራቸው እንደሆኑ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ 
የሞሮቾ፣ ዲምቱና ቢታና መንገድ ከአዲስ አበባ ሞምባሳ ናይሮቢ የመንገድ ኮሪደር ጋር በማገናኘት በመንገዱ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነሰና በማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የመንገዱ ግንባታ የትላልቅና የአነስተኛ የውኃ መተላለፊያ ቱቦዎችና በርካታ ስትራክቸር ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡ 
ከዚሁ መንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ እንደ ሁለተኛ ምዕራፍ የተያዘው የሞሮቾ፣ ዲምቱና ቢታና ሶዶ 43.3 ኪሎ ሜትር መንገድ ሥራ እንደሚሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም የዲዛይንና የግንባታ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ 
እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ የአዳባ አንገቱ ፕሮጀክት መገንባት በተለይ ከአዲስ አበባ በዶሎ መና በኩል አንገቱ ለመድረስ 712 ኪሎ ሜትር ያስኬድ እንደነበር፡፡ አዲሱ መንገድ ግን 400 ኪሎ ሜትር በማሳጠር ጉዞው 312 ኪሎ ሜትር ብቻ እንዲሆን ያስችላል፡፡
በማክሮ የሚሠራው መንገድ ድልድዮችን፣ ትላልቅና አነስተኛ የውኃ መተላለፊያ ቱቦዎችንና ሌሎች ስትራክቸሮችን የያዘ ነው፡፡ 
ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ለሚገነባው መንገድ የምሕንድስናና የማማከር ሥራውን አማካሪ ለመምረጥ በሒደት ላይ ነው፡፡ ማክኖ ለሚገነባው መንገድ ግን የምሕንድስናና የማማከር ሥራውን እንዲሠራ ኔት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ የተባለ አገር በቀል ኮንትራክተር እንደተመረጠ ታውቋል፡፡ 
የሁለቱን መንገድ ፕሮጀክቶች ኮንትራት ስምምነት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኩል የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ፈርመዋል፡፡ ሰንሻይንን በመወከል የሰንሻይን ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ ማክሮን በመወከል ደግሞ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ማሞ ፈርመዋል፡፡ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ ሁሉም ኮንትራክተሮች በአስፓልት ኮንክሪት ግንባታ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ነው፡፡ 
ከዚህም በላይ ግንባታዎቹ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች መገንባታቸው የውጭ ምንዛሪን እንደሚያድን ተገልጾ፣ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ተሳትፎና አቅም እያደገ መሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡ ሥራው የተሰጣቸው ኮንትራክተሮች እንዳመለከቱትም በተሰጣቸው የጊዜ ገደብና በተቀመጠው የጥራት ደረጃ እናስረክባለን ብለዋል፡፡ 
ሰንሻይን ከዚህ ቀደም ከፊንጫ ለምለም በረሃ፣ ሙከጡሪ ዓለም ገበያ፣ ያቤሎ ተተሌ፣ ከአሊ ውኃ እስከ ጉራራ፣ ከባንቢስ ቶንጎ፣ ከዝዋይ ቡታጅራ፣ ከቡታጅራ ጉብሬ፣ ከዓለም ገበያ ዋል ባረክ መንገዶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ያስረከበ ሲሆን፣ ከመሃል ሜዳ ሐሙስ መንገድ ፕሮጀክትን ደግሞ በመገንባት ላይ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡  
ማክሮ ኮንስትራክሽንም ከዚህ ቀደም ከባለሥልጣኑ ከተረከባቸው ሥራዎች የበቶ አንድና ሁለት ድልድይ ግንባታዎችን አጠናቅቆ አስረክቧል፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ከሆነ ማክሮ በአሁኑ ወቅት ከሃርገሌ ዶሎ ባዲ አዶና ከነሃሌ አብአላ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ሁለቱም ፕሮጀክቶች ከ97 በመቶ ላይ መጠናቀቃቸውንም ይጠቅሳል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተርጋዜጣ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር