የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት መመሥረቻ ሰነዶች ላይ ስምምነት ተደረሰ

ከመስከረም 29 እስከ መስከረም 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በመተዳደሪያ ደንቡና በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው የመጨረሻ የምክክር መድረክ ላይ በተፈጠረው ስምምነት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በምሥረታ ዋዜማ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ መሥራች ጉባዔው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡ 
በሁለቱ ቀናት ውይይት ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች፣ የሚዲያ ተመራማሪዎችና አማካሪዎች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪካ አዳራሽ ስለመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለሁለት ቀናት በተደረገው ውይይት ባለፉት አሥር ዓመታት ሲያወዛግቡ የነበሩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ በመድረሱ፣ ‹‹ትልቅ ዕርምጃ›› እንደሆነ የምክር ቤቱ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡
ምክር ቤቱን ለመመሥረት ቁልፍ የሆኑት የመተዳደሪያና የሥነ ምግባር ደንቦች ላይ ሰፊና በንቁ ተሳትፎ የታጀበ ግልጽ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በተለይ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ታቅፈው ያሉ አንዳንድ ነጥቦች አወዛጋቢነታቸው ግልጽ ነበር፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ የተካተቱት የሕግ መሠረት፣ የተፈጻሚነት ወሰን፣ ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የሕግ ሥልጣን ያለው የመንግሥት አካልን መለየት፣ በምክር ቤቱ አባልነት መሠረት ግለሰብ ጋዜጠኞች ሳይሆኑ የሚዲያ ተቋማት መሆናቸው፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የአገልግሎት ዘመን አራት ዓመት መሆን፣ የፓናል አባላት ስብጥርና ምንጭ፣ የመንግሥት ሚናና የምክር ቤቱ የገቢ ምንጭ ዘርፈ ብዙና ሰፋ ያለ የውይይት መነሻ ነበሩ፡፡ ከመተዳደሪያ ደንቡ በተቃራኒ በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ መጠነኛ ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይሁንና በጥቅም ግጭት፣ በጥላቻ ንግግር (በተለይም ፖለቲካዊ አስተሳሰብን መሠረት ባደረጉ ላይ)፣ የቃላት አምታችነትና አሻሚነት፣ የኤዲቶሪያል ነፃነትን መጋፋት፣ የሚዲያ ማኅበራዊ ኃላፊነት፣ መልስ የመስጠት መብት፣ ሚስጥራዊ (ስውር) መሣሪያዎችን መጠቀምና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ መጠነኛ ውይይቶችና ክርክሮች ተደርገዋል፡፡
የአደራጅ ኮሚቴው አባላት ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ ከዛሚ ኤፍኤም፣ አቶ አማረ አረጋዊ ከሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር (ሪፖርተር)፣ አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ፣ አቶ ፀጋልዑል ወልደኪዳንና እንዲሁም አቶ አበበ ባልቻ ከሸገር ኤፍኤም፣ አቶ ዘሪሁን ተሾመ ከዛሚ ኤፍኤም፣ አቶ አብዱ አሊ ሒጅራ ከሆርን ኦፍ አፍሪካ ፕሬስ ኢንስቲትዩት፣ ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት፣ አምባሳደር ካብራል ብላይ አሚህሬ ከጋና፣ ዶ/ር ዘውድነህ በይን በአወያይነት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እውነቱ ብላታ መግሥትን በመወከል ያደረጉት ንቁና በጠንካራ ነጥቦች የታጀበ ተሳትፎ በመድረኩ የተነሱት የተለያዩ ሐሳቦች እንዲሰበሰቡና ወደ ስምምነት እንዲያመሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሚዲያው ራሱን በራሱ በመቆጣጠር መንግሥት የሚያደርገውን ቁጥጥር ጣልቃ ገብነት ለመቀነስ ያገለግላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የጋዜጠኝነት ሙያን የሚገዙ ሙያዊ ደረጃዎችን በማጎልበት ጋዜጠኛው የሚግባባቸውን የጋራ ቋንቋዎች በመፍጠር፣ የጋዜጠኛውን አቅም በማጎልበት፣ አጥፊዎችን በአደባባይ በመኮነን፣ ሕዝባዊ ተቀባይነትን በመጨመር፣ ከመንግሥት ጋር ያለው የሚዲያ ግንኙነት እንዲሻሻል በማድረግ፣ ለተበዳይ ተጠቃሚዎች መፍትሔ በመስጠት፣ ሙያውን ከውስጣዊና ከውጫዊ ተፅዕኖ ለመጠበቅ ትልቅ አትዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ዶ/ር አብዲሳ አስረድተዋል፡፡ 
የአደራጅ ኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ የምክር ቤቱን ሚና በአግባቡ ባለመረዳት እስካሁን ለማቋቋም የተደረጉ ጥረቶች በቀላል ምክንያቶች መስተጓጐላቸውን አስታውሷል፡፡ ይሁንና ሳይቋቋም በመዘግየቱ ኅብረተሰቡ፣ መንግሥትና ሚዲያው ራሱ በርካታ ጉዳቶች እንደደረሱበትም አመልክቷል፡፡ ከገንዘብ፣ ከጊዜና ከተዓማኒነት ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚዲያ ጥፋቶችን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ የተለመደ መሆኑን የጠቆመው አቶ አማረ፣ የምክር ቤቱ መቋቋም እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንደሚቀርፍ አስገንዝቧል፡፡
ሚያዚያ 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል የዓለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ በተከበረበት ዕለት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴንና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሽመልስ ከማል የሚዲያ ኢንዱስትሪው በፈቃደኝነት የራሱን የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ካላቋቋመ፣ መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል በሚያወጣው ሕግ አማካይነት አስገዳጅ ምክር ቤት እንደሚያቋቁም ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ወ/ሮ ሚሚ በመሠረታዊ ሰነዶች ላይ የተደረሰው ስምምነት ላይ የተሰጡትን ማዳበሪያ ሐሳቦች በማካተት ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰነዶች ተደርጎበት ለምሥረታው ዝግጁ እንደሚሆኑ ለሪፖርተር አስረድታለች፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር