የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጥሰው ለመግባት ሞከሩ

  • በዋሺንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መሳሪያ የተኮሰው
 የፀጥታ ሰራተኛ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ

በሳምንቱ መጀመሪያ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የተደረገውን ጥሰት ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕም በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተቃዋሚዎች ተመሳሳይ የጥሰት ሙከራ መደረጉን ምንጮቻችን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በስዊድን ስቶክሆልም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ባለፈው ረቡዕ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ተመሳሳይ የጥሰት ድርጊት ለመፈፀምና በስዊድን የኢትዮጵያ አምባሳደር ወይንሸት አሰፋ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቃት ለማድረስ እንደሞከሩ የጠቆሙ ምንጮች፤ የፀጥታ ሃይሎች ደርሰው ሙከራውን እንዳከሸፉት ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ቅጥር ግቢ  ጥሰው ከገቡ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ጋር በተፈጠረ አተካሮ መሳሪያ ወደ ላይ የተኮሰው የኤምባሲው የፀጥታ ሰራተኛ ያለመከሰስ መብቱን ተጠቅሞ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስ ኃላፊ ጄን ሳኪ አስታወቁ፡፡
ባለፈው ሰኞ  የተወሰኑ ያለ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በተፈጠረ አምባጓሮ ሰለሞን ገብረስላሴ (በቅፅል ስሙ ወዲ ወይን) የተባለው የኤምባሲው የፀጥታ ሰራተኛ መሳሪያ በመተኮሱ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግለሰቡ ያለመከሰስ መብት ተነስቶ ጉዳዩ በአሜሪካ ፍርድ ቤት እንዲታይ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጥያቄው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ አገሩ እንዲመለስ ተደርጓል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ምክንያት ከአሜሪካ የወጣ ማንኛውም ዲፕሎማት ወደ አሜሪካ መመለስ የሚችለው ክሱ በፍርድ ቤት እንዲታይ ብቻ ነው፡፡
በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የተፈጸመውን ጥሰት እንዲሁም የኤምባሲውን ደህንነት ጉዳይ በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላቀረብነው ጥያቄ፣ የኤምባሲው የኢንፎርሜሽንና ፕሬስ ኃላፊ ካትሪን ዲዮፕ በሰጡት ምላሽ፤ “በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በግለሰቦች በተፈፀመው ድርጊት በጣም አዝነናል፤ ነገር ግን ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ አስተየያየት መስጠት አንችልም፣ በዋሽንግተን ዲሲና በሌሎች ግዛቶች ለሚገኙ ኤምባሲዎች ደህንነት አሜሪካ ትኩረት እንደምትሰጥ እናረጋግጣለን” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚያደርገውን ጥበቃ በእጅጉ እንደሚያደንቁም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፅህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መጣስንና መሳሪያ ስለተኮሰው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባልደረባ ተጠይቀው፣ “በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን አስመልክቶ ሙሉ ስዕል የለኝም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ሌሎች የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡  በሰሞነኛ አበይት ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጠው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረ ገፅም ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር