12 ፓርቲዎች መጪውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ቅሬታዎቻቸውን በጋራ ለምርጫ ቦርድ አቀረቡ

በ2005 ዓ.ም በትብብር ሲሰሩ የቆዩ 12 ፓርቲዎች ከአሁን ቀደም የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታና አሁንም ከአሁን ቀደም የተነሱትን ጥያቄዎች የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተፈጸሙ በመሆኑ ከሀገራዊ ምርጫው በፊት ሊፈቱ ይገባቸዋል ያሏቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ምርጫ ቦርድም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በጋራ በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ፡፡
ፓርቲዎቹ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፉትና ዛሬ ለቦረወዱ ባስገቡት ደብዳቤ ላይ እንዳመለከቱት በመንግስት/ገዢው ፓርቲ በማንአለብኝነት የተወሰዱ ህገ-ወጥ እርምጃዎች ዘላቂ ልማትና ሠላም፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ፣ ህገ-መንግስታዊ፣ ሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በጋራ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል፡-
1ኛ/ በተለያየ የመዋቅር ደረጃ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማስፈራራት፣ የአካላዊና የንብረት ጉዳት ማድረስ፣ በሃሰት ውንጀላና የፈጠራ ክስ ማሰር፣ እየተጠናከረ መምጣትና በዚህም የፓርቲዎችን በዕቅዳቸው መሰረት የመሥራትና የዕለት ተዕለት ነጻ ህጋዊ እንቅስቃሴ መገደብ፤
2ኛ/ በአንድ በኩል የሠላማዊ ትግል ስልቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ በመዝጋት፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እዳይገናኙና ዓላማቸውን፣ ፕሮግራማቸውንና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለህዝብ እንዳያደርሱ በማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ ከምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በፊት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ መንግስታዊ መዋቅርና ሃብት በመጠቀም ለት ተለት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እየጠመቀ የምርጫ ቅስቀሳ ያደረገበትና እያደረገ ያለበት ሁኔታ ግልጽ መሆኑ፤
3ኛ/ ገዢው ፓርቲ ከመንግስት ካዝና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብሎ ያለምንም መስፈርት ለሚፈልጋቸው ፓርቲዎች በማከፋፈል በፓርቲዎች መካከል አላስፈላጊ የአቅም ልዩነት በፈጠረበትና የጥቅም ትስስር/ድጋፍ በገዛበት ሁኔታ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከተግባርና ኃላፊነቱ ውጪ ተሳታፊ መሆኑ፤
4ኛ/ ገዢው ፓርቲ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን በብቸኝነት በሚጠቀምበት እውነታ ለህዝብ አማራጭ መረጃዎችን የሚያቀርቡና በሥርዓቱ ላይ ትችቶች የሚያቀርቡ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንና አሳታሚዎችን በመክሰስ አንድም ለወህኒ ያሊያም ለስደት (በቅርብ ጊዜ ብቻ ከ10 በላይ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መታሰራቸውን፣ ከ20 በላይ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች መሰደዳቸውን ያጤኑኣል) በመዳረግ መራጩን ህዝብ ከአማራጭ መረጃ የማግኘት መብት ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ የተገደበበት፤
5ኛ/ በተለያዩ ቦታዎች በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ የሚታየው ግጭትና ይህን ተከትሎ የሚታየው የህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀልና ማኅበራዊ ምስቅልቅል አሳሳቢ መሆኑ በግልጽ የሚታይና በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለ እውነታ መሆኑ፤
የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ጥያቄዎች 2005 ዓ.ም ወቅት የቀረቡ ከነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ናቸው ያለው ትብብሩ ከ2005 ዓ.ም እስከ ዛሬ ያቀረብናቸው ጥያቄዎቻች እንዲመለሱ፣ ገዢውን ፓርቲና አጋሮቹን ጨምሮ ሁሉም ህጋዊ ፓርቲዎች በጋራ ተገናኝተው በምርጫና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚወያዩበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ ተጠይቋል፡፡
‹‹እነዚህ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት የሚደረግ የምርጫ ተሳትፎ ለኢ-ህገ-መንግስታዊነትና ኢ-ዴሞክራሲያዊነት ዕውቅና በመስጠት አገሪቷንና ህዝብን ወደባሰ አዘቅት መወርወር በመሆኑ በታሪክና ትውልድ ፊት የሚያስጠይቅ ነው›› ያለው የትብብሩ ደብዳቤ ምርጫ ቦርድ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠውና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሚዛናዊነቱን፣ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ በምርጫ ህጉ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሚሰራ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ጠይቋል፡፡
በትብብር እየሰሩ ያሉት ፓርቲዎች ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጸኃፊ የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ ‹‹በ2005 ለምርጫ ቦርድ ያነሳናቸውና ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ባልተመለሱበትና እንዲያውም ያነሳናቸውን ጥያቄዎች የበለጠ የሚያጠናክሩ ሁኔታዎች በተፈጠረበት፣ አንደኛ እነዚህን ጥያቄዎች መንግስት እንዲመልስ፣ ሁለተኛ ባነሳናቸው ጥያቄዎች ላይ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ውይይት እንድናደርግባቸው ነው ጥያቄዎቹን ያነሳናቸው›› በሚል ለምርጫ ቦርድ ያስገቡትን ደብዳቤ አላማ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ደብዳቤውን ካስገቡ በኋላ ምርጫ ቦርድ ‹‹የሚስተካከል ነገር አለውና ተመልሳችሁ እንደትመጡ›› ማለቱ የታወቀ ሲሆን አቶ ግርማ በበኩላቸው ‹‹ያቀረብነው አቤቱታ እንዲስተካከል አቤት ከተባለበት አካል አቤቱታውን እንድናስተካክል የሚመጣ ማስተካከያ መኖር የለበትም ብለን ገልጸንላቸዋል›› ብለዋል፡፡



ምንጭ፦ ዘሐበሻ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር