የመኖሪያ ቤቶች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መመርያ ለማሻሻል ረቂቅ ተዘጋጀ

•  በረቂቅ መመርያው መንግሥት ለማኅበራቱ መኖርያ ቤቶች አይገነባም
መንግሥት የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ለመቅረፍ ካቀረባቸው አራት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የሆነው የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መመርያ ሊሻሻል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ረቂቅ መመርያውን አዘጋጅቶ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ማቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
ለነዋሪዎች የቀረቡት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች ባለፈው ክረምት ምዝገባቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ቢገባም፣ በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፕሮግራም ግን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለመደረጉ ተመዝጋቢዎችን እያስጨነቀ ነው፡፡ መሰባሰብ የቻሉት ተመዝጋቢዎች በቅርብ ለከንቲባ ድሪባ ኩማ አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡ 
ከንቲባ ድሪባም ይህንን ጉዳይ በቅርብ መርምረው ምላሽ እንደሚሰጡ ለቅሬታ አቅራቢዎች ቢገልጹም፣ እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አለማግኘታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምዝገባ ከተካሄድ ከዓመት በኋላ ምንም ሥራ ያልተካሄደበት የመኖርያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መመርያ በድጋሚ እንዲከለስ የከንቲባው ጠረጴዛ ላይ ተቀምጧል፡፡ 
ምንጮች እንደሚገልጹት የተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ በተለይ ከግንባታና ከዳያስፖራ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ይደረጋሉ፡፡ በግንባታ በኩል ማሻሻያ የሚደረገው ከዚህ ቀደም አስተዳደሩ ባወጣው የመኖሪያ ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአደረጃጀት መመርያ ላይ ማኅበራቱ ስለሚገነቡት መኖሪያ ቤት ሲያትት፣ ማኅበራቱ ከከተማው አስተዳደር ጋር በሚገቡት የውል ስምምነት መሠረት መንግሥት ያቋቋመው የመኖሪያ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ግንባታውን ሊያካሂድ እንደሚችል ይገልጻል፡፡ 
መንግሥት ያቋቋመው የግንባታ ኢንተርፕራይዝ በመንግሥት ግንባታዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩር በመፈለጉ፣ ይህንን አንቀጽ ለማሻሻል ተፈልጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዳያስፖራን በሚመለከት ቀደም ሲል የነበረው አቅጣጫ ላይ ለውጥ ተደርጐበታል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው አቅጣጫ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ መኖሪያ ቤታቸውን እንዲገነቡ የሚያሳይ ነበር፡፡ 
አዲሱ አቅጣጫ የዳያስፖራ አባላት በፈለጉበት አካባቢ መኖሪያ ቤታቸውን እንዲገነቡ የሚፈቅድ በመሆኑ፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ዳያስፖራውን ለማስተናገድ የሚያስችል መመርያ እንዲያዘጋጅ ተወስኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ብሎ ባወጣው በመመርያ ቁጥር 4/2005 ከአዲሱ የመንግሥት አቅጣጫ ጋር እንዲጣጣም እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለካቢኔው የቀረበው ይህ ረቂቅ መመርያ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው የሚያስፈልገውን 50 በመቶ ክፍያ ፈጽመው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ነዋሪዎች፣ ፕሮግራሙ በወቅቱ ባለመጀመሩ ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም በዝግ ሒሳብ ያስቀመጡትን ገንዘብ ሌሎች ሥራዎችን ቢሠሩበት ትርፋማ ሊሆኑ የሚችሉ በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ገንዘብ ያለ ሥራ ታስሮ የሚገኝ ስለሆነ፣ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተመዝጋቢዎቹ እየጠየቁ ነው፡፡ 
ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር