ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅም እንዳላት ተገለጸ

አዲስ አበባ መስከረም 2/2007 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅሙ እንዳላትና የትኛውንም አይነት መሰል ኃላፊነት ቢሰጣት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን /ካፍ/ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ በበኩላቸው አስፈላጊን ቅደመ ሁኔታ ካሟላች ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በካፍ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኢሳ ሃያቱ የተመራ የልኡካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይቷል።
በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የስፖርት ኢንዱስትሪ ለማገዝና ለማጠናከር ከኮንፌደሬሽኑ ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተነጋግረዋል።
ከውይይቱ በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴዎች ጀምራለች።
ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ስፖርት ትልቅ ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም ይህ ለረጅም ጊዜ ተቀዛቅዞ ቆይቷል ያሉት አቶ ደመቀ አሁን እየታየ ያለው መነቃቃት የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ኮንፌደሬሽኑ ይህንን ተነሳሽነትና መነቃቃት በሚደገፍባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም አገሪቱ በተለያዩ መድረኮች ያላትን ውክልና በማስፋት ዙሪያም ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ እንደገለጹት "በውይይቱ ኮንፌደሬሽኑ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያለውን የስልጠና ማእከልና ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድኑን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል"።
የካፍ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኢሳ ሃያቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ፍላጎት እስካላትና ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟላች ድረስ ካፍ ሃላፊነቱን ቢሰጣት ደስተኛ እንደሆኑ ነው የተናገሩት።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በኢትዮጵያ በተለይ በታዳጊዎች እና ወጣቶች ላይ ያለውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለማሳደግ በሚረዳዱባቸው ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸውንም ገልጸዋል።
መንግስት ይህን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ ኮንፌደሬሽኑም በሚችለው ሁሉ ይህን ያግዛል፣ ያበረታታልም ብለዋል።
ካፍ በየሁለት ዓመቱ የሚደረገውን የኮንፌደሬሽኑ አመታዊ የስራ አስፈጻሚና የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ያካሂዳል።
"ይህን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ የተመረጠችው እግር ኳሷን ለማሳደግ ትልቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያለች አገር በመሆኗ ነው" ሲሉ ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ።
ሊቢያ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫን እንደማታዘጋጅ ከታወቀ በኋላ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ጋና የማዘጋጀት እድሉ ይሰጣቸው ዘንድ ለካፍ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ናቸው።
ምንጭ፦ ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር