በቡና ዘርፍ ማሻሻያ ሳይደረግ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ታቀደ

• ንግድ ሚኒስትር ሕገወጥ የቡና ንግድ ለመግታት ከነጋዴዎች ጋር መወያየት ጀመረ    የቡና ላኪዎች ማኅበር የመፍትሔ ሐሳቦችን አቀረበ
በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ የማሻሻያ ዕርምጃ ሳይወሰድ በ2007 በጀት ዓመት ከዘርፉ 900 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቀደ፡፡
የንግድ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 235,000 ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 900 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራው ብሔራዊ የኤክስፖርት ምክር ቤት ማፅደቁ ታውቋል፡፡
ይኼንን ዕቅድ ለማሳካት ንግድ ሚኒስቴር በቅርቡ ዋነኛ ከሚላቸው 195 ቡና ላኪዎች ጋር ለመምከር እንደተዘጋጀ የሚናገሩት ምንጮች፣ ሚኒስቴሩ በቡና የወጪ ንግድ ዘርፍ ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች እስካልፈታ ድረስ በታቀደው ዕቅድ ስኬት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው እየገለጹ ነው፡፡
‹‹በሕገወጥ ነጋዴዎች ምክንያት ሥራችን ለማካሄድ ተቸግረናል፤›› የሚሉ ቡና ላኪዎች ባይቀበሉትም፣ ንግድ ሚኒስቴር ሕገወጥ የቡና ንግድን ለማስቀረት ያስችላል ያለውን ሥራ ጀምሯል፡፡ ሚኒስቴሩ ደረስኩበት ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በኤክስፖርት ደረጃ የተዘጋጀ ቡና በየሱፐር ማርኬቱና በየገበያው በብዛት ይገኛል፡፡ የዚህ ቡና ምንጩ አዲስ አበባ ውስጥ መፈልፈያ ጣቢያ ካላቸው ነጋዴዎች እንደሆነ የሚያስረዳው የሚኒስቴሩ መረጃ፣ እነዚህን ነጋዴዎች ማወያየት ያስፈልጋል የሚል ዕምነት እንዳሳደረ አመልክቷል፡፡
በዚህ መሠረት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የቡና መፈልፈያ ባለቤቶች ሚኒስቴሩ አንድ በአንድ እየጠራ በማነጋገር ላይ እንደሚገኝም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ሕጋዊ ነኝ የሚሉ ነጋዴዎች በዚህ የሚኒስቴር ተግባር ዕምነት እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸውን በሕገወጥ የቡና ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሚታወቁ መሆናቸውና ሚኒስቴሩም በቂ መረጃ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በየስብሰባውም ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ በመሆኑም ወደ ዕርምጃ እስካልተገባ ድረስ የሚመጣ ለውጥ እንደማይኖርም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በ2006 ዓ.ም. የቡና የወጪ ንግድ ደካማ የሥራ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የ2006 ዓ.ም. የአሥር ወራት አፈጻጸም፣ በአሥር ወራት ውስጥ 207,000 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 822 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን የተላከው ቡና 136,000 ሜትሪክ ቶን እንደሆነና የተገኘው ገቢም 489 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅም አጠቃላይ በቡና ዘርፍ የተያዘው ዕቅድ እንዳልተሳካ ተገልጿል፡፡
አቶ ከበደ ዕቅዱ ያልተሳካበትን ምክንያት ሲገልጹ የሚፈለገውን መጠን ያህል ቡና ለገበያ አለመቅረቡ፣ የዓለም የቡና ገበያ በዋጋ መዋዥቁ፣ በየደረጃው ያለው ፈጻሚ በቅንጅት ሊሠራ ባለመቻሉ፣ የኤክፖርት ቡና በሕገወጥ መንገድ በአገር ውስጥ መሸጡ፣ ወደ ጎረቤት አገሮችም እንዲወጣ መደረጉና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል በቂ ጥረት አለመደረጉን በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ይህ ነው የሚባል ሥራ ሳይሠራ በተያዘው በጀት ዓመት ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቡና ላኪዎች አልተቀበሉትም፡፡
በዘርፉ በተለይ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስ በመሆኑና የቡና ንግድ ረዥም የንግድ ሰንሰለት ያለው በመሆኑ፣ ለሙስና ተጋላጭ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ይኼንን ተጋላጭነት ለመከላከል የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ቁርጠኛ ባለመሆናቸው፣ ዘርፉ በችግር ውስጥ እንደሚገኝም ያስረዳሉ፡፡
ይህ ሁኔታ በዓለም ደረጃ ተወዳጅ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ እንዲያጣ ከማድረጉም በላይ፣ በሕጋዊ መንገድ በዘርፉ የሚሠሩ ነጋዴዎችን ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ሥራ አመራር ቦርድ በቡና ግብይት ላይ ስብሰባ አካሂዶ እንደነበር የሚጠቅሱት ምንጮች፣ በዚህ ስብሰባ በ2007 ዓ.ም. የብራዚል ሁሉም ዓይነት ቡና በድርቅና በውርጭ በመመታቱና  የቡና ዛፎች እየተገረዙ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ቡናን በዓለም አቀፍ ገበያ አሸናፊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን እንዳሰመረበት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን እጥረት ሊሞላ የሚችል አገር ባለመኖሩ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ቡና ክፍተት እንዳለም አመልክተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ክፍተት ስለሚፈጥር ዋጋ ያነሳል በማለት ቦርዱ በመልካም አጋጣሚ እንደተቀበለውም ጠቅሰዋል፡፡
ቦርዱ በአገር ውስጥ ያሉ የቡና አቅርቦት ምርት ገበያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ከቡና ግዢና ከሎጂስቲክስ አንፃር እንደ ሥጋት አስቀምጧቸዋል፡፡ ቦርዱ መፍትሔ ያላቸውን ጉዳዮች ለመንግሥት እንዲቀርቡ መስማማቱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን መንግሥት ቀደም ብሎ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመረዳት የማሻሻያ ዕርምጃዎችን እስካልወሰደ ድረስ ዕድሉን መጠቀም አስቸጋሪ እንደሚሆን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡ 
Source:http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/7399-%E1%89%A0%E1%89%A1%E1%8A%93-%E1%8B%98%E1%88%AD%E1%8D%8D-%E1%88%9B%E1%88%BB%E1%88%BB%E1%8B%AB-%E1%88%B3%E1%8B%AD%E1%8B%B0%E1%88%A8%E1%8C%8D-%E1%8A%A8%E1%8D%8D%E1%89%B0%E1%8A%9B-%E1%8C%88%E1%89%A2-%E1%88%88%E1%88%9B%E1%8C%8D%E1%8A%98%E1%89%B5-%E1%89%B3%E1%89%80%E1%8B%B0

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር