ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን እየሆኑ ነው?

ምርጫ 2007 ዘጠኝ ወራት ያህል እየቀሩት ነው፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን የሚያዘጋጁበት፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለመጀመር የቤት ሥራቸውን የሚያጠናቅቁበትና ምርጫው ምርጫ እንዲመስል የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት ነው፡፡
አሁን እያየን ያለነው ግን ይህንን ምሥል ሳይሆን ተቃራኒውን ነው፡፡ የምርጫ ሸብ ረብ ሳይሆን በትንሽ በትልቁ እርስ በርስ መናቆር ነው፡፡
በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ አለን የሚሉት ስማቸው ጎላ ብሎ የሚታይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሽኩቻ ውስጥ ናቸው፡፡ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ለዓመታት የከረሙበት መናቆር እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ደግሞ ወደ ውስጥ ግብግብ ገብተዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መጠናከር ሳይሆን መፍረክረክ እየታየ ነው፡፡ ምርጫ ዋዜማ ላይ ሆኖ ይህንን ትርምስ የሚታዘቡ ደጋፊዎችም ሆኑ አባላት ተስፋ እየቆረጡ ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ትግሉንም ሊሸሹ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አይበጅም፡፡
ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚደረግ ሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አስፈላጊ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚያብበው መራጩ ሕዝብ የተለያዩ አማራጮች ያሉዋቸውን ፓርቲዎች ማግኘት ሲችል ነው፡፡ አማራጭ ሲባል ለይስሙላ የሚነገር በጥናት ላይ ያልተመሠረተ ስንክሳር ሳይሆን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተደራጁ ፕሮግራሞችን ይዞ መቅረብ ነው፡፡ አሁን የምናየው ይህንን አይገልጽም፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ለእንቅስቃሴዎቻቸው መገደብ ሁለት ዓበይት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ውጪያዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ውስጣዊ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ውጫዊው ምክንያት በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ የሚገለጽ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማጥበብ አንስቶ በርካታ ምክንያቶች የሚቀርቡበት ተፅዕኖ ብዙ የተባለበት በመሆኑ፣ አሁን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ችግሮች ላይ እናተኩራለን፡፡ በውስጡ ጥንካሬ የሌለው የውጭውን መመከት አይችልምና፡፡
በቅርቡ አንድነት ፓርቲና መኢአድ የመዋሀድ አጀንዳ ይዘው እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፣ ውህደቱ ይሳካል ወይ የሚሉ ጥርጣሬዎች ነበሩ፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለውህደቱ መሳካት መሟላት አለባቸው ካላቸው ጉዳዮች መካከል የምልዓተ ጉባዔ አለመሟላት ሳንካ ሆኗል፡፡ ይህ በተሰማ ሰሞን አምስት የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባለመግባባታቸው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡
መኢአድ በምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ጥያቄ ለመመለስ ላይ ታች በሚልበት ወቅት ሕግና ደንብ አልተከበረም ያሉ አባላት ተነስተዋል፡፡ መኢአድ ውስጥ ከሦስት ዓመታት በፊት ተጀምሮ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው መከፋፈል እንኳን ለውህደቱ ለድርጅቱም አደጋ ሆኗል፡፡ የውስጥ ችግሮች ቢዳፈኑም እየቆዩ ማመርቀዛቸው እየታየ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ምክትል ፕሬዚዳንቱን ማገዱ ተሰምቷል፡፡ በፕሬዚዳንቱና በምክትሉ መካከል ተከስቷል የተባለው አለመግባባት አደባባይ ወጥቶ ደግና ክፉ አናግሯል፡፡ በተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም ውስጥ ለውስጥ የሚካሄዱ ሽኩቻዎች አሉ፡፡ በአንድ ወቅት ከሰማያዊ ፓርቲ የወጡ ግለሰቦች ውስጣዊ ትግሉ እንደሚቀጥል መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ምርጫው የወራት ዕድሜ እየቀሩት ነው፡፡
የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የመጨረሻ ግብ ሥልጣን መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ ትግል ሥልጣን የሚገኘው መራጩ ሕዝብ በሚሰጠው ድምፅ ነው፡፡ መራጩን ሕዝብ በመቅረብ አማራጮቹን በሚገባ አሳውቆ ለውድድር የማይቀርብ ፓርቲ ህልውና ትርጉም የለውም፡፡ በተቃዋሚው ጎራ የሚታየው ደግሞ ከመጠናከር ይልቅ መፍረክረክ፣ ከመዋሀድ ይልቅ መለያየት መሆኑ የአገሪቱን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ እየፈረካከሰው ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ ላይ የሚቀርቡት ስሞታዎች ድክመትን መሸፋፈኛ እየመሰሉ ናቸው፡፡ የመራጩን ሕዝብ አመኔታም እያሳጡ ናቸው፡፡
የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረቶች ከሆኑት መካከል ምርጫ አንዱ ነው፡፡ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ ሆኖ ተመጣጣኝ ውክልና ያለበት ጠንካራ ፓርላማ እንዲኖር ከተፈለገ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ፈትሸውና ገምግመው መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከውስጣዊ ችግሮቻቸው ሳይላቀቁ ለሥልጣን የሚያደርጉት ትርምስ መሳቂያና መሳለቂያ ያደርጋቸዋል፡፡ የራሳቸውን ችግር ሳይፈቱ ገዥው ፓርቲ ላይ ቢያፈጡ ለትዝብት ይዳረጋሉ፡፡
በአንድነት ፓርቲም ሆነ በመኢአድ ውስጥ በተቃራኒ ጎራ የተሠለፉ ኃይሎች የድርጅት ሥልጣን ለመቆጣጠር ያሰፈሰፉ ይመስላሉ፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚታየው ግብግብም ይህንን ያጠናክራል፡፡ በፓርቲ ውስጣዊ ዲሞክራሲ ያልተፈታ ቅራኔ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተግለበለበ ሲሄድ የፓርቲዎችን ህልውና ይፈታተናል፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹መርህ ይከበር›› በሚል የአንድነት ፓርቲ አባላት በፈጠሩት አምባጓሮ የደረሰው ቀውስ አይዘነጋም፡፡ ሰሞኑን በመኢአድ ተቃራኒ ጎራዎች መካከል የሚሰማው ኃይለ ቃል ወደ ትርምስ ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ በምርጫ ዋዜማ ነው፡፡
መራጩ ሕዝብ በሚቀጥለው ምርጫ የተለያዩ ፓርቲዎች አማራጮችን ይዘው እንዲቀርቡለት ይፈልጋል፡፡ በምርጫ ሥልጣን ላይ በሚወጣበት በየትኛውም አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳና ክርክር ይጠበቃል፡፡ ራሱን ለሰላማዊ ፉክክር የማያዘጋጅ ፓርቲ የሕዝብ ድምፅ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን ሊከስም ይችላል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ ሽኩቻ ለህልውናቸው አደጋ እየደቀነ ነው፡፡ ይህንን ችግር ካልፈቱ ስለመድበለ ፓርቲም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የመሟገት ሞራል እንዴት ይኖራቸዋል? ፓርላማው በገዥው ፓርቲና በአጋሮቹ ተሞላ እያሉስ እስከ መቼ ይዘልቃሉ? ይህ መመለስ ያለበት መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
ላለፉት 23 ዓመታት የዘለቀው የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሽኩቻ ወደ እውነተኛ የምርጫ ፉክክር መለወጥ ካልቻለ ስለዲሞክራሲ መናገር ይከብዳል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረጉ የሥልጣን ሽኩቻዎች ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አይጠቅሙም፡፡ የሕዝብ አመኔታና ክብር የሚገኘው ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎች ሲከናወኑ ነው፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ይክፋም ይልማም ለምርጫ ራስን ማዘጋጀት አንዱ ነው፡፡ አሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን እየሆኑ ነው? ማለት የወቅቱ ዓቢይ ጥያቄ ነው፡፡
_____________________________________________________
We welcome comments that advance the story through relevant opinion and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers. 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር