ብሮድካስት ባለሥልጣን ደቡብ ክልል የራሱን የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲጀምር ፈቃድ አልሰጠሁም አለ

ዜናው የhttp://www.ethiopianreporter.com ነው

-ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶበታል 
-ብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ አልሰጠሁም አለ
ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በመቋቋም ሒደት ላይ የነበረው የደቡብ ክልል ቲቪ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሥራውን አጠናቆ ነሐሴ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ከተመረቀ በኋላ፣ በቀን የአሥር ሰዓት ሥርጭት እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡ 

የደቡብ ክልል ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ቱሬ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ በኢቲቪ በቀን ለአንድ ሰዓት ይተላለፍ የነበረው የክልሉ መንግሥት የቲቪ ፕሮግራም በክልሉ የሚኖሩትን በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ ኑሮ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በላቀ ሁኔታ ለመግለጽ በቂ እንዳልሆነ በመታመኑ፣ ጣቢያውን የማቋቋም ሥራው በፕሮፖዛል መልክ በ2004 ዓ.ም. ከተሠራ በኋላ በ2005 ዓ.ም. የክልሉ መንግሥት አፅድቆት ነው የማቋቋሙ ሒደት የተጀመረው፡፡ 

በማቋቋም ሒደቱ ስቱዲዮ በመገንባት፣ የመሣሪያዎች ግዥ በመፈጸምና ሠራተኞችን በመቅጠር ያለፉትን ሁለት ዓመታት እንዳለፉ የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፣ ጣቢያውን ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማስጀመር ከሚያስፈልጉ ሠራተኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑ 110 ሠራተኞችን መቀጠራቸውን አመልክተዋል፡፡ 

ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ከዚህ በፊት ለሕዝብ እይታ ያልቀረቡ ርዕሰ ጉዳዮችን በማቅረብ የክልሉ ነዋሪዎችን ለማስተማርና ለማዝናናት ጣቢያው ቁልፍ መሆኑን አቶ ዮሐንስ አስረድተው፣ በመረጃ ነፃነት ሕጉ አማካይነት የክልሉ ነዋሪዎችና ሌሎች ተመልካቾች ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ጣቢያው እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ በቀን 18 ሰዓት በ47 ቋንቋዎች እየሠራ የሚገኘው የደቡብ ሬዲዮ ለደቡብ ቲቪ ጠቃሚ ተሞክሮ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ ግን፣ ባለሥልጣኑ የቴሌቪዥን ሥርጭት ፈቃድ ከሰጣቸው ክልሎች መካከል የደቡብ ክልል እንደማይገኝ አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን ፈቃድ የወሰዱት ክልሎች ኦሮሚያ፣ ሐረሪና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮችም እንዲሁ ፈቃድ አግኝተዋል ብለዋል፡፡ ከደቡብ ክልል በተጨማሪ የአማራ ክልል በቅርቡ የጣቢያውን ስቱዲዮ ያስመረቀ ሲሆን፣ ትግራይ ክልልም የስቱዲዮ ግንባታውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ 

አቶ ወርቅነህ ብሮድካስት ባለሥልጣን አዲስ ፈቃድ ለመስጠት የቴሌቪዥን አሠራርን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለመቀየር የሚደረገው ሥራ መጠናቀቁን መጠበቅ ግድ እንደሚሆንበት የጠቆሙ ሲሆን፣ ሒደቱ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ወይም በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ 

በብሮድካስቲንግ አዋጁ የግል ቴሌቪዥን የተፈቀደ ቢሆንም፣ እስካሁን በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤትነት ከመንግሥት አልወጣም፡፡ በቅርቡ ለግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ያልተሰጠው ጣቢያዎቹ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት በመፍራት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
_______________________________________________________________

We welcome comments that advance the story through relevant opinion, anecdotes, links and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers.

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር