የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስገዳጅ ሥልጠና እየወሰዱ ነው


በሁለት ዙር ለሚደረግ ሥልጠና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመንግሥት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራሞች ዙርያ ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ሥልጠናውን የማይሳተፉ ተማሪዎች ለቀጣዩ ዓመት ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት መመዝገብ እንደማይችሉም ታውቋል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተመደቡበት ጣቢያ ለ15 ቀን ያህል በሁለት ዙር የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የፕሮግራም ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር በመማር ማስተማር ሒደቱ ስለሚከሰቱ ተግዳሮቶች፣ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ስለሚያስችሉ ሁኔታዎችና የመልካም ዜጋ ባህሪያት ላይ ጥልቅ ውይይቶች እንደሚደረጉ፣ የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በየዓመቱ መጀመርያ ላይ ካለፈው ዓመት የመማር ማስተማር ሒደት ግምገማ ማድረግ የተለመደ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደሳለኝ፣ የትምህርት ጊዜን ላለመሻማትና በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የተነሳ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ጊዜ የተለያየ በመሆኑ በክረምቱ ወቅት ሥልጠናውን ለመስጠት እንደመረጡም አመልክተዋል፡፡
በሥልጠናው ላይ ተካፋይ የሆኑ ተማሪዎች ሥልጠናው አስገዳጅ በመሆኑ ነፃነታቸውን የሚጋፋ መሆኑን ለሪፖርተር መግለጻቸውን አስመልክቶ የተጠየቁት አቶ ደሳለኝ፣ ሥልጠናው የትምህርታቸው አንድ አካል በመሆኑ መሠልጠን የማይፈልጉበት ምክንያት እንደማይታያቸው ገልጸዋል፡፡ ሥልጠና ለማይካፈሉ መመዝገብ የተከለከለ ስለመሆኑም የተወሰነው በትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡
በሥልጠናው ላይ ከ250,000 በላይ የሁለተኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ተማሪዎች፣ እንዲሁም ከ116,000 በላይ አዳዲስ ተማሪዎች እንደሚሳተፉ የተጠቆመ ሲሆን፣ ሥልጠናው በትምህርት ሚኒስቴርና በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በጋራ መዘጋጅቱም ተገልጿል፡፡
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሥልጠናው በሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች፣ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና በኢትዮጵያ ህዳሴ ላይ እንደሚመክር የዘገቡ ሲሆን፣ ሌሎች ሚዲያዎች ሥልጠናው በመጪው ዓመት ከሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዓመፅ እንዳይቀሰቅሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት አቶ ደሳለኝ ግን በቅርብ ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎች ምንም ዓይነት ኮሽታ አለመሰማቱን ጠቁመው፣ ሥልጠናው በአጠቃላዩ የመማር ማስተማር ሒደት ላይ ከመምከርና የመንግሥት አሠራሮችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ከምርጫ 2007 ጋር የሚያገናኘው ምንም እንደሌለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ 
_____________________________________________________
We welcome comments that advance the story through relevant opinion and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers. 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር