መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሳይስማሙ ተለያዩ

‹‹ዲሞክራሲ እንደ ጃኬት ከአውሮፓ ተሰፍቶ አይመጣም››
መንግሥት
የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ሲመክሩ፣ በአገሪቱ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ግምገማ ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡ 
ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት በጽሕፈት ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በኢኮኖሚያዊ ልማት፣ በዕርዳታ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ምክክር አድርገዋል፡፡ 
የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የኢኮኖሚ ዕርዳታ ከፍተኛውን መጠን የሚይዝ መሆኑ የተናገሩት አምባሳደር ዲና፣ አገሪቷ ውስጥ ባለው የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ግን ሳይስማሙ መለያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በእስር ላይ ስለሚገኙት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች አስመልክቶ ውይይት ስለመደረጉም ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ከሰብዓዊ መብትና ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ተያይዞ የታሳሪዎች ጉዳይ መነሳቱን ገልጸው፣ ‹‹በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞች የታሰሩት ጋዜጠኞች በመሆናቸው አይደለም፤›› የሚለው የመንግሥት አቋም በአውሮፓ ኅብረት ተቀባይነት አለማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ችግር በማናቸውም የዲሞክራሲ ሒደት ውስጥ የሚያጋጥም እንጂ፣ ‹‹ሲስተሚክ›› አይደለም የሚለው የመንግሥት አቋም ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ግን መንግሥት በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና በጋዜጠኞች ላይ በሚወስደው ዕርምጃ ደስተኛ አይደለም፡፡
አምባሳደር ዲና መንግሥት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በአካባቢ ፀጥታ፣ በኢኮኖሚ ግንኙነትና በኢንቨስትመንት በትብብር ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው፣ በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ግን መስማማት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
ከአውሮፓ ኅብረት የቀረበው ትችት በመንግሥት ተቀባይነት እንደሌለው ለማስረዳትም፣ ‹‹ዲሞክራሲ በአገር ውስጥ የሚበቅል እንጂ በማንም ተፅዕኖ እንደ ጃኬት ተሰፍቶ ከአውሮፓ የሚወጣ አይደለም፤›› በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር