ሁለተኛው ቱር መለስ የአረንጓዴ ልማት የብስክሌት ውድድር በሀዋሳ ከተማ

ሃዋሳ ነሐሴ 14/2006 በሀዋሳ ከተማ ዛሬ የተጀመረው ሁለተኛው ቱር መለስ የአረንጓዴ ልማት የብስክሌት ውድድር በደቡብና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 11 ከተሞች ከቀጠለ በኋላ ነሀሴ 27 ፍጻሜውን በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡
በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የ80 ኪሎ ሜትር ውድድር ከትግራይ ክልል የጉና፣ ትራንስ ኢትዮጵያና መሰቦ ክለብ ብስክሌተኞች አሸናፊ በመሆን የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዶች ተቀብለዋል።
በስፖርታዊ ውድድሮች ሀገሪቱ ውጤታማ መሆን እንድትችል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በቱር መለስ አረንጓዴ ልማት የብስክሌት ውድድር ላይ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች አስታውቀዋል፡፡
በሁለተኛው የቱር መለስ አረንጓዴ ልማት የብስክሌት ውድድር ላይ ከተሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካከል የሜታ አቦ ፣የመቀሌ ብሩህ ተስፋና የድሬደዋ ከነማ ተወዳዳሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በልማቱ መስክ ያስመዘገበችው ድል በስፖርቱ መድገም እንድትችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
የሜታ አቦን ክለብ የወከለው ተወዳዳሪ በርይሁን መርሶ እንዳለው መለስ ስፖርትን የልማት አንዱ አካል በማድረግ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሀገራችን በየውድድሩ የምታመጣው ውጤት ከፍተኛ መሻሻል እየታየበት ነው፡፡
የመቀሌ ብሩህ ተስፋ ክለብ ተወዳዳሪ ቴዎድሮስ ሀብቱና የድሬደዋ ከነማ ተወዳዳሪ ብሩክ አለማየሁ እንዳሉት መለስ ሀገሪቱ በልማት መስክ ብቻ ሳይሆን በስፖርቱም የቀድሞ የበላይነቷ እንዲረጋገጥና እየተመዘገበ ላለው ውጤት መሰረት የጣሉ ጀግና መሪ ናቸው፡፡
በመለስ የተጀመሩ የልማት የመልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከብስክሌት ውድድሩ ጎን ለጎን በሀዋሳ ፣በወላይታ ሶዶ፣ በሆሳዕና ፣በአሰላና አዲስ አበባ ከተሞች ተወዳዳሪዎችና የከተሞቹን ነዋሪዎች ተሳታፊ የሚያደርግ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በመዘጋጀቱ ትናንት በሀዋሳ ታቦር ተራራ ላይ የችግኝ ተከላ ስነስርዓት ተካሂዷል፡፡
በሁለተኛው ዙር ቱር መለስ ለአረንጓዴ ልማት የብስክሌት ውድድር ከትግራይ ፣ከአማራ ፣ኦሮሚያ፣ደቡብ ክልል፣ከድሬደዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ 13 ክለቦችን የሚወክሉ ከ90 የሚበልጡ ተወዳዳሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ባለፈው አመት ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ የተካሄደውን ቱር መለስ የብስክሌት ውድድር የአፍሪካና አውሮፓ ታላላቅ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት አለም አቀፍ የቱር ውድድር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዲያሬክተር አቶ መሳይ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡
መነሻውን ሀዋሳ ከተማ በማድረግ ዛሬ 80 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ጎዳና ላይ የተጀመረው የብስክሌት ውድድር በደቡብና ኦሮሚያ ክልል ሀላባ፣ ወላይታ ሶዶ፣ሆሳዕና ፣ቡታጅራ ፣ዝዋይ ፣ሻሸመኔ ፣በቆጂና አዳማ ከተሞችን በማካተት 893 ኪሎ ሜትሩ ፍጻሜ የሚያገኘው ነሀሴ 27 ቀን 2006 በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የ80 ኪሎ ሜትር ውድድር የትግራይ ክልል የወከሉት ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ ከጉና ፣ሀይላይ ብርሀነ ከትራንስ ኢትዮጵያና ልሳን ጌታቸው ከመሰቦ ስፖርት ክለብ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት የክብር ጀርሲ ተሸላሚ ሲሆኑ ትራንስ ኢትዮጵያ የቡድን አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ሽልማት አግኝቷል፡፡
ባለፈው አመት በተካሄደው የመጀመሪያው ቱር መለስ የብስክሌት ውድድር ጉና ፣ትራንስ ኢትዮጵያና መሰቦ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው፡፡
http://www.ena.gov.et/index.php?option=com_k2&view=itemlist&layout=category&task=category&id=22&Itemid=252&lang=am

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር