በአገራችን ያልቀረው ሕፃናትን የመቅጣት ‹‹መብት››

በቤተሰብና በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሕፃናትን ጠባይ ለማረም የሚወስዱ የቅጣት ዕርምጃዎች በየወቅቱ አነጋጋሪ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ሕፃናት ካልተቀጡ፣ ካልታረሙ፣ ካልተገሰጹ ጥሩ ሥነ ምግባር አይኖራቸውም፤ ባህላችንም፣
ሃይማኖታችንም ሕፃናት እንዲቀጡና መልካም ጠባይ ኖሮአቸው እንዲያድጉ ያስተምራሉ የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ ይህንን አቋም የማይቀበሉት ሌሎቹ ደግሞ ሕፃናትን በማስተማር፣ በመንገር፣ በትዕግስት ቀርቦ በማስረዳት ካልሆነ መቅጣት አያስተምራቸውም፣ አያርማቸውም፤ እንዲያውም የሥነ ልቦና ጫና በማሳደር እንዲፈሩ፣ እንዲጨነቁና ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ያደርጋል በሚል የተቃውሞ ክርክራቸውን ያሰማሉ፡፡ ከተወሰኑ ዘመናት በኋላ ደግሞ ሕፃናትን ጠባይ ለማረምም ቢሆን መቅጣት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ያም ሆኖ ሕፃናትን መቅጣት አሁንም በብዙ አገሮች ሕጋዊ የሆነ ተግባር ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል፡፡ 
ከሕፃናት መብት አንፃር አገራችን በዚህ ዘመን ከትናንቱ የተሻለ ቢሆንም ሕፃናት መቀጣታቸው፣ መቆንጠጣቸው፣ በእጅ ወይም በዱላ መመታታቸው የቀረ አይመስልም፡፡ በቀደሙት ዘመናት በቤት ውስጥ ያጠፋ ሕፃንን መግረፍ፣ በበርበሬ ማጠን፣ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ መንከር፤ በትምህርት ቤትም ለረጅም ሰዓታት እንዲንበረከክ ማድረግ፣ በክፍል አለቃና በመምህር በትር መገረፍ፣ አጎንብሶና ተገልብጦ ጆሮን መያዝ የተለመዱ እንደነበሩ ብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስታውሰው ሃቅ ነበር፡፡ አሁን ለውጡ አገራችን ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር ባመጣችው የባህል ለውጥ ይሁን በዘመናዊነት ወይም በዘመነ ሉላዊነት (Globalization) ተፅዕኖ ሕፃናት እንደ ድሮው ዓይነት ለከፋ ቅጣቶች አይጋለጡም፡፡ አሁንም ቢሆን ግን መቀጣት፣ መገረፍና መቆንጠጥ አልቀረላቸውም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን አልፎ አልፎ እንደምንሰማው አንዳንድ ወላጆች ስሜታዊ በመሆን ልጆቻቸውን በመቅጣታቸው ሕፃናቱን ለአካል ጉዳት ሲከፋም ለሞት ያደረሱ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ጸሐፊው በአንድ ወቅት በሬዲዮ የሰማው አሳዛኝ ታሪክ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ አባት ሦስት ብር ከኪሱ የሰረቀበትን አካለ መጠን ያልደረሰ ልጁን በስሜታዊነት ሲደበድብ ዋለ፤ ልጁም በድብደባው ብዛት ሕይወቱ አለፈ፤ አባትም ዘብጥያ ተወረወረ፡፡ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ወይም አስተማሪ ልጁን ወይም ተማሪውን ሲቀጣ ሕፃኑን ለማረም በጠባይ ለማስተካከል እንደሆነ ቢታመንም አልፎ አለፎ ቅጣቱ በሕፃኑ አካልና ሥነ ልቦና ላይ ያለውን ውጤት ስናስተውል የቅጣቱ ዓላማ እንደማይሳካ እንረዳለን፡፡ ሕፃናትን መቅጣት ‹‹መብት›› ነውን? ሰውን መምታት፣ መግረፍና መንካት በሕግ ያልተገባ ወይም የማይፈቀድ ድርጊት ሆኖ ሕፃናት እንዲቀጡ መፍቀድ ፍትኃዊነቱ ከወዴት አለ? የአገራችንን ሕግጋት መሠረት አድርገን ሕፃናትን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆች ወይም አሳዳሪዎች ወይም አስተማሪዎች ሕፃናትን የመቅጣት መብት ያላቸው መሆኑን አለመሆኑንና በሕጉ የተቀመጡ የተለያዩ ገደቦችን በአጭሩ ለመመልከት እንሞክር፡፡ 
በአካል ላይ የሚፈጸም ቅጣት (Corporal Punishment)
የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን የሚከታተለው በተባበሩት መንግሥታት የተቋቁመው ኮሚቴ ከአካል ላይ የሚፈጸም ቅጣት ማለት በእጅ ወይም በሌላ ግዑዝ ነገር የሕፃናት ሰውነትን በመምታት፣ በመቀጥቀጥ፣ በመወርወር ቀላል የአካል ጉዳትም ቢሆን ጉዳት ማድረስ ነው፡፡ “Corporal Punishment refers to any punishment in which physical force is used & intended to cause some degree of pain or discomfort, however, light, including hitting (smacking, slapping, spanking) children” ሲል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ 
የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን በአንቀጽ 19 ፈራሚ አገሮች ሕፃናት በቤት ውስጥ በወላጆቻቸው፣ በአሳዳሪያቸው ወይም እነሱን ለመንከባከብ ሥልጣን ባለው አካል ማንኛውም ዓይነት የአካልና የአዕምሮ ጥቃት እንዳይደርስባቸው የመጠበቅ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ 
በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሕፃናትን በማንኛውም ዓይነት ምክንያት መቅጣት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ የኮንቬንሽኑን አፈጻጸም የሚከታተለው ኮሚቴው እ.ኤ.አ. በ2006 ባወጣው ማብራሪያ ሕፃናትን ለማረምና ጠባይ ለማስተካከል በሚል መቅጣት ወይም መምታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን አስምሮበታል፡፡ ከትምህርት መብትም ጋር በተያያዘ በተሰጠ ሌላ የኮሚቴ አስተያየት ሕፃናትን መቅጣት በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለውና የሚከለከል መሆኑን ገልጿል፡፡ አገራችን የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን የፈረመችና ያፀደቀች በመሆኑ ሕፃናትን መቅጣት የሚፈቅድ ሕግ፣ ልማድ ወይም አሠራር እንዳይኖር የማድረግ ግዴታ ተጥሎባታል፡፡
የአገራችን ሕግጋት
የተለያዩ የአገራችን ሕግጋት የሕፃናት መቀጣትን የተመለከተ ድንጋጌዎች አሏቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ፣ የወንጀል ሕጉና የተሻሻሉት የቤተሰብ ሕግጋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መሠረታዊ መርሁ የሚገኘው ሕገ መንግሥቱ ላይ ሲሆን ሕገ መንግሥቱ የሕፃናትን መቀጣት በመርህ ደረጃ የሚከላከል ቢመስልም የሚፈቅድበት ሁኔታ መኖሩን ካስቀመጠው ድንጋጌ መረዳት እንችላለን፡፡ የሕፃናትን መብት የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36(1)(ሠ) ማንኛውም ሕፃን ‹‹በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢ ሰብዓዊ ቅጣት ነፃ የመሆን መብት አለው፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሕፃናት በአካላቸው ላይ ከሚፈጸም ቅጣት ነፃ የሚሆኑት በትምህርት ቤቶችና በማሳደጊያ ተቋማት ብቻ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ብዙ ቅጣቶች በተግባር የሚፈጸሙት በእነዚህ ተቋማት እንደመሆኑ መጠን ክልከላው የሕፃናቱን መብት የሚጠብቅ ቢሆንም፣ ክልከላው መኖሪያ ቤትን የሚመለከት አለመሆኑ ክፍተት አለበት፡፡ ሕገ መንግሥት ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ የቤተሰብ አባላት ሕፃናትን ለማረም በማሰብ የሚፈጽሙትን ቅጣት ይፈቅዳል፡፡
ከሕገ መንግሥቱ በታች ያሉ ዝርዝር ሕግጋትም በተመሳሳይ መልኩ ግን ሰፋ ባለ መልኩ በልዩ ሁኔታ ሕፃናት መቅጣትን የሚፈቅዱበት ድንጋጌዎችን ቀርፀዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን አስተዳደግና እነሱን ከመቅጣት ጋር የተያያዘ ኃላፊነትን የተመለከቱ ሁለት ድንጋጌዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አንቀጽ 267(2) ሲሆን ‹‹ያደረጋቸውን ጥፋቶች በማመዛዘንና አስተዳደጉን በመጠበቅ አስተያየት ቀላል የሰውነት ቅጣቶችን አካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ ለመፈጸም ይችላል፤›› በሚል ‹‹ቀላል የሰውነት ቅጣት››ን የሚፈቅድበት ሁኔታ አለ፡፡ ድንጋጌው የቅጣቱ ዓላማ ሕፃኑን በአግባቡ ለማሳደግና የፈጸመውን ጥፋት ለማረም የሚፈጸም መሆኑን ግልጽ አድርጓል፡፡ የሆነ ሆኖ ከቤተሰብ ሕግጋቱ መሻሻል ጋር በተያያዘ ድንጋጌው በመሻሩ ወቅታዊ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ያም ሆኖ በተሻሻሉት የቤተሰብ ሕግጋትም ተመሳሳይ ድንጋጌ እናገኛለን፡፡ ለአብነት የፌዴራሉን የተሻሻለ የቤተሰብ ሕግ ብንወስድ ሕጉ በአንቀጽ 258(2) ‹‹አሳዳሪው አካለ መጠን ላልደረሰው ልጅ መልካም አስተዳደግ ተገቢነት ያለውን የዲሲፕሊን ዕርምጃ ለመውሰድ ይችላል፤›› ሲል ደንግጓል፡፡ የዲሲፕሊን ዕርምጃ ተግሳጽ፣ ቁጣ፣ ቀላል የሰውነት ቅጣት፣ ቁንጥጫ ወዘተን ሊያካትት እንደሚችል ልብ ይሏል፡፡
ሁለተኛው የፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌ እስካሁን ድረስ ተፈጻሚነት ያለው ሲሆን ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ ላይ የምናገኘው ነው፡፡ ሕጉ በአንቀጽ 2038(1) ‹‹አንድ ሰው ሆን ብሎ ሌላው ሰው ሳይፈቅድ በሚያደርገው መንካት በዚህ መንካቱ ጥፋተኛ ነው፤›› ሲል ቢደነግግም፣ ሕፃናትን በተመለከተ ግን በአንቀጽ 2039(ሐ) ላይ ተፈጻሚ የማይሆንበትን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ‹‹ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው የማይባለው ሥራው የተፈጸመው ተከሳሹ ልጁን፣ የአደራ ልጁን፣ ተማሪውን ወይም አሽከሩን በሚገባ ለመቅጣት ሲል በሰውነቱ ላይ ተገቢ የሆነውን አቀጣጥ ፈጽሞበት እንደሆነ ነው፡፡›› ስለዚህ ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግም ሕፃናት በመምህራቸውና በአሳዳሪያቸው እንዲቀጡ የሚፈቅድ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ 
የወንጀል ሕጉም ከሌሎቹ ሕግጋት በጊዜ ቅደም ተከተል የቅርብ ቢሆንም ሕፃናቱን ከቅጣት የሚያድናቸው አልሆነም፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 567 እና አንቀጽ 68(2) ጣምራ ንባብ ሕፃናቱን መጉዳት ወንጀል ቢሆንም ለመልካም አስተዳደግ ከሆነ ግን በወንጀል አያስጠይቅም፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 567 ሙሉ ንባብ እንዲህ ይላል፡፡
567 - ለአካለ መጠን  ያልደረሱ ልጆችን መጉዳት
(1)ለአካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ የሚጠብቅ ወይም በኃላፊነት የሚያሳድግ ማንም ሰው በማናቸውም ምክንያት ወይም ሁኔታ ልጁን የበደለ፣ ችላ ያለ፣ ከአቅሙ በላይ ያሠራ ወይም የመታ እንደሆነ ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡ 
(2)ወንጀሉ በልጁ ጤንነት፣ ደኅንነት፣ ትምህርት ወይም አካላዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በሚያስከትልበት ጊዜ አስፈላጊ ሲሆን ከቤተ ዘመድ ሥልጣን የመሻሩ ቅጣት እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
(3)ይህ ድንጋጌ በወላጆችና ተመሳሳይ ኃላፊነት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ለመልካም አስተዳደግ የሚወስዱትንና ሕግን የማይቃረን የዲሲፕሊን ዕርምጃን አይመለከትም፡፡ 
ወንጀል ሕጉ ከልካይም ፈቃጅም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ወላጆችና ተመሳሳይ ኃላፊነት ያላቸውን ሰዎች ሕፃኑን እንዲቀጡ ይፈቅዳል፡፡
የሕግጋቱ ክፍተት
ከላይ በዝርዝር የተገለጹትን የአገራችንን የተለያዩ ሕግጋት ይዘት በጥሞና ለመረመረ ሕግጋቱ የሕፃናትን የሰብዓዊ መብት በተለይም የአካል ደኅንነት መብት፣ ከአካልና ከአዕምሮ ጥቃት የመጠበቅ መብት በማስከበር ረገድ ክፍተት እንዳለበት መረዳት ይቻላል፡፡ የክፍተቶቹ ምንጭ በዋናነት ሕፃናት በወላጆቻቸው፣ በአሳዳጊያቸው ወይም በመምህራኖቻቸው የሚቀጡበትን ሁኔታ በመፍቀድ ላይ ነው፡፡ የድንጋጌዎቹ ይዘትም ወጥነት የሌለውና የሕፃናቱን መሠረታዊ ጥቅም በማስቀደም ካልታዩ በቀር ሕፃናትን ለቅጣት ወይም ለጥቃት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ሦስት ክፍተቶችን ለማሳየት እንሞክር፡፡ 
ቀዳሚው ሕገ መንግሥቱ አገራችን ከፈረመችው የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን ጋር ያለው ተቃርኖ ነው፡፡ አገራችን የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን በመፈረም በሕፃናት ላይ በወላጆች በማናቸውም ምክንያት (ጠባይ ለማረምም ቢሆን) ቅጣት ወይም ጥቃት እንዳይደርስባቸው የመጠበቅ ግዴታ ገብታለች፡፡ ከዚህ ዓለም አቀፍ ግዴታዋ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ሕገ መንግሥቱ በትምህርት ቤቶችና በማሳደጊያ ተቋማት ቢከለክልም በቤት ውስጥ ሕፃናት አካል ላይ የሚፈጸም ቅጣትን ይፈቅዳል፡፡ ይህም የአገራችንን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታ የመፈጸም ቁርጠኝነትን መና ያስቀረዋል፡፡ 
ሁለተኛው ዝርዝር ሕግጋቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ካላቸው ተቃርኖ የሚመነጭ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በትምህርት ቤቶችና በማሳደጊያ ተቋማት ሕፃናት የአካል ቅጣት እንዳይደርስባቸው ይከለክላል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉና የወንጀል ሕጉ ግን ወላጆች፣ መምህራን፣ አሳዳጊና ተመሳሳይ ኃላፊነት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ለሕፃኑ መልካም አስተዳደግ እስከሆነ ድረስ የሕፃናትን መቀጣት ይፈቅዳሉ፡፡ በተለይ የወንጀል ሕጉ ከፌዴራል ሕገ መንግሥት መውጣት፣ አገራችን የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን ከፈረመች በኋላ የተረቀቀና የፀደቀ ሕግ እንደመሆኑ መጠን የሕፃናቱን መብት ችላ ማለቱ ግርምት ይፈጥራል፡፡ የዝርዝር ሕግጋቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መቃረናቸው የሕገ መንግሥቱ በበላይነት ወይም በቀዳሚነት መፈጸሙን አያስቀረውም የሚል የሕግ ትርጓሜ መርህ መከተል ቢቻልም የሕግጋቱ ይዘት በሕግ ማሻሻል እስካልተስተካከለ ድረስ ላለመፈጸማቸው ዋስትና አይሆንም፡፡ 
ሦስተኛው የሕፃናትን መቀጣት የሚፈቀዱት ሕግጋት የተጠቀሙባቸው ቃላትና ሐረጎች ለትርጉም አስቸጋሪና የሕፃናቱን መብት በልዩ ሁኔታውም ውስጥ ለማስከበር አዳጋች የሚያደርግ ነው፡፡ በዝርዝር ሕግጋቱ የሕፃናት ቅጣት የሚፈቀደው ‹‹ከደንበኛው ሕሊናዊ ልማድ ወሰን ካልወጣ›› (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 68(2)፣ ‹‹ለመልካም አስተዳደግ››፣ ‹‹ቀላል የሰውነት ቅጣት››፣ ‹‹ተገቢ የሆነውን አቀጣጥ›› ወዘተ በሚሉ ለትርጉም አስቸጋሪ የሆኑ ሐረጐች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መስፈርቶች በማን ዕይታ ይመዘናሉ? ወላጅ ወይም መምህር ስሜታዊ ሆኖ ሕፃናቱን በሚቀጣቸው ሁኔታ መስፈርቶቹ መሟላታቸውን አብነት የሚሆነው ማነው? ለአባት ቅጣቱ ለመልካም አስተዳደግ የተገባ ቢሆን ጉዳዩን ገለልተኛ ሆኖ ለሚዳኘው ያልተገባ ሊሆን ይችላልን? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች ቀላል መልስ የማያገኙና አፈጻጸሙን የሚያከብዱ ናቸው፡፡ 
እንደማጠቃለያ
ሕፃናትን መቅጣት የባህል፣ የልማድ፣ የሃይማኖት ወይም የአመክንዮ ትንተና አይኖረውም አይባልም፡፡ ሕፃናትን መገሰጽ፣ ማስተማር፣ በጎና ክፉውን እንዲለዩ ማድረግ ተገቢም፤ የሚደገፍም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቅጣት ሕፃናቱን ያርማል፣ ያስተምራል፤ በመልካም እንዲያድጉም ይረዳል፡፡ ሕፃናትን መምታት፣ መቆንጠጥ፣ መግረፍ፣ መቀጥቀጥ፣ መደብደብ፣ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ በምንም መልኩ ሕፃናትን ሊያስተምርና ሊያርም አይችልም፡፡ በሕፃናት ሥነ ልቦና ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በመመታት የሚቀጡ ሕፃናት ድንጉጥ፣ ፈሪ፣ ትምህርት የማይገባቸው፣ መምህራንን የሚፈሩ፣ ሐሳባቸውን መግለጽ የማይችሉ ወዘተ እንደሚያደርጋቸው ነው፡፡ በእርግጥ ወላጆችና መምህራን ሕፃናትን ለመጉዳት በማሰብ ይቀጣሉ አይባልም፡፡ ያም ሆኖ ግን ቅጣቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሆነ፣ የሕፃናቱንም የወደፊት ሁኔታና ትምህርት የሚጎዳ ከሆነ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡
ሕፃናትን በመምታት መቅጣት በኅብረተሰቡ ውስጥ የዘለቀ አስተሳሰብ በመሆኑ ልማዱን ለማስቀረት ብዙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች የሚያስፈልጉ ቢሆንም፣ ቢያንስ በሕግ ደረጃ በወጥነት መብቶቻቸውን ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ አካለ መጠን ያደረሰ ሰው የአካል ደኅንነት መብቱ ተጠብቆ ደካማና ጥገኛ የሆኑት ሕፃናት የአካል ደኅንነት መብት፣ ከአካላዊና አዕምሮአዊ ጥቃት የመጠበቅ መብታቸውን አለማክበር ፍትኃዊም አሳማኝም አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን ከፈረመችው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን አንፃር ሕፃናትን ከመቀጣት፣ ከመመታት፣ ከመጠቃት የሚጠብቅ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋታል፡፡ በአንዳንድ የምዕራብ አገሮች ልጆቻቸውን ሳይቀጡ ወይም ሳይመቱ በማስተማር ብቻ ጠባያቸውን መግራት እንደቻሉት ማኅበረሰባችንም በዚህ ረገድ ለውጥ ለማምጣት መሥራት ይኖርበታል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖተር ጋዜጣ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር