ከአዲስ አበባ ናዝሬት ለተዘረጋው የፍጥነት መንገድ ማስፋፊያ ለሆነው የሞጆ- ሐዋሳ-ሞያሌ መንገድ ከፊል ግንባታ የሚውል 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ ተጠየቀ፡፡

የብድር ጥያቄውን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ያቀረበው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ፈጻሚ ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መሆኑን የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር ጥያቄውን ያቀረበው ከዝዋይ-ሐዋሳ ላለው የመንገድ ግንባታ መሸፈኛ የሚሆን 300 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የዚህ መንገድ አጠቃላይ ወጪ 370 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በብድር ከሚገኘው 300 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ የሚቀረው ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌ (የኬንያ ድንበር ከተማ) መንገድ የሚገነባው በተለያዩ ምዕራፎች ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የሚካሄደውም ለሁለት ተከፍሎ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ከሞጆ-መቂ-ዝዋይ ያለው መንገድ የመጀመሪያው ምዕራፍ አጠቃላይ ወጪውም 225 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሞጆ-መቂ ያለውን የመንገድ ክፍል ለመገንባት ከአፍሪካ ልማት ባንክ 126 ሚሊዮን ዶላር ሲገኝ፣ ቀሪው 99 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እንደሚሸፈን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ቀሪውን ከመቂ-ዝዋይ የሚገኘውን መንገድ ለመገንባት ደግሞ ከኮሪያ የኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመገኘቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀሪውን ወጪ ይሸፍናል፡፡
ከዓለም ባንክ የተጠየቀው ብድር ከዝዋይ-ሐዋሳ የሚያመራውን መንገድ ለመሸፈን የሚውል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኩ የቀረበውን የብድር ጥያቄ ተቀብሎ እየገመገመ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በባንኩ በኩል የብድር ጥያቄውን እየገመገመ ያለው ቡድን መሪ የቀድሞው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ተስፋ ሚካኤል ናሁሰናይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
የተጀመረው የፍጥነት መንገድ ግንባታ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለመተግበር ያቀደው የፍጥነት መንገድ አገር አቀፍ ኔትወርክ አካል እንደሆነ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም የፍጥነት መንገዱ ሲጠናቀቅ ከሞጆ-ሐዋሳ እንዲሁም ከሐዋሳ-ሞያሌ ድረስ በአንድ ጊዜ አራት ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ እንደሚሆን፣ የመንገድ ፕሮጀክቱ ሌላው ዓላማም ኢትዮጵያን ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር ማስተሳሰር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር