ለ200 ሺህ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎች ስልጠና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ ነሐሴ 8/2006 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም እና በምስራቅ አፍሪካ የማይክሮሰፍት ድርጅት 200 ሺህ ኢትዮጵያዊያን  ስራ ፈጣሪዎችን ለማብቃት የግል ዘርፍ የትብብር ስምምነት ተፈራራሙ።
የልማት ፕሮግራሙ ለኢዜአ እንደገለጸው ስምምነቱ ሁለቱ ደርጅቶች በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ለ200 ሺህ ስራ ፈጣሪዎች የስልጠናና የክትትል አገልግሎት ለመስጠት ተስማምተዋል።
እነዚሀ አገልግሎቶችም አገር በቀል ስራ ፈጣሪዎችን በማብቃት የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠንና በዓለም ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ  የማይክሮሶፍት ፎር አፍሪካ ኢኒሽዬቲቭ አካል ይሆናሉ፡፡
ስምምነቱ በስራ ፈጠራ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማሳደግ ያለመ ነው።
በስምምነቱ መሰረት ከፍተኛ የማይክሮሶፍት በጎ ፍቃደኞች ስራ ፈጣሪዎችን በመከታተል በስትራቴጂና በገበያ ድጋፍ በማድረግ ምርጥ ስራ ፈጣሪዎችን በመደገፍ ለማይክሮሶፍት ፎር አፍሪካ ኢንሽዬቲቭ ሽልማት እጩ ያቀርባሉ።
በተጨማሪም ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ነጻ ሶፍትዌር ለሚያቀርበው ማይክሮሶፍት "ቢዝስፓርክ" ለተሰኘ የዓለም ፕሮግራም እድል እንዲያገኙ ለማስቻል ይሰራሉ።
በቀጣይም ስራ ፈጣሪዎችን ምርታቸውንና አገልግሎቶቻቸውን በማቅረብ  በማይክሮሶፍት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በኩል ዓለም  አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኙ ድጋፍ ይሰጣሉ።
ስምምነቱ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢዝነስና ስራ ፈጣሪዎችን ለማነሳሳት ለተቀረጸው የራስን ቢዚነስ መገንባት በሚል ስያሜ  የስልጠና ፕሮግራም  ያካትታል፡፡
በኢትዮጵያ  የልማት ፕሮግራሙ ተወካይ ኢዩጌኔ ኦውሱ  በማይክሮሶፍት የሚቀርቡ ምርቶችና አገልግሎቶች  ወጣትና ተስፋ ሰጪ ስራ ፈጣሪዎችን አቅም ለማመንጨት ልዩ የሆነ እድል መሆኑን ነው የተናገሩት።
ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገትና የእመርታ ልማት ጉልህ ሚና  እንዲጫወቱ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ማይክሮሶፍት ኃላፊ ኢሪክ ኦዲፖ በበኩላቸው እንደተናገሩት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያፋጥኑ የሚችሉ አገር በቀል ስራ ፈጣሪዎችን አቅም፣ ዕውቀትና ችሎታ ማዳበር ወሳኝ ነው።
በማይክሮሶፍት በአፍሪካ የጅመራ ተሳትፎና የትብብር ኢኒሽዬቲቭ ዳይሬክተር አምሮቴ አበደላ እንደተናገሩት ስራ ፈጣሪዎች ፈጠራን በማጎልበትና የአፍሪካ ኢኮኖሚ  ለዘለቄታው  ተወዳዳሪ እንዲሆን  ቁልፍ ሚና አላቸው።
የተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ማይክሮሶፍት ብዛት ባላቸው አገሮች በዘለቄታዊ ልማት፣ ርሃብን በማጥፋት፣ በመልካም አስተዳደርና በሕግ የበላይነት ዙሪያ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር