ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቆም ብለው ያስቡ!

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዋር ውስጥ እየታየ ያለው አካሄድ የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ማድረግ የተሳነው ይመስላል፡፡ ምንም ያህል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንዲህና እንዲያ ተደረገ ቢባልም፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ
ፓርቲዎች ሕዝብን ማዕከል እያደረጉ አይደሉም፡፡ ይህንንም በተለያዩ መገለጫዎች ማሳየት ይቻላል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከዚህ አንፃር እንቃኛቸዋለን፡፡
ኢሕአዴግ ባለፉት ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ ለማወያየት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ ከምርጫ 97 በኋላ ይህንን ሐሳቡን ቀይሯል፡፡ እስካሁን ድረስ በጠንካራ ተቃዋሚዎች አለመኖር ደስተኛ አለመሆኑን የሚናገረው ኢሕአዴግ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀምጦ ለመነጋገር ፈቃደኛ አይደለም፡፡ መነጋገሩ ቀርቶ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመኖራቸው በራሱ ደስተኛ አይመስልም፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰላማዊ ሠልፍ፣ ሕዝባዊ ስብሰባና መሰል ተግባራትን ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ የተለያዩ መሰናክሎችን ይፈጥራል፡፡ በሰበብ በአስባቡ ለቅስቀሳ የወጡ የፓርቲ አመራሮችንና አባላትን ያስራል፡፡ ለሚያቀርቡዋቸው የመብት ጥሰትና የዲሞክራሲ መጓደል ጥያቄዎች ምላሽ አይሰጥም፡፡ በርካታ አቤቱታዎችና ጥያቄዎች እንዳሉዋቸው ሲናገሩ ለማዳመጥ ፍላጎት የለውም፡፡ 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩን ከማጣበብ አልፎ የሚያዳፍን ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ነን ያለነው እያሉ የሚወተውቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በሽብርተኝነት እየተከሰሱ ናቸው፡፡ የፍርድ ሒደቱን በተመለከተ ለጊዜው የምንለው ባይኖርም፣ በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሽብርተኝነት ነገር ሲመጣ ብዙዎችን ያስደነግጣል፡፡ ገዥው ፓርቲ አገር እንደመምራቱና ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አካል የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ እንዳይረበሽና ሕዝቡ ውስጥ ያለው ስሜት እንዳይበረዝ ማድረግ ካልቻለ፣ መጪው ምርጫም ሆነ የአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንከን ይፈጠርበታል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሒደቱ እንዳይደናቀፍ ሲል ከአወዛጋቢ ነገሮች ራሱን ማራቅ አለበት፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለሕዝብና ለብሔራዊ ደኅንነት ሲል የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ቢኖሩ እንኳን ዲሞክራሲያዊውን ሒደት እንዳያበላሽ መጠንቀቅ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው በሕዝብ ስም የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉት የሕዝቡን ልብ መማረክ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን ጥርጣሬና ሥጋት ውስጥ የሚከቱ ዕርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር መንግሥትና ሕዝብ ይለያያሉ፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሲለያዩ ደግሞ ሕዝባዊነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሚታይበት አሠራር ሊሰፍን ይገባዋል፡፡
በመሆኑም ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም በገባው ቃል መሠረት ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ኃይሎች ጋር መነጋገር አለበት፡፡ የቱንም ያህል አስቸጋሪ የሆኑ ችግሮች ቢያጋጥሙም በሆደ ሰፊነት ለሕዝብ ሲባል ውጥረት መርገብ ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ እውን ሊሆን የሚችለው ከተጣደፈ የፖለቲካ ውሳኔ በፊት መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሕዝብ ጋር ያቃቅራሉ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሒደቱንም ይበርዛሉ፡፡
በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩልም የሚታየው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ በከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማዕቀፍ ሥር መካሄድ ሲገባው ከዚህ በተቃራኒ ሲዘወር ይታያል፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ገዥውን ፓርቲ ከመክሰስና ከማውገዝ ባለፈ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍለው ለመወያየት ዝግጁ ናቸው ወይ? የፈለገውን ያህል በደልና ችግር ቢደርስባቸው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለማራመድ ቁርጠኝነት አላቸው ወይ? የሕዝብንና የአገርን ጥቅም ያስቀድማሉ ወይ? የአባላቶቻቸውን ውሎና እንቅስቃሴ ያውቃሉ ወይ? ለሕግ የበላይነት ይሠራሉ ወይ? ብዙ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡
በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ፕሮግራሞቻቸውንና የድርጊት መርሐ ግብራቸውን ሲቀርፁ ለሕዝብ ጥቅም መቆማቸውን ቢተነትኑም በተግባር ግን አይታይም፡፡ የሕዝቡን መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች አንስተው እነሱ ቢመረጡ በምን ዓይነት መንገድ እንደሚፈቱ ሲናገሩ አይሰሙም፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከገዥው ፓርቲ የተለዩ የሚሉዋቸውን አማራጭ ፖሊሲዎች በዝርዝር አፍታተው ሲገልጹ አይታዩም፡፡ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የተቃኙ የፖሊሲ ግብዓቶችን አያሳዩም፡፡ ከዚህ ይልቅ ገዥውን ፓርቲ እግር በእግር እየተከተሉ በመተቸትና በማውገዝ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፡፡ በዚህ መሀል ሕዝብ ይረሳል፡፡
ገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ ሰላማዊንና ሕገወጡን እያቀላቀላችሁ ናችሁ ብሎ ሲከሳቸው በተጨባጭ ውድቅ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ለሰላማዊው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚረዱ ሐሳቦችንም ሲያመነጩ አይስተዋሉም፡፡ በውግዘትና በትችት የተሞሉ መግለጫዎቻቸው ጥላቻን ባዘሉ ዓረፍተ ነገሮች ታጅበው ሲቀርቡ የአገሪቱ ፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ዕጣ ፈንታ ያሳዝናል፡፡ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ የበለጠ እንዲጠብ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጪው ምርጫ እየተዘጋጁ ይሁኑ ወይም ትተውት እንደሆነ እንኳ አይታወቅም፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማሰብ ይቻላል?
ገዥውም ፓርቲ ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቆም ብለው የሚያስቡበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት የዘለቀውና በጥላቻና በመረረ ስሜት የተበላሸው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር በበቂ ሁኔታ ካልተከፈተ ችግር አለ፡፡ መጪው ምርጫ ካሁኑ ወደ ድቅድቅ ጨለማ እያመራ ይመስላል፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት ወደ ጎን እየተገፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራስ ወዳድነት እየገዘፈ ነው፡፡ የአሁኑን የአገሪቱ ፖለቲካ ምኅዳር እያጨናነቁ ያሉት አላስፈላጊ ነገሮች በጊዜ መልክ ካልያዙ መራጩን ሕዝብ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞውን ይቀጫሉ፡፡
በተደጋጋሚ እንደምንለው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለአገሪቱና ለሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ንትርክና ሽኩቻ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ሕዝብን እናከብራለን የሚሉ ፖለቲከኞች በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ የአገሪቱን የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር አያበላሹ፡፡ ዲሞክራሲያዊት አገር እንድትፈጠር የሚፈልጉ ወገኖች ከራሳቸውና ከቡድን ስብስባቸው በላይ ለሕዝብ ቅድሚያ ይስጡ! ሕዝብን ማዕከል ያድርጉ! ቆም ብለው ያስቡ!  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር