የቡና ምርትና ግብይት የሚቆጣጠር መንግሥታዊ ተቋም ሊቋቋም ነው

-አዲስ የቡና ስትራቴጂ እየተቀረፀ ነው
ቡናን ከምርት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን የግብይት ሒደት የሚቆጣጠር፣ በቡና ላይ የሚሠሩ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ ጠቅልሎ የሚሠራ አዲስ መንግሥታዊ ተቋም ሊቋቋም ነው፡፡
 ከቡና ምርትና ግብይት ሒደት ጋር ተያይዞ አለ የሚባለውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለውን አዲሱን መንግሥታዊ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችለው ጥናት ተጠናቅቆ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል፡፡
የተቋሙ አስፈላጊነት ላይ ውሳኔ ከደረሰ በኋላ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በቡና ምርትና ግብይት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ  ቡናን የሚቆጣጠር መንግሥታዊ ተቋም እንዲቋቋም መወሰኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ምንጮች ከሆነ እስከዛሬ የነበረውን የቡና ግብይት ሙሉ ለሙሉ የሚለውጥና አዲስ አሠራርን ይፈጥራል የተባለው ይህ ተቋም በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ተቋሙን ለመፍጠር የተደረገው ጥናት ተጠናቆ ለመንግሥት ከመቅረቡ በፊት የሌሎች የቡና አምራች አገሮች ልምድ እንዲወሰድ መደረጉም ተገልጿል፡፡
በተለይ በቡና ላይ የሚታየውን ረዥም የግብይት ሰንሰለት በመስበር ቀልጣፋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር በማድረግ በአገር ውስጥ የቡና ዋጋ እንዳያሻቅብ ለማድረግ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድንም ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር የሚኖረው ሲሆን፣ የቡና ምርታማነትም እንዲያድግ የሚያስችል አሠራር እንደሚከተልም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ተቋም መቋቋም ጎን ለጎን አዲስ የቡና ስትራቴጂ በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ ስትራቴጂው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ከብራዚል ቀጥላ ሁለተኛዋ የቡና አምራች እንድትሆን ለማድረግ ያስችላል የተባሉ ዝርዝር የአፈጻጸም ሥልቶችን የያዘ መሆኑም ታውቋል፡፡ አዲሱን የቡና ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ምርት ማሳደጉ ዓይነተኛ አማራጭ በመሆኑ፣ ምርቱን ማብዛት እንዲቻል አዳዲስ የቡና መሬቶች እንደሚዘጋጁና አነስተኛ ገበሬዎችም የቡና እርሻቸውን እንዲያስፋፉ የሚስችሉ አሠራሮችን የሚያሳይ ነው፡፡
አገሪቱ በቡና ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ አሁን ቡና ከሚለማባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ አዳዲስ የቡና ማብቀያ ቦታዎች እየተለዩ መሆኑም ታውቋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ አንዳንድ የአማራና የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ወረዳዎች ውስጥ ለቡና ምርት የሚሆን ቦታ ይዘጋጃል፡፡ ለምርቱ የሚሆን ፋይናንስ የሚገኝበትን ዕድል ለማመቻቸት ጠቋሚ መረጃዎች የያዘው ስትራቴጂ፣ የግል ባለሀብቶች በዚህ ሥራ ውስጥ እንዲገቡ የሚሰጡ ማበረታቻዎችን ያካተተ ነው፡፡ ስትራቴጂው ተግባራዊ እስኪደረግና አዲሱ ተቋም እስኪቋቋም ድረስ ግን በጊዜያዊነት የቡና ግብይትን ለማገዝ ንግድ ሚኒስቴር ሥር ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ ወር ተኩል በፊት የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ይህም ዳይሬክቶሬት የወጪ ንግድን የሚመለከቱ ሥራዎችን ራሱን ችሎ እንዲሠራ ለማስቻል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የራሱን ቢሮ ይዞ እንዲቋቋም የተደረገው አዲሱ ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር ተሹሞለት ሥራ ጀምሯል፡፡ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙትም የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አማካሪ አቶ አሰፋ ሙሉጌታ  መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተጻፈ በ  ተጻፌ በሪፖርተር ጋዜጣ


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር