ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማገናዘብ የተሳነው የወጪ ንግድ ዕቅድ

አገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ መንግሥት በየዓመቱ የተለያዩ ሁኔታዎችን መሥፈርት በማድረግ ዕቅድ ይይዛል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የወጪ ንግድ ምርቶችን ወደተለያዩ የዓለም ገበያ መዳረሻዎች ለማቅረብ በማሰብ ዕቅዶችን ለጥጦ ማቅረብም እየተለመደ ነው፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ዕቅድና አፈጻጸም ሲነፃፀሩ ግን መዛነፎች እየታዩ ናቸው፡፡ እነዚህ መዛነፎች እየታዩ ያሉት ደግሞ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ባለመቻሉ ምክንያት ነው፡፡ 
ለምሳሌ በ2005 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የተያዘው ዕቅድ አራት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የተገኘው ግን 3.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህ አፈጻጻም ባያመፃድቅም ብዙም ሳያስከፋ ያለፈ ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. ዕቅዱ ተለጥጦ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢፈለግም፣ ያለፉት አሥር ወራት የወጪ ንግድ ገቢ 2.6 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በሁለት ወራት ውስጥ የተቀረውን 2.4 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተዓምር ካልሆነ በስተቀር የማይታሰብ ነው፡፡ 
ከአገሪቱ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ የሆነው ቡና አሁንም ትልቁ የገቢ ምንጭ ቢሆንም፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት 822 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበታል የተባለው ቡና የአሥር ወራት አፈጻጸሙ ሲታይ ከ429 ሚሊዮን ዶላር አልዘለለም፡፡ ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም. በነበሩት ሦስት ዓመታት በአማካይ 806 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ዘንድሮ ዕቅዱ ይሳካል ተብሎ ቢጠበቅም የሚታዩት ተጨባጭ ሁኔታዎች ግን ይህንን አያመላክቱም፡፡ 
በአንድ ወቅት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ይባል የነበረው ቡና ባለቤት የሌለው ይመስል ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረበት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው እያሸቆለቆለ ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ አነስተኛ ዋጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የማይፈልጉ የዘርፉ የተወሰኑ ተዋናዮች አገር ውስጥ ይቸበችቡታል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በኮንትሮባንድ ወደ ጐረቤት አገሮች እየተወሰደ ይሸጣል፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ማለትም ግብርና ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ፀረ ኮንትሮባንድ የፀጥታ ኃይሎች ሊቀናጁ ባለመቻላቸው ነው፡፡ 
በዚህ ዘርፍ ያለው ሌላው ችግር በቡና ኤክስፖርተርነት የማይታወቁ ግለሰቦችና ድርጅቶች አገር ውስጥ ቡና በውድ ዋጋ ይገዙና በዓለም ገበያ በደከመ ዋጋ ይሸጡታል፡፡ የእነሱ ዓላማ በተጓዳኝ ለሚያካሂዱት የአስመጪነት ሥራ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በመሆኑ፣ ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለተለያዩ ሸቀጦች መግዣ ያውሉታል፡፡ በቡና ኤክስፖርት ላይ እንዲህ ዓይነቱ የተዝረከረከና አስገራሚ አሠራር ሰፍኖ፣ የሚወጣው ዕቅድ ተጨባጭ ሁኔታን ያገናዘበ አይሆንም፡፡ 
በሆርቲካልቸር ዘርፍም ብንመለከት አስገራሚ ጉዳዮች ይገጥሙናል፡፡ ይህ ዘርፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን መሠረት በማድረግ የተለጠጠ ዕቅድ ተይዞለት በአበባ፣ በአትክልት፣ በፍራፍሬና በተለያዩ ምርቶች ውጤታማ እንዲሆን ተፈልጐ ነበር፡፡ በየዓመቱ ከዚህ ዘርፍ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶም ሰፋፊ መሬቶች ቀርበው፣ የባንክ ብድሮች ተሰጥተው፣ ገበያዎች ተመቻችተውና የተለያዩ እገዛዎች ቢደረጉም አዳዲስ ገበያዎች በመፍጠር በተጨባጭ የሚታይ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት የተያዘው ዕቅድ እንዲከለስ ተደርጓል፡፡ የሚገርመው ዕቅዱ ተከልሶ እንኳን ያንን የተከለሰ ዕቅድ ማስፈጸም አልተቻለም፡፡ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማገናዘብ ችግር በዚህ ዘርፍ ጐልቶ እየታየ ነው፡፡
ከግብርና የምርት ውጤቶች ወጣ ሲባል ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ጀምራለች፡፡ በንግድ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው 30 ዓይነት ምርቶች ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ አሥር ምርቶችን እያቀረበ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ጅምር ላይ ሲሆኑ፣ በሌሎቹ ምርቶች ላይ የሚታየው የአፈጻጸም ችግር ዕቅዶችን በድጋሚ መከለስ እንደሚገባ ማሳያዎች አሉ፡፡ በዓለም ገበያ ውስጥ ሰብሮ መግባት አለመቻል፣ ገበያውን የሚመጥን የምርት ጥራት አለመኖር፣ የአመራረት አቅም ደካማነትና የዕቅድ መዛባት በመኖራቸው ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አብሮ መጓዝ አልተቻለም፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመሩት ብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ በዚህ ዓመት በከፍተኛ ሥራዎች ተጠምዶ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለንግድ ሚኒስቴርና ለማዕድን ሚኒስቴር ክትትል የሚደረግባቸው የኤክስፖርት ምርቶች አፈጻጸም ላይ የተለያዩ መመርያዎችን መስጠትና አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን ዕቅድና አፈጻጸም አልተጣጣሙም፡፡ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ የተሰጠባቸው ዘርፎች ሊሻሻሉ አልቻሉም፡፡ 
በሌላ በኩል የአገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶችና የመዳረሻ ገበያዎች ቁጥር መጨመር እንደ ስኬት ቢነገርም፣ አገሪቱ አሁንም ከዚህ መስክ መጠቀም በሚገባት ደረጃ ላይ አይደለችም፡፡ ዕቅድ ሲወጣ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘብ አለበት የሚባለው ቢቻል ከአፈጻጸሙ በተሻለ ሁኔታ እንዲያድግ ማድረግ፣ ካልሆነ ደግሞ ተቀራራቢ እንዲሆን መደረግ አለበት በሚል ታሳቢ ነው፡፡ የዘንድሮን የወጪ ንግድ ገቢ ስናነፃፅርም ዘንድሮ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር እንጂ፣ አምና ወይም ካቻምና ከተገኘው ገቢ ጋር መሆን የለበትም፡፡ ባለፉት ዓመታት ተገኙ የተባሉት ገቢዎች የራሳቸው ዕቅድ ነበራቸውና፡፡ 
አገሪቱ ከወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ ዕቅድ ሲያዝላት ዕቅዱ በተከፋፈሉ የጊዜ ሰሌዳዎች፣ ምርቶች ለገበያ ከሚደርሱባቸው ጊዜያት፣ አምራቾችና ላኪዎች ከሚያገኙዋቸው የባንክ ብድሮችና የተለያዩ ድጋፎች፣ ከመሠረተ ልማቶች፣ ከቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶች፣ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ያልተጠበቁ ክስተቶችና ከዓለም ወቅታዊ ሁኔታና ገበያ አንፃር ሊተነተኑ ይገባል፡፡ ዕቅዶች ተለጥጠው እንዲቀርቡ ሲፈለግም ኮታ ለመሙላት በሚደረግ ጥድፊያና ሁካታ ሳይሆን፣ ይልቁንም በከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ተፈጻሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረስ አለበት፡፡ ዕቅዶች ተፈጻሚነታቸው የሚረጋገጠው ተጨባጭ ሁኔታዎችን ሲያገናዝቡ ብቻ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረግ የይስሙላ እንቅስቃሴ ዕቅዶችን እርባና ቢስ ያደርጋቸዋል፡፡  
ዜናው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር