ደመወዛችን ሃምሳ ጉዳያችን መቶ!

እነሆ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ልንጓዝ ነው። አጀማመራችን በፀጥታ የተጠነሰሰ ነው። የዛሬዎቹ ተሳፋሪዎች ትንፋሽ ያላቸው አይመስሉም። በውጥረት የታፈነው ጎዳና መንገደኛውን መተንፈሻ የነሳው ይመስላል።
ጩኸት ኑሮው የሆነው ወያላ ዕድሜው በለቅሶ ተጀምሮ በጩኸት በሚገባደድ ሕዝብ መሀል ያለ ዕረፍት ይጣራል። እንደ ንጋት ጎርናና ድምፁ ሁሉ ጎርበጥባጣ ኑሮው ይለሰልስለት ይመስል እሪ ሲል አይታክትም። ጥሪ በማይፈልገው የትግል ጎዳናችን ላይ ግን የወያላው ልፋት መና የቀረ ይመስላል። ከወዲያ ወዲህ ሲሯሯጥ ከቆየ በኋላ አካባቢውን የሚቀያይረው ሕዝብ ፍልሰቱ መቼም የሚቆም አይመስልም። ሰው የሚደርስበትን ቦታ እያሰበ ስለአዋዋሉ፣ ስለኑሮው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለሥራው እያውጠነጠነ ባላሰበው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የህልማችንና የሩጫችን ውጤት በአብዛኛው አንገት ያስደፋል። ሲዘሉ መሰበር የመንገዱ ህልውና መሠረት ቢሆንም ቅሉ በዚህ በአገራችን የአረማመድ ዘዬ ሳንዘል በተቀመጥንበት የተሰበርን ጥቂት አይደለንም። የዚህ ጎዳና ትርክት ብዙ ነው። 
ማጠቃለያ ሐሳብ ይሰጠው ሲባል ግን ቃሏ አንዲት ናት። እሷም ‘ተግዳሮት’ ትባላለች። መውጣትና መውረድ አክርማና ስንደዶ ሆነው ያልቀየሱት ጎዳና በእርግጥ በየትም አገር ታሪክ አይኖርም። ነፃ ብሎ መንገድ፣ እንደ ጨርቅ የሚጠቀለል አልጋ ባልጋ ጎዳና ለሰው ልጅ አይገባውም የተባለ የተፈጥሮ ሕግ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ግጭቱ፣ ተንኮሉ፣ ተግዳሮቱና ሸሩ በማያልቅ የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉም እንደራሱ አረማመድ እየተጓዘ እንደ ሕዝብ ደግሞ በጋራ መጓጓዣ እንዝርቱ ይፈትላል። በፈተለው ልክ ሁሉም የድርሻውን ሕይወት እየሸመነና እየለበሰ፣ ለታሪክና ለታዛቢ በሩን ይከፍታል። መንገድ ሁሉን ይዳኛል። የፍትሕ ያለህ ባዩ ወዮታ ግን እያደር በርትቷል። መቼም መልካሙና በጎው ነገር አልበረታ ያለበት ዘመን አይደል?!       
ታክሲያችን ተንቀሳቅሶ። የዝምታው ድንበር ቀስ በቀስ መጣስ ጀምሯል። ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በየትኛውም የዕድሜ እርከን ያለ ሁሉ ተሳፍሯል። ሠራተኛው ስለሥራው፣ ተማሪው ስለትምህርቱ፣ ነጋዴው ስለወረቱ ይነጋገራል። በመሀል ደግሞ ስለኑሮ ጡዘት ሹክ ይባባላል። ከወሬው ሳይታቀብ በቆረጣ በወያላው ሒሳብ አምጣ መባልን ፈርቶ የሚሳቀቅም አለ። መቼስ መንገድ የማያሰባስበው የተለያየ ዓይነት ተፈጥሮ የሌለው የለም። በዚህ መሀል፣ “ኑሮና የዓለም ዋንጫ ይመሳሰላሉ፣ ጋባዡ እየራበው እንግዳ ያጠግባሉ፤” ሲል አንድ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ወጣት ከጎኑ ካሉት ጋር ሲሳለቅ ይሰማል። “ሙሰኛና ገጣሚ እንደበዛብን ምንም አልበዛብንም፤” ትለኛለች ከጎኔ ተቀምጣ የታክሲውን ጣራ በራስ ቅሏ የምትታከክ መለሎ። ከሾፌሩ መቀመጫ ኋላ ከፊታችን ከተቀመጡ ተሳፋሪዎች አንድ ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ “የሌብነቱን ምንጭ ባላውቅም ሲፈጥረው አገሩ የጥበብና የኪነት ነው፤” አላት። አነጋገሩ ውስጥ ቁጭት ነገር አለ። 
በዚህ መሀል የመንገዱ ፍሰት ታወከና ታክሲያችን ቆመ። “ኧረ እባክሽ ሴትዮ ተረጋጊ፤” ጮኸ ሾፌራችን። ሁላችንም ወደ ደጅ አሰገግን። እጅግ ውድና ዘመናዊ መኪና የምታሽከረክር እንስት መንገዱን ቆላልፋዋለች። “እሷ እቴ ስትሰማህ እኮ ነው!” ይላል ወያላው። ግጥም አድርጋ መስታውቶቿን ጠረቃቅማ የምታሽከረክረው ሴት ሰምታ ለመመለስ፣ ተሳስባ ለመጓዝ ፈቃደኛ አትመስልም። “እስኪ አሁን መንገዱ የሕዝብ፤” ቢል ከሾፌሩ አጠገብ እዚያው ጋቢና የተሰየመ ወጣት፣ “አይ አንተ ሕዝብ የግለሰቦች ከሆነ ውሎ ማደሩን አታውቅም?” ብሎ ሾፌሩ መለሰለት። ሴትዮዋ የያዘችውን ዘመናዊ መርሰዲስ ቢገጭ በቀላል ወጪ የማይጠገን ስለሆነ በፍራቻ ሁሉም ቅድሚያ እየሰጠ አሳለፋት። ‘አመሰግናለሁ’ አለማለቷን ወያላው ታዝቦ፣ “ሌላው ቢቀር ‘ቴንኪው’ ርካሽ ነው! እስኪ አሁን ምነ አሰሰታት?” ከማለቱ አንዱ በጎርናና ድምፅ፣ “ጠግቦ የተኛና ርቦት የሞተ አንድ ነው፤” አለው። በመጠን መኖር እንዴት መታደል ነው?   
 ጉዟችን ቀጥሏል። አንዱ ተሳፋሪ ወርዶ ሌላ ተሳፋሪ ይጫናል። ወያላው በወረዱት ፈንታ ታክሲውን ለመሙላት ይጣራል። ሲገኝም ትርፍ ይደርባል። “ይቅርታ እዚህ ጋ ጠጋ ትሉላት?” ፊት መቀመጫ ያሉትን ያስቸግራል። “ደርብብን ኧረ! ‘ላለው ይጨመርለታል’ አይደል የሚባለው?” አለው ጎልማሳው። የምትደረበዋ ልጅ ቀበል አድርጋ፣ “ታዲያስ! እንዲህ ታክሲ ወንበር ላይ ካልተለማመድነው ደግሞ ነገ ከነገ ወዲያ የመተካካት ፖለቲካ ይሰምርልናል?” ብላ ፈገግ አሰኘችን። “ጨዋታ ትችያለሽ እ? ለእንዳንቺ ዓይነቷስ እንኳን መጠጋት ብነሳም አይቆጨኝ፤” አለ ጎልማሳው። 
“አመሰግናለሁ” ከማለቷ ጎልማሳው ወዲያው ቀጠል አድርጎ “አሉ እንጂ ወይ ጨዋታ አያውቁ ወይ ጨዋታ አይወዱ! በሕዝብ ወንበር የባለንብረትነት ስሜት የሚሰማቸው። አይደለም እንዴ? አጋጥመውሽ አያውቁም?” አላት። “ፍርድ እንደራስ ነው። የአንዳንዱ ሰው የታክሲ ውስጥ አቀማመጥ ከአኗኗሩና ከመጣበት አድካሚ መንገድ ጋር ሲገናኝ ታዝቤያለሁ፤” አለችው። “እሱስ ልክ ነሽ። እኛም የሰውን አቀማመጥ ካመጣጡ ጋር አገናዝበን መቀበል አበዛን መሰለኝ፣ በሰላም ተሳፍሮ በሰላም እንዳይወርድ በሽብር ተሳፍሮ በነውጥ መውረድ የሚመኘውን እናበረታታለን፤” አለ ጎልማሳው። ግራ ገብቶን መላው የታክሲ ተሳፋሪዎች እርስ በርስ ተያየን። “በቀኝ አሳይቶ በግራ ሸጠው ማለትስ አሁን ነው፤” የምትለኝ አጠገቤ የተቀመጠችው መለሎ ናት። ከጀርባ የተቀመጡ አንድ አዛውንት በበኩላቸው፣ “አላድለን ብሎ እንጂ እስኪ አሁን ስለወንበር ይኼን ያህል ዘመን መንገዋለል ነበረብን?” እያሉ ከጓደኛቸው ጋር ያወጋሉ። “መጀመሪያ የመቀመጫዬን” ያለችው ጦጣ ናት? ወይስ ዘንጅሮ? ጉድ ነው!    
መንገዱ ከተጋመሰ ቆይቷል። ወያላችን ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ በመመለስ ተጠምዷል። አንዳንዱ አፍንጫውን ይዞ መልስ ሲቀበለው ለአንዳንዱ የመልስ ሳንቲሙን ለመስጠት ወያላው ራሱ ይለምናል። “ኧረ ተቀበለኝ ወንድሜ!” ይላል ወያላው መጨረሻ ወንበር በጥግ በኩል በሁለቱም ጆሮዎቹ ‘ኢርፎን’ ሰክቶ ‘ስማርት ፎን’ ሞባይሉን እየጎረጎረ ዓለምን ወደረሳው ታዳጊ አስግጎ። በስንት ጉትጎታ አጠገቡ ባሉት ተሳፋሪዎች ጉሰማ ልጁ ጆሮውን የደፈነበትን ገመድ ነቅሎ መልሱን ተቀበለ። “ይኼ ትውልድ እኮ በዚህ ዓይነት እንኳን መብቱን በተመለከተ ጥያቄ ሊጠይቅ ለአሮጌው ጥያቄ መልስ ሲመጣም ግድ የለውም ማለት ነው፤” አሉ አንደኛው አዛውንት። እዚያው አካባቢ ጠየም አጠር ያለች የደስደስ ያላት ልጅ፣ “ምን ይደረግ? አኳኋናችን አልጥም ያለው ይህ ትውልድ ተፀይፎን ቢሆንስ? እያየ ላለማየት እየሰማ ላለመስማት ወስኖ ይሆናል፤” አለች። 
አዛውንቱ እኛ የገባን የገባቸው አይመስሉም። ሒደት ቀለሟን ስትቀያይር በቋንቋም ታደንቋቁረን ይዛለች። ታዳጊው በተራው ነገሩን በዝምታ ሊያልፈው ስላልፈለገ፣ “ታዲያ በየቦታው የተንኮል፣ የርህራሔ አልባነት፣ የሐሜት፣ የጦርነት፣ የሽብርና የክፋት ነጋሪት እየተጎሰመ ምን ማድረግ አለብን?” ብሎ ጠይቆ ሲያበቃ በአካባቢው ያሉትን ተሳፋሪዎች ገረመማቸው። “እውነት ነው! ‘ቫይበር’ እና ‘ፌስቡክ’ ባይኖሩን ኖሮ ምን እንሆን ነበር? ዓለም እንደሆነች ይኼን ያህል ሺሕ ዘመን ፍትሕ የማታውቅ፣ በፖለቲካ ቁማር ሰላማዊ ኑሮን ማመስ ያልሰለቻት ሆነች። ደግሞስ እንኳን ፍትሕን የዓለም ዋንጫን አራት ዓመት እየጠበቅን መሳተፍ ህልም የሆነብን ከዚህ በላይ ብንዘጋጋ ይገርማል?” አለች ጠይሟ ወጣት ነገሩን አስፍታ። እንደኖሩት ኖረው እንደሚሰነብቱት እየሰነበቱ ያሉት አዛውንት በበኩላቸው ዝምታን መርጠዋል። እንዲህ እንዲህ ያለው ወቅት ላይ ዝምታው ራሱ ብዙ ይናገራል፡፡
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ በሞባይል ስልካቸው የጡረታ ገንዘባቸውን ለመቀበል ከሄዱበት እየተመለሱ መሆናቸውን ያወራሉ። ጋቢና የተቀመጠ ደላላ አልሸጥ ስላለው ቤት እያነሳ፣ “ምነው ሰው ነፈሰበት?” ሲል እንሰማዋለን። “እንዴት አይነፍስበት? በየሄደበት የሚያስተነፍሰው በዝቶ፤” ትለኛለች ከጎኔ የተቀመጠችዋ መለሎ። “ያለው ማማሩ የሌለው መደበሩ ሆነና አመዳሞች በዛን። ይህ አልበቃ ብሎን በኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገብን መሆናችን ጠዋት ማታ ይበሰርልናል። ኧረ ጎበዝ በዕድር ድክመት እንጂ ከሞትን የቆየን እኮ በዝተናል፤” ሲል መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት ተነፈሰ። ወዲያው ሾፌራችን ቦታ ይዞ ሲያቆም ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። ተንጋግተን ከመውረዳችን ዝናብ ስለያዘን ታክሲ ውስጥ የነበርን ሁሉ አብረን በአንድ ሥፍራ የመጠለል ዕድል ገጠመን። ደግሞ ይኼን ጊዜ በግል አውቶሞቢል ዘና ቀብረር ብለው ወደሚሄዱበት የሚያዘግሙትን እየታዘበ ያው ልጅ “ያለው ምን አለበት?” ከማለቱ አጠገቡ የቆመው ያ ጎልማሳ፣ “ያለውማ ምን አለበት! የሌለው ነው እንጂ የሚያብላላበት። የሰው ከማየትና ከመመኘት የራሳችንን ኑሮ መኖሩ አይሻልም?” አለው። ዝናቡ ይለዋል። ወጣቱ “መቼ ወደን ሆነ ወዳጄ። ቅድም ያቺ ልጅ (እየጠቆመ) ያለቺው እየረበሸን እንጂ!” አለው። “ምን ነበር እሱ?” ቢለው ጎልማሳው፣ “በማጭበርበርና በሌብነት እንደ ጎማ የሚያስተነፍሰን በዛ!’ ስትል አልሰማሃትም እንዴ?” አለው። አባርቶ እንስክንለያይ ድረስ ጨዋታው ቀጠለ። አንዱ ነገረኛ “የደመወዝ  ጭማሪው ከመበሰሩ የቤት ኪራይ፣ የትምህርት ቤት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ መሰቀል ጀመረ እኮ?” እያለ ወጉን ጀመረ፡፡ የሚወርደውን ዝናብ እያየን የዋጋ ንረቱንና የጭማሪውን ወሬ አቦካነው፡፡ ሁሉም የመሰለውን እያወራ ደቂቃዎች ነጎዱ፡፡ በስተመጨረሻ አንዱ፣ “ደመወዛችን ሃምሳ ጉዳያችን መቶ” እያለ ወግ ሲጀምር ዶፉ ለቆን ከተጠለልንበት እየወጣን ተበታተንን። መልካም ጉዞ!  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር