ደመወዝ ጭማሪና አሳዛኙ ድርጊት

የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ሁሌም የሚተች ነው፡፡ ይሻሻላል ተብሎ ሲጠበቅ ብሶበት ይገኛል፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች ከእንከን ፀድተው አያውቁም፡፡
ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ከሸማቾች ሮሮ አምልጠው ያውቃሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ የንግድ ሥርዓታቸው ሚዛናዊ አይደለም፡፡ የራስን ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ በሸማቾች ሲረገሙ መስማትም የተለመደ ነው፡፡ ይህ አብዛኛውን የንግዱ ኅብረተሰብ የሚገልጽ ነው ባይባልም፣ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች መገለጫ ሊሆን እንደሚችል ግን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ 
የእስከዛሬውን ትተን ሰሞኑን ብዙዎቻችንን ያስገረመን፤ እንደውም ያበሳጨንን ድርጊት በአስረጅነት መግለጽ ይቻላል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተሰማው መንግሥት ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ የመጨመሩን መረጃ ተከትሎ እየፈጸመው ነው የተባለው ድርጊት ነው፡፡ ነጋዴዎቻችንን ያስገረመን ብቻ ሳይሆን መች ይሆን እንዲህ ካለው ተግባር ፀድተው ሸማቾችን በአግባቡ የሚያስተናግዱት? ብለን አሁንም እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው፡፡
ደመወዝ ሊጨመር ነው የሚለውን ወሬ የሰሙ አንዳንድ ነጋዴዎች ወዲያው የዋጋ ለውጥ አደረጉ፡፡ ዋጋ ጨመሩ፡፡ ነገሩ ሠርግና ምላሽ ሆነላቸውም ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ደመወዝ ከተጨመረ እኛም ዋጋ መጨመር አለብን የሚለው ስግብግብ ስሜትቸው ፈጥጦ ወጣና ሸማቹን ምስቅልቅል ስሜት ውስጥ ከተቱት፡፡ በደመወዝ ጭማሪው ሊደሰት የሚገባውን የኅብረተሰብ ክፍል ከወዲሁ አሸማቀቁት፡፡ ምን ዋጋ አለው ብሎ ከንፈሩን እንዲመጥ አስገደዱት፡፡ 
ይህ አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ ገና ለገና ደመወዝ ሊጨመር ነው ተብሎ ወሬው እንደተሰማ ለዋጋ ጭማሪ መንቀልቀል ጤናማ የንግድ ባህሪ አይደለም፡፡ ሆኖም አደረጉት፡፡ 
ከሁሉም በላይ አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ ደመወዝ ተጨምሮልሃል የተባለው ሠራተኛ የተጨመረለት ደመወዝ ገና ኪሱ ሳይገባና ምን ያህል እንደተጨመረለት እንኳን ሳይታወቅ ይህ ወሬ መስማቱ ነው፡፡ የቱንም ያህል የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገ ቢታወቅ እንኳ አሁን ባለው ደረጃ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ፈጽሞ ትክክል አይደለም፡፡ መስገብገብና ለአገልግሎታቸው ከፍሎ ለሚጠቀም ዜጋቸው የሚገባም አይደለም፡፡ 
ደመወዝ ተጨመረ መባሉ ብቻ በፍጹም ዋጋ ሊያስጨምር የሚያስችል ምክንያት አይደለም፡፡ መንግሥትም እንደገለጸው የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ የዋጋ ጭማሪን ሊያስከትል ወይም በኢኮኖሚ ውስጥ ተፅዕኖ ሊፈጥር በሚችል ደረጃ አይደለም፡፡ 
ይህ ከሆነ ደግሞ ለዋጋ ጭማሪ የሸሚዛቸውን እጅጌ ሰብስበው ሸማቹን ለመንጠቅ የተዘጋጁ ነጋዴዎችን ድርጊት በፍጹም ዝም ሊባል የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ የሚያመላክተን የደመወዝ ጭማሪው ተደርጓል የሚለው መረጃ ከተሰማ በኋላ አንድ የማውቃቸው የመንግሥት ሠራተኛ ‹‹እንኳን ደስ አልዎት ደመወዝ ሊጨመርልዎ ነው፤›› ስላቸው፣ ‹‹እንኳን አብሮ ደስ አለን›› ሊሉኝ አልፈቀዱም፡፡ ምክንያቱን ያወኩት ቆየት ብሎ ነው፡፡ ከእርሳቸው እንደተረዳሁትም ከደመወዝ ጭማሪው ጐን ለጐን በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ተጨመረ የተባለው ዋጋ ስሜታቸውን ነክቷል፡፡ 
የንዴታቸው ብዛት ሌላው ቢቀር ምነው ደመወዝ እስክንቀበል እንኳን ቢታገሱን ብለው ደመወዝ ጭማሪውና ነጋዴዎች ዋጋ እየጨመሩ ነው የተባለው ወሬ ተደበላልቀው ደስታቸውን በአግባቡ እንኳን ሊያጣጥሙ ያለመቻላቸውን ልረዳ ችያለሁ፡፡ 
በሌላ በኩል ግን መንግሥት ሁኔታውን በመከታተል ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችንም እቀጣለሁ ብሏል፡፡ ግን እንዴት? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ካልተመለሰ ሸማቹ ባልተገባ ሁኔታ ተጎጂ ሊሆን ነው፡፡ 
በተናጠል ስናየው መንግሥት ደመወዝ የሚጨምርላቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ ነጋዴዎቹ የፈጠሩት አላስፈላጊ ተግባር ግን የሚጎዳው ሁሉንም ነው፡፡ ምክንያቱም አንተ ደመወዝ ስለተጨመረልህ የምትከፍለው ይህንን ያህል ነው፡፡ አንተ ደግሞ ካልተጨመረልህ ዋጋ ይቀነስልሃል አይባልምና የችግሩ ሰለባ የሚሆነው ሁሉም ሸማች በመሆኑ በሁሉም ዜጎች ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ የከበደ ይሆናል፡፡ 
በነገራችን ላይ በሸቀጦችና በአገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ጭማሪ የተደረገው የቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ሳይቀር እንጨምራለን ያሉም መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት ቤት አከራያቸው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ 300 ብር ጨምሬያለሁ የሚል መልዕክት የደረሳቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት በንዴት ምነው ደመወዝ ጭማሪው በቀረ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ነገ ተነገወዲያ በዚሁ በደመወዝ ጭማሪ ሰበብ በሁሉም አገልግሎቶች ላይ ዋጋ እንዲጨመር የሚገፋፋ ጭምር ስለሚሆን መንግሥት ጉዳዩን በልዩ ትኩረት ሊመለከተው ይገባል፡፡ ዕርምጃውም ፈጣን ካልሆነ ደመወዝ የተጨመረላቸው ሠራተኞች ጭማሪውን በአግባቡ እንዳያጣጥሙ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዋጋ ጭማሪው እንዳይጎዱ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል መቀልጠፍ ያስፈልጋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር