የእኛ አገር ትምህርት ሁለት የቆዩ የቁልፍ ችግሮች

(በተለይ በመለስተኛና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ)
በሳምራዊት ኅሩይ
የኢትዮጵያ ትምህርት ከፍተኛ የውድቀት ታሪክ በእጅጉ ከደርግ ዘመን ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትርምስ፣ ርዕዮተ ዓለማዊና ፕሮፓጋንዳዊ እመቃ፣ የዘመቻና የጦርነት ጣጣዎች ኅብረተሰቡንና ትምህርቱን አዳሽቀውታል፡፡
በየትም ቦታ ቅድሚያ ይሰጠው የነበረው የፓርቲ፣ የፖለቲካ፣ የፕሮፓጋንዳ፣ የክብረ በዓልና የዘመቻ ሥራ ነበር፡፡ የሚያስመሰግነው፣ የሚያሸልመውና የሚያሾመው ይህ ዓይነቱ ‘አብዮታዊ ሥራ’ ነበር፡፡ ከትምህርቱ አስተዳደር አንስቶ እስከ መምህራን ድረስ በ‹‹አብዮታዊ ግዴታዎች›› መጠመድና ሥራ መፍታት እየበዛ ትምህርቱ ተዝረከረከ፡፡ ሥራ ትጋትና ዋጋ አጥቶ፣ ሥራ ጠሉ ሁሉ ‹‹አብዮታዊ›› እና ‹‹ጓድ›› እየተባለ ጥቅማ ጥቅሙን ሲቀራመትና የታታሪው ገምጋሚና አዛዥ ሲሆን የሥራ ፍቅርና ትጋት ሞተ፡፡ ‹‹አብዮታዊ አስተዋጽኦ››፣ ‹‹ጓድ››ነትና የ‹‹ጓድ›› ዘመድነት ከትምህርት ቤት የማያባርር፣ ልዩ ፈተና የሚያሰጥ፣ ፈተና የሚያሳልፍ፣ ከደንብ ውጪ ለመድገምና ማትሪክን ደጋግሞ በመደበኛነት ለመፈተን የሚያስችል እየሆነ በመምጣቱ የሙያ ሥነ ምግባሩ ተቦዳደሰ፡፡ 
የመምህራን ከሥራ መጓደል የተማሪን ታጉሮ መዋል እያስከተለ፣ የመምህራን የሥራ ስሜትና ሥነ ምግባር መውደቅ የተማሪውን ችሎታ እያደከመ፣ 12ኛ ክፍል ደርሶ የማለፍ ዕድልም ህልም እየሆነ መሄድ ራሱ ተስፋ እያሳጣ የተማሪው የትምህርት ስሜትና ትጋት ይጠፋል፡፡ የወጣት አጥፊነት ይለማል፡፡ የትምህርቱ መፋለስና የይስሙላ መሆን የግምግማና የማለፊያ ሥርዓቱን ያፋልሰዋል፡፡ በአግባቡ ያላስተማረ መምህር በቀላል ፈተና፣ ብዙ ተማሪ ከወደቀም ነጥብ በመጨመር ጉድ መሸፈን ውስጥ ይገባል፡፡ ያልሠራና ተስፋ ያጣ ተማሪም በበኩሉ በኩረጃ፣ በዛቻ፣ በልመናም ሆነ በጥቅም ልውውጥ ማርክ የማግኘት ትግል ውስጥ ይገባል፡፡ ሳይሠሩ ማግኘትና ማለፍ በተስፋፋበት ሁኔታ ውስጥ፣ ‘‘ለፍተህ አግኝ፣ አላስኮርጅም፣ ማርክም አልጨምርም’’ የሚል መምህር ቅራኔና ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ በተማሪ መውደቅ የሚደሰት ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ የጥሩ መምህር መመዘኛ ውሉን ይስታል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ብዙ ተማሪ አሳልፎ ከታች ለሚመጣው ቦታ ለማስለቀቅ ማለፊያውን እያወረደው ሲሄድ መማር የክፍል ቆጠራ ጉዳይ መሆኑ አጠቃላይ ይሆናል፡፡ ከአስተዳደሩ አጐሳቋይነት በተጨማሪ የተማሪው ሥርዓት እየለቀቀና ተተናኳይ እየሆነ መሄድ፣ የመምህራኑን ታጋሽነት፣ ቅንነትና ጨዋነት እየሸረሸረው፣ በመምህራኑም በኩል የሚታየው ብልሽትና ተተናኳሽነት ይበልጥ ተማሪውን እየመረዘ መከባበርና መግባባት ያዳግታል፡፡ በአጠቃላይ አላሻቂው ማኅበራዊ አካባቢ፣ የትምህርት አስተዳደሩ፣ መምህሩና ተማሪው አንዳቸው ሌላቸውን ቁልቁል እየጐተቱ በኢሕአዴግ ዘመንም ይኼው እየተባባሰ ቀጥሎ፣ ዛሬ የምንገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ 
የጥራቱን ጉዳይ እንተወውና ቀድሞ ሁለተኛ ደረጃን አልፎ ወደ ኮሌጅ ለመግባት ጥቂቶች ብቻ የሚችሉበት በር ዛሬ ሰፍቷል፣ ገናም ይሰፋል፡፡ በዚህ በኩል የነበረው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ተገፏል፡፡ ግን ተማሪ ተስፋ መቁረጥን ፈረካክሶ በስሜትና በትጋት የመማር ለውጥ አላሳየም፡፡ ድህነትና የኑሮ መቃወስ በዚህ ውስጥ የራሱን ድርሻ ያበረክታል፡፡ ይህ እንደታወቀ ሆኖ ከትምህርት ጋር በተያያዙ ሁለት ሥር የሰደዱ ችግሮች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የችሎታ ማነስና የትምህርት አካሄድ ችግር፡፡ 
ሀ) የተጠራቀመ የችሎታና የዕውቀት ማነስ
ሀ.1. ከክፍል ደረጃ ወደ ክፍል ደረጃ እየተንከባለለና እየተደራረበ የመጣ የዕውቀትና የልምምድ ማነስ ችግር ተማሪውን ጠፍሮታል፡፡ በዚህም ምክንያት ለየደረጃው የሚሰጠውን ትምህርት ለመሸከም ለማዋሀድ ይቸገራል፡፡ በየጊዜው የሚታየው ከወጣት አጥፊነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ቀልጦ መቅረት፣ ማርፈድና ትምህርትን ጥሎ (‘ፎርፎ’) መሄድ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ 20 ቀን የቀረ የሚታገድበት ደንብ ቀርቶ በነበረበት ወቅትም (በኢሕአዴግ ዘመን) መምህሩ ሁሉ ቀሪ መቆጣጠር ትቶ ለፈተና ጊዜ ብቻ የሚመጣው በርክቶ ነበር፡፡ ግማሽ ዓመት ሙሉ ጠፍቶ ሳያሟላ የቀረ ተማሪ ገንዘብ ከፍሎ እየተፈነተ የሚያልፍበት መንገድም ተከፍቶ ነበር፡፡ ዛሬም በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ውሎ ከመመለስ በስተቀር ውጤት አመጣሁ ብሎ የመሥራት ብርታትና ጥረት ችግር እንደሆነ ይገኛል፡፡ ሒሳብና ፊዚክስ ከኤድስ ጋር ተመሳስለዋል፡፡ አይገባንም የሚል ሽንፈትም ተንሰራፍቷል፡፡ 
ሀ.2. የእንግሊዝኛ ‹‹ማስተማሪያ›› ቋንቋና ችሎታ 
በሌሎች ትምህርቶች በኩል ያለውን የማስተማር መማር ተግባር ቀስፎ የያዘው ትልቁ ችግር፣ የእንግሊዝኛ ችሎታ ማነስ ነው፡፡ ችግሩ መምህሩንም ተማሪውንም ይመለከታል፡፡
የሚሰጠው የእንግሊዝኛ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመገልገል ክህሎትን ለማስጨበጥ የሚያስችል አይደለም፡፡ ለዚያውም የምንባብ ሐሳብ፣ የቃላት ትርጉምና የዓረፍተ ነገር አሰካክ ገለጻ አገርኛ ቋንቋ ይገባበታል፡፡ 
በሌሎች ትምህርቶች በኩልም መምህሩ የራሱንና ተማሪዎቹን የቋንቋ ችግር አሸንፎ ዕውቀትን ለማድረስ በጉራማይሌ ሲያስተምር ኖሯል፡፡ (ዛሬ የሳተላይት ትምህርት ተጀምሮም ቢሆን የክፍል መምህሩ ከጉራማይሌ አልወጣም፡፡ ወዶ ሳይሆን ለማስረዳት ሲል)
ለተማሪው የሚሰጠው ማስታወሻ (ጭማቂ)፣ መጽሐፉና ፈተናው ግን ሁሌም በእንግሊዝኛ ነው፡፡ (ከአገርኛ ቋንቋ ትምህርት በስተቀር) የሚያነብና የሚያጠናው በማይገባው (በደንብ በማይረዳው) ቋንቋ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ልሥራ ያለ ችግሩን የሚወጣው በአብዛኛው በሽምደዳ ነው፡፡ ከዚህ ዝቅ ያለው በፈተና ጊዜ ከሌላው ለመኮረጅ ወይም ማስታወሻ ይዞና ደብተር ገልጦ ለመገልበጥ የሚታገል ነው፡፡ 
ለ. ጤናማ ያልሆነ የትምህርት አካሄድ
ለ.1. በየክፍል ደረጃው የሚሰጠው ትምህርት ውዝፍ ችግርን ሊያቃልልና ሊጠግን ይቅርና ለዚያ ደረጃ የተወሰነውን ትምህርት አጣጥሞ ለማገባደድ በማያስችሉ ችግሮች ውስጥ ተይዞ ቆይቷል፡፡    
ጫጫታ፣ ሹክሹክታ፣ መማሪያ ደብተርንና መጽሐፍን ይዞ አለመምጣት፣ የክፍልና የቤት ሥራ አለመሥራት፣ ለመማር ፍላጐትና ትኩረት ማጣት የትምህርት ሒደት ፈተናዎች ናቸው፡፡ 
ከእነዚህ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ጭቅጭቆችና ትንቅንቆች (ቁጣ፣ ስድብ፣ ተንበርከክ/ውጣ፣ ኩርኩም፣ ማጥፊያ ውርወራ፣ ድብድብ፣ ወዘተ) የትምህርት ሥራው ሲበጣጠስ ኖሯል፡፡ 
ከዚህ ባሻገር ተንጠባጥቦ የሚመጣ አርፋጅና ከቀደመ መምህር ጋር ወጥቶ የነበር ተመላሽ ተማሪ፣ በየክፍሉ እየተዞረ የሚነገር ማስታወቂያ፣ ዕርዳታ የማሰባሰብ ቅስቀሳ፣ የቲኬት ሽያጭና ገንዘብ ለቀማ፣ ወዘተ ክፍለ ጊዜን ሲሻሙ የቆዩ ችግሮች ናቸው፡፡ 
ከዕውቀት ማነስና ከፍላጐት ማጣት ጋር የሚዋደደው ጥፋተኛነት በምክር፣ በግብግብ፣ ወደ ቢሮ በመላክም ሆነ ወላጅ በማስመጣት የሚፈታ አልሆነም፡፡ መምህራን ረባሹና ትምህርት ጠሉ የተቀነሰበት ሰላማዊ ክፍል ለማግኘት ሲሉ ቀሪ መቆጣጠርን የተውበት፣ እንዲያውም ቀሪ አላደርግህም ፈተና ሲኖር ብቻ ና ብለው እስከመደራደር የደረሱባቸው ገጠመኞች ተከስተው ያውቃሉ፡፡ 
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የትምህርት ቤት አስተዳደር የቀሪ ቁጥጥርን በግቢ ውስጥ ያለ ትርምስን ለማቃለል መሣሪያ አድርጐ ሙጥኝ ያለበትና ስም ጥሪ ዋና ሥራ እስከመምሰል የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ባለበት መጥቶ የማያውቀውና ደብተር የለሹ ዱርዬ ሁሉ ይታጨቅና ንትርክ እየናረ አስተማሪ ጥሎ የሚወጣበት፣ ወይም እዚያው ሆኖ የ‹‹ምን አቃጠለኝ›› ሥራ የሚሠራበት አጋጣሚ ሲደጋገም ቆይቷል፡፡
ለ.2. የመምህርና የተማሪ ግንኙነት
የመምህርና ተማሪው ግንኙነት ከተበለሻሸ ብዙ ጊዜው ነው፡፡ አስተማሪው በተማሪ ዘንድ በጥያቄ በማፋጠጥ፣ በማንጓጠጥ፣ በዛቻ፣ ማርክ በመንፈግ፣ ከክፍል በማስወጣት፣ ወላጅ በማስመጣት፣ ቀሪ በመቆጣጠር፣ ወዘተ ጥቃት ሲፈጽም የሚውል ተደርጐ ይታያል፡፡ በአስተማሪውም ዘንድ ሙያውን እያማረረ የሚያስተምር ብዙ ነው፡፡ ወደ ክፍል ሊያስተምሩ መሄድ ወደ ‹‹ትንቅንቅ›› የመሄድ ያህል ሆኖ ቆይቷል፡፡ የክፍልን ፀጥታ ከመቆጣጠሪያ ሁነኛ መሣሪያዎች አንዱ መኮሳተርና ደምን ማስቆጣት ነው፡፡ አንዱን ተለቅ ያለውን የፀጥታ አደፍራሽ በሆነ ምክንያት መምታት ወይም የሚያሸማቅቅ ስድብ መስደብ ተደማጭነትና ተከባሪነት ለማግኘት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ዘዴዎች ናቸው፡፡ በሳቂታነት ባህርይ የሚታወቅ መምህር ተማሪ በሚያናግርበት ጊዜ ኩስትርትሩ ወጥቶ ማየት እንግዳ አይደለም፡፡ ለማዋዛት ሲሞከር ከተማሪ በኩል ሊገለጽ የሚችለው ያልታረመ ባህርይ ይህንኑ ሲያበረታታ ኖሯል፡፡ በአጠቃላይ የተማሪና የአስተማሪ ፍቅርና መተሳሰብ ክፉኛ ተዳክሟል፡፡ 
ሐ. ተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ሥራ ላይ ሊውል አለመቻል 
የተማሪ ተኮር ትምህርት አሰጣጥ ጠቃሚነት አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ቀደም ብለው በተጠቀሱና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ተግባራዊ የማድረግ ጥረቱ ከንቱ ውትወታና ድካም ሆኗል፡፡
የባህል ልሽቀትና የወጣት አጥፊነት ተማሪውን ልሶ ለመጨረስ ጉልበት ማበጀታቸው (በተለይ በከተሞች)፣ ተማሪዎች ላሉበት ደረጃ የተዘጋጀውን ትምህርት ለማዋሀድ (Assimilate) የሚያስችል ቅርስ የሌላቸው መሆኑ፣ ትምህርት በሚቀርብበት ቋንቋ ላይ የችሎታ ችግር ያለባቸው መሆኑና ይህን መሰሉን ጉድለት የሚሞላ ድጋፍ ማጣት ተጋግዘው በግል ንባብ፣ በግልና በቡድን ሥራ የሚካሄድን ትምህርት ውጤታማነት አዳክመውታል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ተማሪ ሌሎች ሲሠሩ የሚመለከት፣ ሌሎች የሠሩትን የሚገለብጥና ባልተሳተፈበት የቡድን ሥራ ስሙን የሚያጽፍ ነው፡፡ 
በአንድ ክፍለ ጊዜ ተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ሊሰጥ የሚችለው ትምህርት በመጠን አነስተኛ መሆን፣ በሌላ በኩል የዓመቱን በርካታ የትምህርት ጭነት የማገባደድ ኃላፊነት ደግሞ ቶሎ ቶሎ ማጉረፍን የሚጠይቅ መሆኑ ሌላው ችግር ነው፡፡ 
በተጨማሪ ከፊል ወይም ሙሉ ክፍለ ጊዜን የሚወስድ ማስታወሻን (ኖትን) በሰሌዳ ላይ መለቅለቅም በራሱ ‘‘ትምህርት’’ ሆኖ ጊዜን ሲሻማ ኖሯል፡፡ በራስ አንብቦ የራስን ማስታወሻ የማዘጋጀት ነገር እንኳን የሁለተኛ ደረጃ የኮሌጅ ተማሪም ችግር ሊሆን በቅቷል፡፡ 
ኖት በመጻፍ ክፍለ ጊዜ መፍጀትና በተለያዩ ጣልቃ ገብ ነገሮች የትምህርት ሒደት መቆራረጥ የሳተላይት ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርቶችና የተወሰኑ የክፍል ደረጃዎች ላይ የተቃለለ ቢሆንም አጠቃላይ ችግሩ እንዳለ ነው፡፡ የሳተላይት ትምህርትም ቢሆን ለተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥ የሚያወላዳ አይደለም፡፡
እንደ መፍትሔ አንዳንድ ነገሮች 
ሀ. ለጤናማ ግንኙነት 
1.መምህራንና ተማሪዎች ታላቅ የልማት ኃይል ናቸው እየተባለ ከተሠለፉበት ሙያ ውጪ በሌሎች ሥራዎች ማሰማራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በነፃ ፈቃደኝነት የሚገባባቸውና የሙያ ግዴታ የሆኑ ተግባራት እየተደበላለቁ ችግር መፍጠራቸው መቆም አለበት፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የልማት ተግባር በተማሪዎች ትጋት፣ ዕውቀትና ችሎታ ላይ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከትምህርቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተግባራትም (ለምሳሌ ቤተ መጻሕፍትን ማደራጀት፣ የመጻሕፍትና የገንዘብ ዕርዳታ ማፈላለግ፣ የተጓዳኝ ትምህርት ክበቦችና የውድድር ሥራዎች) መደበኛውን የትምህርት ሥራ በሚጐዳ አካሄድ፣ ማለትም መምህራንና ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ገበታ እየተፋቱ የሚከናወኑ ከሆነም እያፈሰሱ መልቀም ይሆናል፡፡ 
2.የትምህርት ቤት አመራር፣ የመምህራንና የተማሪዎች ግንኙነት ዕድሳትን ይሻል፡፡ ‘‘በትምህርት ቤት ውስጥ ዋናው ሰው መምህሩ ነው’’ የሚል መፈክር ለትምህርት ቤቶች እንግዳ አይደለም፡፡ የተግባር ትርጉም ካጣ ግን ቆይቷል፡፡ መምህሩ በሁኔታዎች መዝማዥነት ከአራቂነትና ከቀራፂነት ደረጃ ወርዶ ከተማሪ እኩል ራሱን አስተካክሎ ‘‘የእኔ ወንድም ሥራዬን ልሥራበት ልቀቅልኝ ወይ ልልቀቅልህ’’ ባይ እስከመሆን ደርሷል፡፡ የትምህርት ሥራና የትምህርት ቤቶች ውጤታማነት የመምህራንን የማስተማር ብቃት፣ ፍላጐትና ትጋት በመንከባከብና በማበልፀግ ላይ የቆመ መሆኑ የትምህርት አመራሩም ሥራ ይህንን ማገልገል መሆኑ ተስቷል፡፡ መምህሩን አስተዳደሩ ላንቀጥቅጥ እያለ የሚሠራው ሥራ ውጤት አያስገኝም፡፡ የትምህርት አመራርና መምህሩ እንደ አንድ የሥራ ኃይል ልብ ለልብ ሆነው መንቀሳቀስ መቻላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በስብሰባ ብዛትና በ‘‘ዱላና በካሮት’’ ሥልት በመጥመድ ተጨባጭ አይሆንም፡፡ እስከማስወገድ ሊደርስ የሚችል ዕርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግበት ሁኔታ እንደሚኖር ዕውቅ ነው፡፡ ነገር ግን የመቀጣትና የመባረር አደጋን (ፍርኃትን) ሸር አድርጐ መሣሪያ አድርጐ ለመጠቀም መሞከር አጥጋቢ ውጤት አያስገኝም፡፡ ከፍላጐቱ ውጪ መምህሩ ቤተ መጻሕፍት ማዘውተር አለማዘውተሩን በመከታተል መምህሩን አንባቢ ማድረግ እንደማይቻል በተግባር ታይቷል፡፡ ለደካማ ተማሪዎችና ለሴት ተማሪዎች የትርፍ ጊዜ እገዛ መስጠትን የሥራ አፈጻጸም መመዘኛ አድርጐ፣ ለራስሀ ስትል እወቅበት የሚል ሥልትም የረባ ውጤት አላስገኘም፡፡ 
የትምህርት ቤት አስተዳደር ራሱን ከመምህሩ ነጥሎ ከድብድብና ከስድብ የፀዳ የትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር ተቆጣጣሪና የተማሪዎችን በደል ሰሚ፣ በመምህራንና በተማሪ መካከል ፈራጅ የመሆን ዓይነት ሚና መያዝ፣ እንዲሁም ፓርቲ ቀረብ ተማሪዎችንና የተማሪ መማክርት አባላትን እንደ መረጃ መጠቀም በሦስቱ ወገኖች መሀል ያለውን ግንኙነት ሲያበላሽ የቆየ ነው፡፡ መቅረትም አለበት፡፡ ተማሪ እንደ ወሬ አቀባይ መታየት የለበትም፡፡ አስተማሪው እንደ ተሳዳቢና ደንፊ ተደርጐ የሚታይበትና የሆነበት ግንኙነት መለወጥ አለበት፡፡ ብልሽቱ ከተስተካከለ መምህሩ በብዙ መንገድ የተማሪውን ችግር የሚጋራ፣ አንዳንዴም ከወላጅ ይበልጥ የተማሪው ጭንቀት አዳማጭና አማካሪ የሚሆን የቅርብ አለኝታ ነው፡፡ ይህንን የመምህሩን ሚና አስተዳደሩም ሆነ የተማሪዎች መማክርት (ካውንስል) በፍፁም አይተኩትም፡፡ ወደዚህ የሚያመጣ የመምህርና የተማሪ ግንኙነት መገንባት አለበት፡፡ በትምህርት አሰጣጥም ሆነ በሌላ ቅሬታ ቢኖር ተማሪው መጀመሪያ መምህሩን ማዋየት መልመድ አለበት፡፡ አስተዳደሩም መምህሩን ዘሎ የመጣ ስሞታ ሲደርሰው በቀጥታ መምህሩ ባለበት ተማሪው ቅሬታውን አውጥቶ እንዲያቃልል፣ ለሌላ ጊዜም ከሁሉ በፊት ወደ መምህሩ መሄድን እንዲገነዘብ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ይህ ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይሆን በሁሉም በኩል ‘‘እናትህን … ልበላት’’ ‘‘የእንትን ልጅ’’ እየተባባሉ ቡጢና ካራ እየተሰናዘሩ የሚዋልበትን ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል አዲስ መተማመንና መከባበር ለመፍጠር መትጋትን ይጠይቃል፡፡  
3.በሌላ በኩል የመምህሩ የሥራ ውጤታማነት መለኪያ የሚሆነው ሆኖ አብዛኛውን ከ75 በመቶ ያላነሰ ነጥብ ቀጥታ በተማሪዎች ላይ የሚያስከትለው የችሎታና የባህርይ ለውጥን የሚመለከት ሊሆን ይገባዋል፡፡ መምህሩ ከፍርኃት ነፃ ሆኖ የሚሠራበት ሁኔታ መፈጠር (በግላዊ ጥላቻ ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት አድልኦና ጥቃት ሊደርስበት የማይችል መሆኑን በተግባር የሚያሳምን አሠራር መዘርጋት) ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ቤቱ አመራር ከተወሰነ የፖለቲካ ቡድን አባላት ወይም ሸሪኮች ጋር ልዩ ቅርበት መፍጠር ወይም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን መርጦ ከማስጠጋት መራቅ መቻል አለበት፡፡ የመምህራንን ትብብር የሚጠይቅ ሥራ ሲገጥመው በግልጽ መጠየቅንና ችግሮችን በማሳሰቢያ፣ በማስጠንቀቂያና በቅጣት ወረቀቶች ለመፍታት ከመሞከር በበለጠ የቅርብ ውይይት ማድረግን መልመድ ያስፈልገዋል፡፡    
4.ከመምህራን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታና ግንኙነት ከተፈጠረ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ቀላል ይሆናል፡፡ 
ረብሻንና አልማጭነትን አሳፋሪ ማድረግ ይቻላል፡፡ 
በመግቢያና በእረፍት ሰዓት እየጐተጐቱና እያባረሩ የማስገባትን ልምድ ማስቀረት ይቻላል፡፡
በክፍል ውስጥ ሥራ ከተጀመረ በኋላ ማንኳኳት የማይኖርበትን፣ በሕመም ከቢሮ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ወይም በትምህርት ምክንያት ካልሆነ በቀር ተማሪ በግቢ ውስጥ የማይንቀዋለልበትን ሁኔታ የሁልጊዜም ማድረግ ይቻላል፡፡
መምህሩ በፈተና ላይ ነፃ ለቅቆ እንዲኮረጅ ለማድረግ የማይደፍርበትን ጨዋነት ማዳበር ይቻላል፡፡ 
ተማሪው ለቀጣዩ ደረጃ የሚያበቃ ዕውቀት መጨበጡ በተከታታይ ምዘናና ድጋፍ በአግባቡ ተረጋግጦ እንዲያልፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
የመምህራን በሙሉ ስሜት ለጐበዞችም ሆነ ለደካሞች እገዛ ማድረግ ተጨባጭ መሆን ይችላል፡፡
ከመላው ተማሪ ጋር በመሆን የአጥፊነት ዝንባሌዎችና ባህሎች በትምህርት ቤት ውስጥ ከመቆጣጠር አልፎ ማረም ይቻላል፡፡
ለ. የእንግሊዝኛ ችሎታን ለማሻሻል 
በአገራችን ያለው የእንግሊዝኛ ትምህርት ችግር ከሁሉም በላይ በትምህርት አሰጣጡ ላይ ያመዘነ ነው፡፡ ቋንቋን የመማር ነገር በቋንቋው መገልገል ነው፡፡ በቋንቋ በመገልገል ረገድ ትልቁና የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው መናገር ነው፡፡ የእኛ አገር ትምህርት ደግሞ የተገላቢጦሽ ተማሪው በአብዛኛው አዳማጭ አስተማሪው ተናጋሪ የሆነበት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ በኩል ያለብንን ችግር ለማስወገድ ይህንን በተቃራኒው እንዲገለበጥ ማድረግ ነው፡፡ 
የ ‘do/does’ ዓይነት ልብ እያወቃቸው አፍ የሚሳሳታቸውን ሰዋሰዎች ከሳምንት ባልበለጠ የጥያቄና መልስ የቃል ልምምድ ተማሪዎች ሊለምዷቸው ይችላሉ፡፡ “If I were … I wish …” ከተባለ የሚከተለው ሐረግ የዚህ ዓይነት ቅንብር በንግግር መጠቀሚያ በማድረግ ሊያከትም ይችላል፡፡ በዚህ መልክ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረቱ ጭውውቶችን አጥንቶ በመለማመድ ልዩ ልዩ የአጠያየቅና የአመላለስ ሥልቶችን፣ የፍላጐት፣ የምርጫ፣ የቁጭት፣ የምኞት፣ የአድናቆት፣ የግርምት፣ የማማከር፣ ወዘተ መግለጫዎችን የተመለከቱ መሠረታዊ መግባቢያዎችን በአጭር ጊዜ መጨበጥ ይቻላል፡፡
በአንደኛ ደረጃ የሚሰጥን የእንግሊዝኛ ትምህርት በዚህ መስመር ውስጥ ማስገባት ያሻል፡፡ እታች “Show me your nose. This is my …” በሚሉ ሥልቶች ዙሪያ መሽከርከር፣ “I wish … I had better … can I … not only … but also” የሚሉ ዓይነት ሥልቶችን ለመጠቀም ደግሞ ከፍተኛ ክፍል ውስጥ መግባት የሚል አመለካከት መቅረት አለበት፡፡ ታዳጊዎችም እንደ ትልልቆች ምኞትን፣ መገረምን፣ ደስታን፣ ወዘተ ስለወደፊቱ፣ ስላለፈውና ሰርክ ስለሚያደርጉት ሁሉ ይገልጻሉና በዕድሜያቸው ደረጃ መግለጽ የሚሹትን መጥኖ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ 
ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ትንሽ ያህል ለመነጋገር የሚያስችል ስንቅ ከያዙ ችሎታቸውን በብዙ ለማዳበር መፈለጋቸው አይቀርም፡፡ የእንግሊዝኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋነት፣ በኢትዮጵያ ትምህርት ውስጥ ያለው የመማሪያ ቦታና የአዋቂነት ምልክትነቱ ያበረታታቸዋል፡፡ አንድ ተማሪ በእንግሊዝኛ ሊናገር ሲሞክር ጉረኛ እያሉ የማሸማቀቅ ድርጊት በአመዛኙ በራስ አለማወቅ ከማፈር የሚመጣ ነውና ብዙው ተማሪ የማያሳፍር ዕውቀት እያገኘ ሲሄድ አሽሟጣጭም ይታጣል፡፡ ትምህርት በእንግሊዝኛ አማካይነት የሚሰጥበት የክፍል ደረጃ ላይ ሲገባም ቅጥአምባር አይጠፋም፡፡
የተማሪዎች የክፍል ውስጥ ብዛት እንደ ችግር መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ እንግሊዝኛን ማወቅ የሁሉም ችግር እንደመሆኑ የተማሪውን ስሜት መያዝ እስከተቻለ ድረስ እንኳን በመማሪያ ክፍል በአዳራሽም ውስጥ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡
ተማሪዎችን በአንድ ላይ እያስጮሁ በቃል መለማመድ አንድ አማራጭ ነው፡፡ በቡድን መድቦ የጭውውት ድርሻ እየተለዋወጡ አጥንተው እንዲመጡና በክፍል ውስጥ እያስከወኑ ነጥብ መስጠት፣ በተወሰነ ረድፍ ያሉ ተማሪዎችን እንደ አንድ ሰው አንድ ድርሻ እንዲወስዱ፣ ቀሪው ረድፍ ደግሞ ሌላውን ድርሻ ይዘው እንዲቀባበሉ ማድረግም ሌላ መንገድ ነው፡፡ በቀጣይነት በተላመዷቸው የዓረፍተ ነገር ሥልቶች የየራሳቸውን ጭውውት በቡድን አዘጋጅተውና አጥንተው መጥተው እንዲጫወቱ ማድረግና ነጥብ መያዝ ይቻላል፡፡ በሚጥሩት ተማሪዎች ላይ የሚታየው ለውጥና ነጥብ መሰጠቱ ቸልተኞቹንም እያነቃቸው ይሄዳል፡፡
ሐ. በሌሎች ትምህርቶች ያለ የዕውቀት ጉድለት ስለማካካስ
1.በመምህራን፣ በአስተዳደርና በተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት መስተካከል ከቻለ የማይገፋ ዳገት አይኖርም፡፡ ካለፉ የክፍል ደረጃዎች እየተንከባለለ የመጣ የዕውቀት ማነስን በግምገማ ለይቶ አውቆ አስፈላጊውን ማካካሻ እንደ ሁኔታው መቀየስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ርዕሰ ትምህርቶችን ለየቡድኑ ከፋፍሎ ቡድኖች በደንብ ተዘጋጅተውበት በልዩ ክፍለ ጊዜ እርስ በርስ እንዲማማሩበት ማድረግ፡፡ 
2.የዕውቀት መጉደል የሚመጣው ከዓመት ዓመት ያለውን ትምህርት ሳይማሩ በመቅረት ብቻ አይደለም፡፡ የመማሪያ ሥልቱ ከምልከታና ከሙከራ መራቁና የትምህርት ይዘትን የመመጠን ችግር የጉድለት መንስዔም ይሆናል፡፡ ይህን መሰሉ ችግር ከታች ጀምሮ ያለ ነው፡፡ በአንድ ሕፃን ልጅ ጉንጭ ውስጥ መዓት ጥሬ ከትቶ ከማስጨነቅ የማይለይ ትምህርት፣ በአራትና በአምስተኛ ክፍል ደረጃ ይሰጣል፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የአፍሪካ ተራሮችን መገኛና ከፍታ፣ የአፍሪካ ረግረጎችን፣ የአፍሪካ አገሮች ሕዝብ ቁጥርን (በገጠር፣ በከተማ፣ በዕድሜ በፆታ) መማር አለበት? 
ከክፍል ክፍል የሚሰጡት ትምህርቶች ደረጃ በደረጃ አንዱ በሌላው ላይ እየተገነባ ተማሪውንም መገንባት ይኖርበታል፡፡ የዚህ ዓይነት አወቃቀር የሌለውና ፈተና ስለሚመጣ ብቻ ተጠንቶ ከፈተና በኋላ ወዲያው የሚረሳ ትምህርት ከትምህርት አይቆጠርም፡፡ መረሳት የሌለበት ትምህርት ከተማሪው የዕውቀት ቅርስ ውስጥ ሊቆይ በሚችልበት አኳኋን መተላለፍ፣ በተለያየ የጥልቀት ደረጃ መመላለስና መገንባት ይኖርበታል፡፡ 
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር