ዩኒቨርስቲው የፍሎራይድ ኬሚካልን ከመጠጥ ውኃ ማጣራት የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ አገኘ

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከስፔን ብሔራዊ የምርምር ምክር ቤት /CSIC/ጋር በመሆን ውኃ ውስጥ ያለውን የፍሎራይድ ኬሚካል ዚዮላይት በተሰኘ ንጥረ ነገር ማጣራት የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ማግኘቱን አስታወቀ።

የቴክኖሎጂ ግኝቱም ከአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባለቤትነት መብት ተሰጥቶታል።
በዩኒቨርስቲው የዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር መንገሻ ማሞ እንዳሉት፥ የቴክኖሎጂ ግኝቱ ዩኒቨርስቲው የሚያደርገው ችግር ፈቺ የምርምር ሥራ አካል ነው።
በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ክፍል የሚገኘው የከርሰ ምድር ውኃ ከፍተኛ መጠን የፍሎራይድ ኬሚካል እንዳለው የገለጹት ዶክተር መንገሻ፥ ይኸው ኬሚካል በሰው ጥርስና አጥንት ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸዋል።
ፍሎራይድ በተፈጥሯዊ ስነ-ምህዳር ከሚመነጩ ኬሚካሎች አንዱ ሲሆን ከመጠን ያለፈ ፍሎራይድ በመጠጥ ውኃ አማካኝነት ሲወሰድ በሰዎች ጤንነት ላይ በተለይም በጥርስና አጥንት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትልም ነው  ዳይሬክተሩ  ያስረዱት።
የዓለም የጤና ድርጅት የጥርስ ፍሎሮሲስን ለመቀነስ እንደ አካባቢው የሙቀት መጠን ቢለያይም በአንድ ሊትር ውኃ የፍሎራይድ መጠን ከ 0 ነጥብ 5 እስከ 1 ነጥብ 5 መብለጥ እንደሌለበት ይመክራል።
የቴክኖሎጂ ግኝቱ ተግባር ላይ ሲውል በአገሪቱ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚኖሩ 14 ሚሊዮን ነዋሪዎች ከፍሎራይድ ነፃ የሆነ ንጹህ የመጠጥ ውኃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ፍሎራይድን ለማጣራት የሚውለው ዚዮላይት የተሰኘው ንጥረ ነገር በአገር ውስጥ ከሚገኙ አለቶች በስፋት ማግኘት የሚቻል በመሆኑ በአነስተኛ ወጪ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የውኃ ማጣራቱ ሂደት ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አመልክተዋል።
በተያያዘ ከዩኒቨርስቲው የሚወጡ አዳዲስ ምርምሮችና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢንዱስትሪዎች ለማድረስና የኅብረተሰቡ ችግር እንዲፈቱ ለማስቻል ከዘርፉ ንግድና ማኅበራት ምክር ቤት ጋር ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር