በሃዋሳ ከተማ የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ለመፍቀድ በወጣው ጨረታ ተወዳዳሪ መታጣቱ ተሰማ

ዜናው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው
-ለሐዋሳና ባህር ዳር ለወጣው ጨረታ ተወዳዳሪዎች አልቀረቡም
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚሠራጭ የንግድ (የግል) ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ አገልግሎት ባወጣው ጨረታ ተሳትፈው ላሸነፉ ድርጅቶች ዛሬ ፈቃዳቸውን ይሰጣል፡፡
ባለሥልጣኑ ለአዲስ አበባ ከተማ፣ ለባህር ዳር ከተማና ለሐዋሳ ከተማ የግል ሬዲዮ ጣቢያ ለመፍቀድ ጨረታ ያወጣ ቢሆንም፣ ለባህር ዳርና ለሐዋሳ ቀርቦ የሚወዳደር ድርጅት አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ለአዲስ አበባ ለሚፈቀደው 102.9 ኤፍኤም ሬዲዮ ለውድድር የቀረቡት ሦስት ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከቀረቡት ሦስት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ‹‹እግር ኳስን በሬዲዮ ይመልከቱ›› በሚል በፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት 98.1 ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ላይ እየሠራ የሚገኘው አቶ መሰለ መንግሥቱ ድርጅት መሆኑ የተጠቆመው ‹‹ዓባይ›› የተባለው ድርጅት አሸናፊ ሆኗል፡፡
ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ሌላ ተጨማሪ ጣቢያ ለመስጠት በድጋሚ ባወጣው ጨረታ ሁለት ተጫራቾች ብቻ ቀርበዋል፡፡ ከሁለቱ ተጫራቾች ብሥራት የተባለ ድርጅት ኤፍኤም 101.1 ሬዴዮ ጣቢያን ማሸነፉ ታውቋል፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 533/99 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያወጣውን የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችን አሸናፊ ተወዳዳሪዎች ድርጅቶች ዛሬ ፈቃዳቸውን እንደሚያስረክብ አስታውቋል፡፡
በጨረታው አዲስ ስቴይለር፣ አዲካ ኢቨንት ኤንድ ኮሙዩኒኬሸን፣ አክሱም ፒክቸርስ (ኢትዮፒካ ሊንክ) እና ሌሎችም ሁለት ድርጅቶች የተሳተፉ ቢሆንም፣ ማሸነፍ አለመቻላቸው ተጠቁሟል፡፡ 
በጨረታው ለመሳተፍ የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችና ስለጨረታው አከፋፈት ማብራሪያ እንዲሰጡ የባለሥልጣኑን የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፍን ከሪፖርተር ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ለአሸናፊዎቹ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት ምንም የሚናገሩት እንደሌለ በመግለጽ ምላሸ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር