የዲያስፖራውን ሙሉ መረጃ አጠናቅሮ መያዝ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ይገባል-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 23/2006 ዲያስፖራው በአገሩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ በስፋት እንዲሳተፍና በሚኖርበት አገር ሁሉ መብቱን ማስከበር እንዲችል የዲያስፖራውን ሙሉ መረጃ አጠናቅሮ መያዝ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም ጋር በመተባበር ከ20 በላይ ከሚሆኑ ኤምባሲዎች ለተውጣጡ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች "ዲያስፖራውን ማወቅ" በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ስልጠና እየሰጠ ነው።
በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደዋኖ ከድር እንደተናገሩት የዲያስፖራውን ሙሉ መረጃ በማወቅ በአገሩ ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ማድረግ ይገባል።
ከአሁን በፊት የነበረው አሰራር የዲያስፖራውን መገኛ ቦታ ብቻ በማወቅ ላይ የተመሰረተ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደዋኖ እንዳሉት ዲያስፖራውን ከአገሩ ልማት ጋር ማቆራኘት እንዲቻል የአሁኑ ስልጠና ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው አገሮችን ልምድ ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል።
ለአሁኑ ስልጠና እንዲሳተፉ የተጋበዙ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በስፋት ከሚገኙበት አገራት እንደመሆኑ መጠን ስልጠናውን ጨርሰው ወደመጡባቸው አካባቢዎች ሲመለሱ ዲያስፖራውን በማስተሳሰሩ ረገድ ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተልዕኮ የኢትዮጵያ ኃላፊ ሚስተር ጆሲያህ ኦጊና እንዳሉት ድርጅቱ የምሁራንን ፍልሰት ለመግታትና የስደተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን ይሰለፋል።  
ከውጭ ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያንም አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ በማገዝና ጊዜያዊ የቁሳቁስ አቅርቦት በማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
ዲያስፖራው ለአገሩ ልማት ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብና ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ያለች አገር በመሆኗ ዲያስፖራው በስፋት ወደአገሩ እንዲመጣ በማድረጉ ረገድም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ለመስራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዲያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ፈይሳ አሊይ እንዳሉት በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች የአገሪቱን ገፅታ በማስተዋወቅና ለአገሪቱ ገቢ በማስገኘቱ ረገድ የማይናቅ ሚና እየተጫወቱ ነው።
ይህን እንቅስቃሴ በእውቀት ላይ በመመስረት በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ለመምራትና ለማነቃነቅ ዲያስፖራውን በጥልቀት ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ፈረንሳይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲያስፖራዎች ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት የስልጠናው ተሳታፊ አቶ በሪሁን ደጉ እንዳሉት ስልጠናው የዲፕሎማቶችን አቅም በማሳደግ የዲያስፖራዎችን መረጃ አጠናቅረው እንዲይዙ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ከአሁን በፊት የዲያስፖራዎችን መረጃ በተበጣጠሰ መልኩ ሲሰበስቡ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ በሪሁን የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችል የእውቀትና የገንዘብ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2ነጥብ 5 እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በተለያዩ አገራት እንደሚኖሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ዜናው የኢዜኣ ነው

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር