በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ በመፍጠር ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት መከሩ

በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ በመፍጠር ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል በሃይማኖት ተቋማት ሚና ላይ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የሃይማኖት ተቋም የሁለት ቀን የምክክር ጉባኤ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ መከካል የደቡብ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ የሲዳማ፣ የቡርጂና ጌድኦ ሀገር ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ሀብተማርያም ገብረመስቀል እንደተናገሩት ያለስነ ምግባር የሚካሄድ ማንኛውም ስራ ሂደቱ አስቸጋሪ ውጤቱም አስከፊ በመሆኑ በስነ ምግባር የተገነባ ዜጋ ለመፍጠር ከሃይማኖት ተቋም አባቶች ብዙ ይጠበቃል፡፡
የአከባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ለሰው ልጆች ምቹና ተስማሚ የመኖሪያ ስፍራ ለመፍጠር፣ልማትን ከሙስና ማጽዳት፣ ስራን ከስህተትና ከጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉ የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮቻቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ጉባኤው በስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራትና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት እንዲሁም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ግልፅ አቅጣጫ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
የደቡብ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዜዳንትና የሃይማኖት ተቋማት ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ ሚፍታህ ሰኢድ በመከባበርና በሰላም አብሮ በመኖር የሚያምኑ፣በልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሀገራዊ ሃላፊነት መሸከም የሚችሉ ዜጎችን የማፍራት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ጠንካራ የስራ ባህል ያላቸው፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ከማንኛውም ጥገኛ ልማድ ነፃ የሆኑ ፣ ኃላቀር አስተሳሰቦችን በመዋጋት እውቀትን የመሻት ዝንባሌ የተላበሱ ወጣቶችን ለማፍራት ከሃይማኖት ተቋማት ብዙ የሚጠበቅ በመሆኑ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
የሀዲያ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ አበበ የምክክር መድረኩ መንግስት ፆታዊ ጥቃትን በማስወገድ የሴቶችን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማስፋፋትና ለቀጣይ ስራ ከፍተኛ አቅም የተገኘበት ነው ብለዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ባወጣው የአቋም መግለጫ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የፆታ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን በሙሉ አቅም መደገፍና ማቋቋም፣ተጠቃዎች ተገቢ ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ፣በህብረተሰቡ ዘንድ የቤተሰብ የምክክር መድረክ ማመቻቸት ስራ ላይ ለመረባረብ ቃል ገብተዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምምክር መድረክ ላይ ከ170 የሚበልጡ የክልልና ፌደራል የሃይማኖት ተቋም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና አባላት፣  የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዜናው በከፍል የኢዜኣ ነው

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር