የደመወዝ ጭማሪው የዋጋ ንረት እንደማያስከትል ግልጽ መደረግ አለበት!

የዋጋ ንረትን በተመለከተ ሰሞኑን ሁለት ተቀራራቢ የሆኑ ክስተቶች ተሰምተዋል፡፡ የመጀመሪያው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. የዋጋ ንረትን በማስመልከት ያወጣው ሪፖርት ሲሆን፣ ሁለተኛው
መንግሥት የዋጋ ንረትን በማይቀሰቅስ ሁኔታ ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ መወሰኑ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ለሠራተኛው ሕዝብ መልካም ብሥራት ነው፡፡ ነገር ግን የተጠና መሆን አለበት፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ሪፖርት እንደሚያሳየው በግንቦት ወር የአገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ንረት 8.70 በመቶ በማስመዝገብ፣ በመላ አገሪቱ ባለፉት 15 ወራት የዋጋ ንረቱ በነጠላ አኃዝ እንደቀጠለ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ እ.ኤ.አ. ከማርች 2013 ጀምሮ በነጠላ አኃዝ መቀጠሉን ለመንግሥት እንደ ስኬት እንደሚታይ ሪፖርቱ ያብራራል፡፡ የዋጋ ንረቱ በነጠላ አኃዝ መቀጠሉ አዎንታዊ ገጽታ ነው፡፡
ይሁንና መንግሥት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ እጨምራለሁ ሲል ያቀረበው ታሳቢ ጭማሪው የዋጋ ንረት የማያስከትል መሆኑን ነው፡፡ ጥያቄ የሚነሳውም እዚህ ላይ ነው፡፡ የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ የዋጋ ንረት እንደማይባባስ የሚደረገው ምን ዓይነት ዕርምጃዎችን ወይም መለኪያዎችን በማሰብ ነው? ለመንግሥት ሠራተኞች የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ ኢኮኖሚው ተረጋግቶ መቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ተጠንቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ መንግሥት መወሰኑ ተገልጿል፡፡ ይህ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ጥያቄ ደግሞ መነሳቱ የግድ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ንረት እስከ 40 በመቶ ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የኅብረተሰቡን ኑሮ በምን ያህል ደረጃ አመሰቃቅሎት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ የዋጋ ንረቱ አሁን በነጠላ አኃዝ ላይ ቢገኝም የዚያን ጊዜው ቁስል እስካሁን ድረስ አልሻረም፡፡ ከመደበኛው የዋጋ ንረት በተጨማሪ ሰው ሠራሽ የሚባለው የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ሥፍራ አለው፡፡ ይህ በዋጋ ግሽበት ጠባቂነት ባህሪ (Inflation Expectation ምክንያትምበገበያው ውስጥ የሚከሰት የዋጋ ንረት በተደጋጋሚ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ 
መንግሥት ለሠራተኞቹ ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ የዋጋ ንረትን እንደማያባብስ ሲያስታውቅ ለሕዝቡ በግልጽ ማስረዳት አለበት፡፡ ገበያው በጠባቂነት ባህሪ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ የደመወዝ ጭማሪም ይባል ማስተካከያ የራሱን ተፅዕኖ ይዞ ይመጣል፡፡ ደመወዝ ተጨመረ ሲባል ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ወገኖች (በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ ለውጥ ባይኖርም) ገበያ ውስጥ ይመጣል ብለው የሚያስቡትን ለውጥን በማስላት ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ የመኖሪያ ቤቶችን የሚያከራዩ ሰዎች በአንድ በኩል ተከራዮቻቸው የደመወዝ ጭማሪ ተደርጎላቸዋል በሚል እሳቤ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ መጨመሩ አይቀርም በሚል ግምት የኪራይ ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ምንም እንኳን የደመወዝ ማሻሻያው በተጨባጭ በፍላጎትና በአቅርቦት ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ባያመጣም፣ ማሻሻያው ግሽበትን ያባብሳል ብለው የሚጠብቁ የገበያ ተዋናዮች ሰው ሠራሽ ግሽበት እንዲቀሰቀስ አደረጉ ማለት ነው፡፡ ገበያው የጠባቂነት ባህሪ ተላብሷል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ 
የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ተደርጎላቸው መልሰው ለዋጋ ንረት የሚያስረክቡት ከሆነ ጭማሪው ትርጉም አልባ ስለሚሆን፣ መንግሥት በተጨባጭ የዋጋ ንረት እንደማያጋጥም ማረጋገጫ መስጠት አለበት፡፡ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ያገኘው ጭማሪ በሕይወቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የማያመጣለት ከሆነ ጭማሪው ፋይዳ አይኖረውም፡፡ አረፋ የመጨበጥ ያህል ይሆንበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለውጤታማ ሥራ አገር አቀፍ ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው በማለት የደመወዝ ጭማሪውንና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሲያበስሩ፣ የመንግሥት ሠራተኞች በሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት እንዳይመቱም ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡
ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት የዋጋ ንረቱን ከድርብ አኃዝ ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አስታውቋል፡፡ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱንም አስረድቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል እንደ ስንዴና ዘይት የመሳሰሉ ምርቶችን በመደጎም፣ ዱቄትና አንዳንድ እህሎች ላይ የነበረውን ታክስ በመቀነስና በማንሳት፣ እንዲሁም በዋጋ ንረት ላይ ይታይ የነበረውን ፈታኝ ሁኔታ በማርገብ ጥረቶች መደረጋቸውን አመልክቷል፡፡ 
በእነዚህ ሁሉ ጥረቶች ተገኝቷል የተባለው ተስፋ ሰጪ ባለአንድ አኃዝ የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀጠለ መሄድ ሲገባው ወደ ኋላ ከተመለሰ አደጋ አለው፡፡ ገበያው የጠባቂነት ባህሪ ስላለው በደመወዝ ጭማሪው ምክንያት ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት መከሰቱ አይቀርም፡፡ ገንዘብ የያዙ ሰዎች ወደ ገበያው በስፋት በገቡ ቁጥር አቅርቦትና ፍላጎት ስለማይጣጣሙ የዋጋ ንረት ይቀሰቀሳል፣ ገበያውም በዋጋ ንረት ይመታል የሚል የተለመደ እሳቤ ስላላቸው በብዛት ምርቶችን ለመሸመት ሲንቀሳቀሱ ሰው ሠራሽ ጭማሪዎች ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ የተለመደ የገበያ ባህሪ ነው፡፡ 
መንግሥት የሚያደርገው የደመወዝ ጭማሪ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ማሰብ ያለበት ይህንን የገበያ የተለመደ ባህሪ ነው፡፡ የደመወዝ ጭማሪው ኢኮኖሚው ተረጋግቶ በሚቀጥልበት ሁኔታ ተጠንቶ ተግባራዊ ይሆናል ሲልም ጥናቱ ምን እንደሆነ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በማሰብ በተወሰኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ጣሪያ ሲቀመጥ የተፈጠረውን ውዝግብና ውጤቱን እናስታውሰዋለን፡፡ በዚያ ውሳኔ ምክንያት የደረሰው ቀውስ እስካሁን ድረስ አሻራው አለ፡፡ 
ስለዚህ መንግሥት የዋጋ ንረት ሳይባባስና ኢኮኖሚው ተረጋግቶ ይቀጥላል ከሚለው መግጫው ባሻገር የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ምክር እንደ ግብዓት ለመጠቀም ፍላጎቱን ማሳየት አለበት፡፡ የዋጋ ግሽበት ጠባቂነት ባህርይ የተፀናወተው የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ፈር እንዲይዝና የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ ዓላማውን እንዲያሳካ ከተፈለገ፣ መንግሥት የዋጋ ንረት እንደማይከሰት አመላካች ነገሮችንና የፖሊሲ ዕርምጃዎችን ማሳየት የግድ ይለዋል፡፡ የደመወዝ ጭማሪው በዋጋ ንረት የሚመታ ከሆነ ልፋቱ በሙሉ ገደል ይገባል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የዋጋ ንረት የማያጋጥም መሆኑን አመላካቾችን የማሳየት ኃላፊነት አለበት!

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር