የኮሪያ መንግሥት ለሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ የፈቀደው ብድር ለፓርላማ ቀረበ

ከሞጆ-ሐዋሳ የመጀመሪያ ዙር የፍጥነት መንገድ ግንባታ የኮሪያ መንግሥት ኤግዚም ባንክ የፈቀደው 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለፓርላማ ቀረበ፡፡
የሞጆ-ሐዋሳ መንገድ 201 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ግንባታው በሁለት ዙር ተከፍሎ የሚገነባ ነው፡፡ የጀመሪያው ዙር ግንባታ ከሞጆ-ዝዋይ በራሱ በሁለት ተከፍሎ የሚገነባ መሆኑን የብድር ማፅደቂያ አዋጁ አባሪ ሰነድ ያብራራል፡፡ የመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ምዕራፍ ከሞጆ-መቂ ሲሆን፣ ለዚህ ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል 128 ሚሊዮን 460 ሺሕ ዶላር በዚህ ዓመት ከአፍሪካ ልማት ባንክ መገኘቱን ሰነዱ ያብራራል፡፡
ለቀሪው የመቂ-ዝዋይ መንገድ ግንባታ ደግሞ የኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት (ኤግዚም) ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር መፈረሙን የአዋጁ አባሪ ይገልጻል፡፡
ከሞጆ-ሐዋሳ ድረስ የሚገነባው የፍጥነት መንገድ በአንድ ጊዜ አራት ተሽከርካሪዎችን እንዲያስተናግድ ይፈለጋል፡፡ አጠቃላይ ወጪውም 349 ሚሊዮን 480 ሺሕ ዶላር መሆኑን ሰነዱ ይገልጻል፡፡ 
ከኮሪያ መንግሥት የተገኘው 100 ሚሊዮን ዶላር የ15 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
ለፕሮጀክቱ ትግበራ ባንኩ በሚፈጽመው ክፍያ ላይ 0.1 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ከብድሩ ገንዘብ ላይ ተቀንሶ እንደሚከፈል፣ ጥቅም ላይ ባልዋለውና ባልተከፈለው የብድር ገንዘብ ላይ ደግሞ 0.01 በመቶ ወለድ እንደሚታሰብበት ረቂቅ ማፅደቂያ አዋጁ ይገልጻል፡፡
የብድር ስምምነቱ እስከዛሬ ከነበሩት የብድር ዓይነቶች ጋር ሲነፃፀር የ55 ዓመት መሆኑ፣ የአገልግሎት ክፍያውና ወለዱ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ የፓርላማው አባላትን አስደንቋል፡፡ ‹‹የኮሪያ ኤግዚም ባንክ ብድር ሳይሆን ስጦታ ነው የሰጠው፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ ዶ/ር አድሃና ኃይሌ አድንቀውታል፡፡
በማከልም የብድር ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጁ በቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ በቀጥታ ቢፀድቅ መልካም እንደሆነ ዶ/ር አድሃና ቢገልጹም፣ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል በመጀመሪያ ንባብ እንዲፀድቅ በመንግሥት በኩል ዝግጅት ባለመደረጉ ቢመራ ችግር የለውም በማለታቸው፣ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ አዲስ አበባን በቀጥታ ከኬንያ ሞምባሳ ከተማ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ የአውራ ጎዳና አካል ነው፡፡ በመሆኑም ከሐዋሳ-ሞያሌ የሚያመራው አውራ ጎዳና የሞጆ-ሐዋሳ መንገድ መጠናቀቅን ተከትሎ የሚጀመር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
Source http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/6267-%E1%8B%A8%E1%8A%AE%E1%88%AA%E1%8B%AB-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%A5%E1%89%B5-%E1%88%88%E1%88%9E%E1%8C%86-%E1%88%90%E1%8B%8B%E1%88%B3-%E1%8B%A8%E1%8D%8D%E1%8C%A5%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%88%E1%8B%B5-%E1%8B%A8%E1%8D%88%E1%89%80%E1%8B%B0%E1%8B%8D-%E1%89%A5%E1%8B%B5%E1%88%AD-%E1%88%88%E1%8D%93%E1%88%AD%E1%88%8B%E1%88%9B-%E1%89%80%E1%88%A8%E1%89%A0

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር