የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ መጠን እስካሁን አልታወቀም


  • በየ3 አመቱ የደሞዝ ጭማሪ ሊደረግ ይችላል
  • ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች እንደሚጨመር የተነገረው የደሞዝ መጠን እስካሁን በይፋ አልተገለፀም፡፡ 


በሌላ በኩል ከአሁን በኋላ በየሦስት አመቱ ለመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ 
በሲቪል ሠርቪስ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ጌታቸው አብዲሣ፤ በቅርቡ መንግስት ይጨመራል ብሎ ከሰጠው መረጃ ውጪ በምን ያህል ፐርሰንት እንደሚጨመር መረጃ አልደረሰንም ብለዋል፡፡ 

ለመንግስት ሠራተኞች ለመጨረሻ ጊዜ ደሞዝ የተጨመረው በታህሳስ ወር 2003 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ ከ38.75 በመቶ እስከ 44.71 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን አሁን ከዚያ በላይ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚጠበቅ በግል ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ መስፍን ይልማ ግምታቸውን ሰንዝረዋል። የደሞዝ ጭማሪው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግስት ደሞዝተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል - ምሁሩ፡፡  የደሞዝ ጭማሪ ስሌቱ አለመታወቁ ትንታኔዎችን ለመስጠት ያስቸግራል ያሉት መምህሩ፤ እስከዛሬ በመንግስት በኩል የሚደረጉ የደሞዝ ጭማሪዎች የሠራተኛውን ፍላጐት አርክተው አያውቁም፤ ይኸኛውም ጭማሪ የተለየ ነገር ይዞ አይመጣም ብለዋል፡፡ 

ባለፉት አምስት ዓመታት በፓርላማ ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ የደሞዝ ጭማሪው አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጭማሪው አንዲት ሣንቲም እንኳ ቢሆን በሠራተኛው ህይወት ላይ ለውጥ ባያመጣም ትርጉም አለው ይላሉ፡፡ 

መንግስት መቼውንም ቢሆን የሠራተኛውን ፍላጐት ሊያሟላ የሚችል ደሞዝ የመጨመር አቅም አይኖረውም ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ አንድ የመንግስት ሰራተኛ የሚመራው ኑሮ ሊስትሮ ከሚሰራ ሰው በታች እንደሆነ ጠቅሰው፤ መንግስት ይሄን የሰራተኛውን ህይወት መለወጥ የሚችል ጭማሪ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ፍጆታን ከማሟላት አልፎ ለቁጠባ የሚተርፍ ገቢ ከጭማሪው ሊያገኝ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡  

የደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ የዋጋ ንረት ሊከሰት ይችላል የሚለውን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ግርማ፤ ስጋቱ ከተሳሳተ አመለካከት የመነጨ ነው ብለዋል፡፡ ነጋዴው ደሞዝ ስለተጨመረ ተመካክሮ ዋጋ የመጨመር አቅሙም ፍላጐቱም የለውም የሚሉት የፓርላማ አባሉ፤ ችግሩ የሚፈጠረው ደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ ሠራተኛው የመግዛት ፍላጐቱ ማደግ ሲጀምር ነው ብለዋል፡፡ የመግዛት ፍላጎቱ ሲያድግ በአቅርቦትና ፍላጐት መካከል አለመመጣጠን ይፈጥራል፤ ስለዚህ መንግስት አቅርቦቱን ማሳደግ አለበት ባይ ናቸው፡፡

የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ በነጋዴው የሚፈጠር ሣይሆን በመንግስት ሠራተኛው ፍላጐትና በአቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት አልጣጣም ሲል የሚከሰት ነው ብለዋል አቶ ግርማ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢህአዴግ ተወካይ የሆኑ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ በበኩላቸው፤ ከ300 ብር ጀምሮ ጭማሪ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ጭማሪው በመንግስት ሠራተኛው ህይወት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ የደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ የሸቀጦች ዋጋ ንረት እንዳይከሰት መንግስት ተገቢውን ቁጥጥር ያደርጋል ሲሉም እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡    በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት የሚሰሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ፤ የደሞዝ ጭማሪው መታሰቡ በራሱ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፤ ፍላጎትን ሊያሟላ የሚችል ጭማሪ ይደረጋል የሚል ግምት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡ 

የደሞዛቸው መጠን 3690 ብር መሆኑን የጠቆሙን እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ ከዚህ በላይ ለህዳሴው ግድብ ቦንድ ግዢ የሚቆረጠውን ጨምሮ ለመንግስት ገቢ ግብር፣ ለጡረታና ለጤና ዋስትና ለመሳሰሉት ተቆራርጦ 2500 ብር ገደማ በወር እንደሚያገኙ ይገልፃሉ፡፡ 

በዚህ ደሞዛቸው የቤት ኪራይ ከፍለው፣ የወር አስቤዛ ሸምተው፣ የትራንስፖርት ቆርጠው፣ ለቤት ቁጠባ ከፍለው ስለማይበቃቸው በአብዛኛው ከቀጣይ ወር ደሞዝ ብድር እንደሚወስዱ ይናገራሉ። “የአሁኑን የደሞዝ ጭማሪ በተስፋ እጠብቃለሁ” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ተርፎኝ በባንክ ለማጠራቀም ባይበቃኝ እንኳ ወር እስከ ወር ሳልሳቀቅ ለመኖር እፈልጋለሁ፤ እንደዚያም እኖራለሁ ብዬ በተስፋ እጠብቃለሁ” ይላሉ፡፡ 

በዚያው ሚኒስቴር መስሪያቤት በረዳት ግዢ ኦፊሠርነት ተቀጥረው የሚሰሩት ግለሰብ በበኩላቸው፤ የ2121 ብር ደሞዝተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በወር የህዳሴ ግድብ ቦንድን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ተቆራርጦ ወደ 1300 ብር ገደማ እጃቸው ላይ እንደሚደርስ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ገንዘብ ከባለቤታቸው ጋር በመተጋገዝ ሁለት ልጆቻቸውን እንደሚያሳድጉ ጠቁመው ጭማሪው በገቢያቸው ላይ ጉልህ ለውጠ ያመጣል የሚል ግምት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ 

የደሞዝ ጭማሪው ተግባራዊ የሸቀጦች ዋጋ፣ የቤት ;መራይ፣ የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ የመሳሰሉት በዚያው ልክ ዋጋቸው ይጨምራል ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ ጭማሪው መሰረታዊ የኑሮ ለውጥ አያመጣም ብለው እንደሚገምቱ ገልፀዋል፡፡ 
“ጭማሪው ምንም ያህል ቢሆን ኑሮአችንን ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አይታደገውም” የሚሉት የመንግስት ሠራተኛዋ፤ መንግስት ዝቅተኛ ደሞዝ ለሚያገኙ ሰራተኞች ከሌላው በበለጠ የደሞዝ ማስተካከያ ቢያደርግ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል። 
ወሬው የኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ ነው

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር