ሰንሻይን ሦስተኛውን የማሪዮት ሪዞርት ሆቴል በሐዋሳ ሊገነባ ነው

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከማሪዮት ኢንተርናሽናል ጋር በፍራንቻይዝ ስምምነት ሦስተኛውን የማሪዮት ሪዞርት ሆቴል ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ሊገነባ ነው፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ እየተገነቡ ካሉት ሁለት ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ አንደኛውን ከስድስት ወራት በኋላ እንደሚያስመርቅ ተገለጸ፡፡
በሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው በሰንሻይን ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሦስተኛውን ማሪዮት ሪዞርት ሆቴል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል ተብሏል፡፡ 
ለሐዋሳ ማሪዮት ሪዞርት ሆቴል የመሠረት ድንጋይ ባለፈው እሑድ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬና የሐዋሳ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በተገኙበት ተቀምጧል፡፡ የሐዋሳው ማሪዮት ሪዞርት ሆቴል ስዊት ቪላዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎችና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎችንም ያካተተ ነው፡፡
የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ እንደገለጹት፣   ማርዮት ሪዞርት ሆቴልን በሐዋሳ ለመገንባት የወሰኑት ሐዋሳ ከተማ እያሳየች ካለው ዕድገትና በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከተማዋ ልታሳይ የምትችውን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ከግምት በማስገባት ነው፡፡ 
አቶ ሳሙኤል ሐዋሳን ለምን እንደመረጡ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ሐዋሳ ከሌሎች ከተሞች በተሻለ እያደገችና በተደጋጋሚ ምርጥ ከተማ በመባል ተሸላሚ መሆኑዋ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ እንዲሁም የከተማዋ ኢንቨስትመንት ዕድገትና በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከተማዋን የሚያቋርጠው የፈጣን መንገድ ግንባታ የሚጠናቀቅ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ የሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያና ሐዋሳን የሚያቋርጠው የባቡር መስመር ግንባታም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚጠናቀቅ በመሆኑ ሐዋሳን ሊመርጡ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
የዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ደግሞ የሐዋሳ ከተማን አጠቃላይ ይዘት በመቀየር ከፍተኛ የቢዝነስ እንቅስቃሴ የሚኖራት ስለሚያደርጋት፣ ከአሁኑ እንደ ቢዝነስ ሰው ይህንን በማሰብ  ጭምር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የሐዋሳውን ሪዞርት ሆቴል ለመገንባት ኩባንያቸው ከወሰነ ሁለት ወራት ሳይሞሉ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውንም አቶ ሳሙኤል በአድናቆት ገልጸዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ለግንባታ የሚፈልጉትን 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በፍጥነት መስጠቱ፣ ‹‹ትክክለኛ የኢንቨስትመንት አቀባበል›› እንደሆነ በመግለጽ ይህንን ዕድል ሌሎችም እንዲያገኙት ተመኝተዋል፡፡ 
ለሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ቦታውን በቶሎ መስጠት ተገቢ እንደነበር ያመለከቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ፣ ‹‹ሰንሻይን እዚህ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ መጠየቁን ስንሰማ ያለምንም ማንገራገር አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ ወስነናል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ያደረጉት የጎላ ሥራዎቹን በመመልከት እንደሆነ በመጥቀስ ነው፡፡ የሐዋሳ ከንቲባ አቶ ዮናስ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ሐዋሳ የሚመጣውን የቱሪስት ፍሰት ለመሸከም የሚችል ዓለም አቀፍ ሆቴል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻን ተከትሎ ለሆቴል ለሪዞርትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ መዝናኛ ቦታዎች ግንባታ የሚሆን ቦታ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ፍላጎት ያለው ካሁኑ ቦታውን ለመውሰድ የሚችል መሆኑን ያመለከቱት የከተማው ከንቲባ፣ ከሐዋሳ ዕድገት አንፃር ይህንን ቦታ ቀድሞ መውሰድ ብልህነት ነው ብለውታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የማሪዮት ኢንተርናሽናልን ስያሜ በመውሰድ በአዲስ አበባ በሁለት የተለያዩ ቦታዎች እየተገነቡ ያሉትና በሐዋሳ ለመገንባት የታቀደው ሆቴልና ሪዞርት ጠቅላላ ወጪያቸው አሁን ባለው ደረጃ ባይታወቅም፣ በአነስተኛ ግምት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ከኢንቨስትመንት ግሩፑ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል የተባለውና በመስቀል አደባባይ አካባቢ እየተነገባ ያለው ማሪዮት አፓርትመንት ሆቴል፣ ግንባታው በሚቀጥለው ህዳር 2007 ዓ.ም. አጠናቆ አገልግሎት ይጀምራል፡፡ 
በተመሳሳይ ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ የሚገነባው ባለአምስት ኮከቡ የማሪዮት ሆቴል ግንባታው በመፋጠን ላይ ነው ተብሏል፡፡ ከማሪዮት ኢንተርናሽናል ሆቴል ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት በጋራ የሚሠራው ሰንሻይን የማሪዮት ሆቴልን ስያሜ ፍራንቻይዝ በማድረግ ነው፡፡
በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰንሻይን የሚገነቡት ሆቴሎችና ሪዞርቶች የሚተዳደሩት ማሪዮት ኢንተርናሽናል በሚመድባቸው ባለሙያዎች ነው፡፡ በፍራንቻይዝ ስምምነቱ ሦስቱም ሆቴሎች ከሚያተርፉት ትርፍ ሰንሻይን ለማሪዮት ኮሚሽን ይከፍላል፡፡  ለሆቴሉ የሚያስፈልጉትንም ባለሙያዎች የመመደቡ ኃላፊነት የማሪዮት ኢንተርናሽናል ነው፡፡  እንዲህ ባለው ስምምነት የሚደረግ ሥራ ከውጭ ለሚመጡ ቱሪስቶች ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያስተናግዱ አማራጭ ሆቴሎችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
ከሰማንያ ሰባት ዓመታት በፊት የተመሠረተው ማሪዮት ኢንተርናሽናል ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚገኘው በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ማሪዮት ኢንተርናሽናል በአሁኑ ወቅት በ80 አገሮች ውስጥ ከአራት ሺሕ በላይ ከመስተንግዶ ጋር የተያያዙ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በመያዝ እያስተዳደረ ሲገኝ፣ እነዚህ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ከ195 ሺሕ በላይ የማረፊያ ክፍሎች አሉዋቸው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት ቢዝነሶች እ.ኤ.አ በ2012 ከ11.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሲያገኝ፣ የተጣራ ትርፉ ደግሞ 571 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. የ2013 መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ማሪዮት ኢንተርናሽናል ሥር 199,929 ሠራተኞች አሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር