ስለ ሃዋሣ እና ዣ – ን – ዣ – ድ … ባ – ር

ስለ ሃዋሣ እና ዣ – ን – ዣ – ድ … ባ – ር


እግር ጥሎኝ… ውበትና ተፈጥሮን አድሎኝ… በፍቅርና በሃሴት ተፍነክነክ ብሎኝ… ደልቶኝ… ሞቆኝ… ምችት፣ ምችትችት ብሎኝ… የሐዋሳ ሰማይ ስር ከርሜ ነበር:: ሐዋሳ ፍቅር እንደሆነች ባየኋት ልክ የምታስደስተኝ… በኖርኩባት ልክ የምትናፍቀኝ… በሸሸኋት ልክ የምታስጨንቀኝ… መሽቶ በነጋ ቁጥር ነገን የምታስመኘኝ የስስት ከተማዬ ናት::
አይደለም አሁን እንዲህ በአስፋልትና በውስጥ ለውስጥ የኮብል ስቶን ንጣፍ አሸብርቃ ይቅርና አቧራ እየለበስን፣ በጠራራ ፀሃይ እየተጠበስን፣ የሞላልን ቀን በጋሪ፣ ያልሞላልን ቀን በኮቴ አሸዋውን በሲሊፐራችን እየዛቅን ስናዘግም እንኳ ለፍቅሯ ጥግ አልነበረኝም… ያን ደማቅ ሰማያዊ የታቦር ሃይስኩል ዩኒፎርም ራሳችን ላይ ጣል እንዳደረግን ጀላቲ እየመጠጥን… አሊያም ሸንኮራ እየጋጥን… ሲደላንም የማዘር ቤትን የ60 ሳንቲም አምባሻ እየጎመጥን… በላዩ ውሃችንን አንዳንዴም ʿሴሏችንንʾ እየጨለጥን ጎዳናውን ስንሸከሽከው እንኳ ለፍቅሯ ልክ አልነበረኝም…
እንዲህ እንደዛሬው በባጃጅ ሽር በሚባልበት ወቅት ይቅርና የጡረታ ዘመኗ ባለፈባት ድክሞ ሳይክል SOSን አልፌ ጥቁር ዉሃ ድረስ ስንተፋተፍ እንኳ ለፍቅሯ የሚያህላት አልነበረኝም!… ዛሬም የሰላምና የደስታ ጥጌ ሐዋሳ ናት!… ሐዋሳ ሰላም… ሐዋሳ ፍቅር!…
እናም የሲዳማን የቆጮ ምግቦችና የወተት አይነቶች እያጣጣምኩ፣ የቶኪቻውን (የዮሐንስ በቀለን) ጫምባላላ እየዘፈንኩ ሐዋሳ ከርሜ ነበር… ምንም እንኳ በዛ ያሉ የጭፈራ ዘፈኖች ቢኖሩም ጫምባላላን ግን እጅግ እወደዋለሁ… ከባህል አንፃር ደህና ትርጉም ስላለው ይሆን?!…ነሸጥ ስለሚያደርገኝ ይሆን?!… እንጃ ብቻ!… “አይዴ ጫምባላላ” … “አይዴ ጫምባላላ” … ማለት እጅጉን ያስደስተኛል …
♫… ሻፌቱ ሺቄና ጊሩ ማሲሬና
አይዴ ጫምባላላ ኢሌ ኢሌ… ♫
♫… ሲዳማ ጎባያ ሲዳማ አዋሳ
ስንቅ ይዤልሻለሁ ስምሽ እንዲነሳ
ቡርሳሜ ናፍቆኝ ስመለስ ሲዳማ
በሩቅ እየታየኝ የታቦሩ ግርማ… ♫
♫… ሌምቦ … ሌምቦ …
ሌምቦ ሌላ ሌምቦ …
ሌምቦ … ሌምቦ …
ሌምቦ ሌላ ሌምቦ… ♫
♫… አይዴ ጫምባላላ
አይዴ ጫምባላላ… ♫
ጫምባላላ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሆነው በፊቼ በዓል ማግስት የሚከበር እለት ሲሆን እለቱ ልጆች ˝አይዴ ጫምባላላ”… ˝አይዴ ጫምባላላ”… እያሉ በየቤቱ በመዞር የሚዘፍኑበት… የተዘጋጀላቸውን ባህላዊ ምግብ የሚመገቡበት… ከማንኛውም ስራ ነፃ የሚሆኑበት፣ የሚመረቁበትና የሚከበሩበት ዕለት ነው… በነገራችን ላይ የሲዳማ ብሔር የጨረቃን ኡደት መሰረት ያደረገ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር አለው… ፊቼ እና ጫምባላላም ከዚሁ ዘመን አቆጣጠር ጋር የሚያያዙ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓሎች ናቸው… በየአመቱ የፊቼ በዓል ሲሆንም በሐዋሳ ከተማ ወደ አሞራ ገደል በሚወስደው መንገድ ጀርባ ሃይቅ ዳር በተዘጋጀ ቦታ ላይ በዓሉ ይከበራል… እኛም ታድመን ኮምኩመነው ነበር… አቤት ደስ ሲሲሲልልል….!
እንዲያው እግረመንገዴን አነሳሁት እንጂ የተነሳሁትስ ስለ ሲዳማ ባህልም ሆነ ስለ ፊቼ ዘመን መለወጫ በዓል አከባበር ለማውራት አይደለም!… ይልቁንም ወደ አሞራ ገደል በሚወስደውና የአካባቢው ድባብ ሰላምን በሚያድሰው ጎዳና… የፊቼ በዓል በጀርባው በሚከበርበት ጎዳና… ሰላማዊ ውሎ ብሎም ነፍስን በሃሴት የሚሞላ ፀጥታ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ዘና ብሎ የእግር ጉዞ በሚያደርግበት ጎዳና… ፀጥ እረጭ ያለ የሰከነ ኑሮ የሚፈልግ ሰው ቤት ኪራይ በሚፈልግበት ጎዳና… በአካባቢው መኖሪያ ቤት ያለው ሰው ረጋ ብሎ አትክልቶቹ ዙሪያ ተቀምጦ ስሜቱን በሚያዳምጥበት ጎዳና… ማንም አካባቢውን የሚያውቀው ግለሰብ ስለፀጥታው ሰላማዊነት በሚመሰክርበት በአሞራ ገደል ጎዳና ላይ በዴርቶጋዳው ደራሲ በፊታውራሪ ይስማዕከ ወርቁ አማካኝነት ስለተከፈተው ዣንዣድ ባርና ሬስቶራንት ላወራ እንጂ …
ዣ – ን – ዣ – ድ … ባ – ር . . .
ስለ ዣንዣድ ባር ከሰማሁበት እለት ጀምሮ ልጎበኘው እጅጉን እፈልግ ነበር… በየጥጋጥጉ ጭፈራና መሸታ ቤት በበዛባት አገራችን ቢያንስ ደራሲ የሆነ ሰው የሚከፍተው ባር ነፍስን የሚያድስ… በሙዚቃ ምርጫው መንፈስን የሚያረካ… የንባብ ባህልን የሚያበረታታ… የህብረተሰብን ንቃተ ህሊና የሚያጎለብት እንደሚሆንም ቅንጣት ጥርጥር አልነበረኝም!… ብቻ ልጎብኘው እንጂ ያለኝን አክብሮትማ እገልጽለታለሁ ስልም አስቤ ነበር… 
ጫምባላላ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሆነው በፊቼ በዓል ማግስት የሚከበር እለት ሲሆን እለቱ ልጆች ˝አይዴ ጫምባላላ”… ˝አይዴ ጫምባላላ”… እያሉ በየቤቱ በመዞር የሚዘፍኑበት… የተዘጋጀላቸውን ባህላዊ ምግብ የሚመገቡበት… ከማንኛውም ስራ ነፃ የሚሆኑበት፣ የሚመረቁበትና የሚከበሩበት ዕለት ነው… በነገራችን ላይ የሲዳማ ብሔር የጨረቃን ኡደት መሰረት ያደረገ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር አለው… ፊቼ እና ጫምባላላም ከዚሁ ዘመን አቆጣጠር ጋር የሚያያዙ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓሎች ናቸው… በየአመቱ የፊቼ በዓል ሲሆንም በሐዋሳ ከተማ ወደ አሞራ ገደል በሚወስደው መንገድ ጀርባ ሃይቅ ዳር በተዘጋጀ ቦታ ላይ በዓሉ ይከበራል… እኛም ታድመን ኮምኩመነው ነበር… አቤት ደስ ሲሲሲልልል….!
እንዲያው እግረመንገዴን አነሳሁት እንጂ የተነሳሁትስ ስለ ሲዳማ ባህልም ሆነ ስለ ፊቼ ዘመን መለወጫ በዓል አከባበር ለማውራት አይደለም!… ይልቁንም ወደ አሞራ ገደል በሚወስደውና የአካባቢው ድባብ ሰላምን በሚያድሰው ጎዳና… የፊቼ በዓል በጀርባው በሚከበርበት ጎዳና… ሰላማዊ ውሎ ብሎም ነፍስን በሃሴት የሚሞላ ፀጥታ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ዘና ብሎ የእግር ጉዞ በሚያደርግበት ጎዳና… ፀጥ እረጭ ያለ የሰከነ ኑሮ የሚፈልግ ሰው ቤት ኪራይ በሚፈልግበት ጎዳና… በአካባቢው መኖሪያ ቤት ያለው ሰው ረጋ ብሎ አትክልቶቹ ዙሪያ ተቀምጦ ስሜቱን በሚያዳምጥበት ጎዳና… ማንም አካባቢውን የሚያውቀው ግለሰብ ስለፀጥታው ሰላማዊነት በሚመሰክርበት በአሞራ ገደል ጎዳና ላይ በዴርቶጋዳው ደራሲ በፊታውራሪ ይስማዕከ ወርቁ አማካኝነት ስለተከፈተው ዣንዣድ ባርና ሬስቶራንት ላወራ እንጂ …
ዣ – ን – ዣ – ድ … ባ – ር . . .
ስለ ዣንዣድ ባር ከሰማሁበት እለት ጀምሮ ልጎበኘው እጅጉን እፈልግ ነበር… በየጥጋጥጉ ጭፈራና መሸታ ቤት በበዛባት አገራችን ቢያንስ ደራሲ የሆነ ሰው የሚከፍተው ባር ነፍስን የሚያድስ… በሙዚቃ ምርጫው መንፈስን የሚያረካ… የንባብ ባህልን የሚያበረታታ… የህብረተሰብን ንቃተ ህሊና የሚያጎለብት እንደሚሆንም ቅንጣት ጥርጥር አልነበረኝም!… ብቻ ልጎብኘው እንጂ ያለኝን አክብሮትማ እገልጽለታለሁ ስልም አስቤ ነበር… 
“… ዴርቶጋዳ … ዴርቶጋዳ
እንነጠቃለን ከተጫነን ፍዳ
ማንም ሰው ላይመጣ እኛን ለመለወጥ
አናፈገፍግም አናቅማማም ለለውጥ
ያቀረቀርክበት አንገት ያስደፋህ ቀን
ነግቷል ብለህ ተነስ ፍዳና ሰቀቀን …”
እኒህንና መሰል የለውጥ ግጥሞችን የጻፈ ገጣሚ… የወጣቱ መለወጥ የሚያንገበግበው ደራሲ… የከፈተው ባርማ በእርግጥም የሚበረታታ እንደሚሆን ለመገመት አላንገራገርኩም!… ነገሩ ግራ የገባኝና የተገላቢጦሽ የሆነብኝ ግን ገና ዣንዣድ የተባለውን ባር በራፍ ስረግጥ ነው …
ዣንዣድን የጎበኘሁት በማታ ነበር… በግምት ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ ይሆናል… ከአንዲት ሐዋሳ ከምትኖር ወዳጄ ጋር ነበርኩኝ… ገና ወደ ውስጥ እንደዘለቅኩ የዋት መጠኑ በውል ከማይታወቅ ʿትልቅ ሞንታርቦ እስፒከርʾ የሚለቀቅና የጆሮን ታምቡር የሚበጥስ ለዛ የሌለው ሙዚቃ ከሚሰነፍጥ ትንፋግ ጋር ተቀበለኝ… እንደምንም መቀመጫ አግኝተን እንደተቀመጥን…
እኔ: ˝እርግጠኛ ነሽ ግን ዣንዣድ ባር ይሄ ነው?!˝ ስል ወዳጄን በጥያቄ አጣድፋት ገባሁ… እስፒከሩ ሲያምባርቅብኝ የሳልኩት ዣንዣድ አፈር ከዲሜ ሲግጥብኝ ይሰማኛል …
ወዳጄ: “እንዴ አዎ ተረጋጋና በደንብ ተመልከተው እንጂ!”… ʿገና ምን አይተህ!… እኛም እንዲህ ነው የተሸወድነውʾ በሚል ቅላጼ!…
የወዳጄን ንግግር ተቀብዬ ዙሪያዬን ስቃኝ… መጽሃፍ ይዞ የቆመ ቅርጽ… የተለያዩ ደራሲዎችና ፈላስፎች ፎቶ… በቅርጽ የተሰራ ጣራ… አንዳች ነገር የተለበጠበት ግድግዳ… ድንግዝግዝ ያለ ክፍል… ብልጭ ድርግም የሚሉና የውስጥን ሰላም የሚያውኩ መብራቶች… ልጅነታቸው የሚያሳሳ ቢጢቆ ጉርድ የለበሱ ጨቅላ ሴት አስተናጋጆች (የትምህርት ቤት ዩኒፎርም የለበሱ የሚመስሉ)… ቅርጻ ቅርጾች… እና ወዘተ…. ነገሮችን ተመለከትኩኝ…
ʽርግጥ ቤቱ ያምራል… ለቤቱ ውበት የተሰጠው ግምትም ደስ ይላል… ብልጭ ድርግም የሚለው መብራትም የሆነ ቅርጽ እንዲሰራ የተፈለገ እንደሆነ ያስታውቃል… ምን አይነት ቅርጽ እንደሆነ የማይበትና የማገናዝብበት ትዕግስት ግን አልነበረኝም… ዴር33 ይሁን?!… ብቻ እንጃ!… በውስጠኛው ክፍል ያለማቋረጥ ብልጭ ድርግም ሲል ይታየኛል…
ወደ ውስጠኛው ክፍል ዘለቅኩ… ገና ስገባ የረበሸኝን አይነት ሁለተኛ ስፒከር እዚህም ከጣራ በላይ ያምባርቃል… እዚህም እዛም ወጣቶች ይደንሳሉ… ባንኮኒውን ከበው የሚጠጡም አሉ… የሚተሻሹ፣ የሚደባበሱ ጥንዶችም ይታዩኛል… መቀመጫ እንደሚልግ ዘወርወር አልኩና ወደነበርኩበት ወደ ሳሎኑ… ወደ ሶፋ መቀመጫዬ ተመለስኩ … ስቀመጥ ከበላዬ የጋሽ ስብሓት ምስል ይታየኛል…
ስሜቴ ተደበላለቀብኝ… የቤቱ ሁሉ ነገር አስጠላኝ… በዚህ ጥግ ካሸር… በዚያ ጥግ አልኮል ቀጂ… በሌላኛው ጥግ የጄኔሬተር ቤት… በአራተኛው ጥግ ሰላም የሚነሳ ስፒከር… በሌላኛው ክፍል ደሞ ሌላ ስፒከር… ደሞ ሌላ ረብሻ… ደሞ ሌላ መደነሻ… የሚያሳሱ አስተናጋጆች ብቻ ስብሰከሰክ የታዘዘችን አስተናጋጅ ምግቡንና መጠጡን እያቀራረበችልን ነበር… ጥያቄዬን አግተለተልኩላት…
እኔ: እኔ ምልሽ እናት በየት በኩል ነው ቤተ መጽሃፍቱ?
አሷ: እ…እ?!… እሱ እዚህ አይደለም ሌላ ቦታ ነው…
እኔ: ሌላ ቦታ?… የት?… (ሌላም ባር አለው ይሆን እያሰብኩ)…
እሷ: እ…እ? እኔጃ ግን አለ…
እኔ: እሺ እሺ … እዚህ ቤት ምንም የሚነበብ ነገር የለም?
እሷ: እ…እ?… የለም!…
እኔ: ሁሌም እንዲህ አይነት ሙዚቃ ነው የምትከፍቱት?
እሷ: እ…እ…?! አዎ!… ምነው ጥሩ አይደለም?… ዘፈን ላስቀይር?
እኔ: አይይ ትንሽ ድምፁ በዛ ብዬ ነው… እስቲ ቤቱ ምን የተለየ ነገር አለው?… አስጎብኚን?
እሷ: ?… ዋሻውን አይታችሁታል?… በውስጥ በኩልʿኮ ዋሻ አለ…
እኔ: አይ አላየነውም… ዋሻው ውስጥ መቀመጥ ይቻላል?
እሷ: አዎ!… እዛም ልትዝናኑ ትችላላችሁ… አሁን ግን ጨለማ ነው… (በድንገት መብራት ጠፍቶ ጄኔሬተሩ እያምባረቀብን ነበር)
እሺ: እሺ እናመሰግናለን . . . 
የተባለውን ዋሻ ላየው ብፈልግም ወደ ውስጥ መዝለቁ አስጠላኝ… ከቤቱ ድባብ ስነሳ ባየውም የተለየ ነገር ጠብ የሚልልኝ አልመስልህ አለኝ… ደግሞም የአስተናጋጇ ˝ልትዝናኑ ትችላላችሁ˝ አባባል አላስደሰተኝም… ደሞ ሌላ ብስጭት ራሴ ላይ መጨመር አልፈለግኩም… እናም ያለማቋረጥ በሚያባርቀው ሙዚቃ እየተደናቆርን ከወዳጄ ጋር መደማመጥ እስኪያቅተን እየተጯጯህን ማውራታችንን፣ መብላት መጠጣታችንን ቀጠልን… ሙዚቃውም ያለማቋረጥ ማንባረቁን ቀጠሏል… ትዝ ከሚሉኝ ዘፈኖች መካከል የሚከተሉት ቁርጥራጭ ግጥሞ ች ይገኙበታል . . .
111 …
♫… ኤሶ … ኤሶ
ኤሶ ኤሶ ጦና ናታ ወላይታ
ዱርሳ ዱርሳ … ወላይታ…♫ 
ዱርሳ ዱርሳ … ወላይታ …♫
♫… ኪኪያ ዳሞታ
አዋንዳይ አዋንዳይ… ♫
222 …
♫… ትብላው ብሬን
ትብላው ብሬን
ለኔስ ግድ የለም
ትብላው ብሬን… ♫ 
♫… Chop my money
… Chop my money
… Cuz I dont care…
… I don’t care… ♫
… I don’t care… ♫
333 …
♫… ሻላዬ ሻላዬ ዮ
ቴ ሻላዬ
ሻላይቱ ገላ ዮ
ቴ ሻላይ …♫
♫ … ዲላ ላይ… ዲላ ላይ… ዲላ ላይ…
ዲላ ላይ… ዲላ ላይ… ዲላ ላይ… ♫
♫… ኤ አና ዴስኮ
ኤ አና ዴስኮ… ♫
እኚህንና መሰል የጭፈራ ዘፈኖችን እየከፈቱ ለማደናቆር ለምን ያን የመሰለ ሰላማዊ መንደር እንደተመረጠ ሊከሰትልኝ አልቻለም… ለዚህ ለዚህማ እነ ከላይ… እነ ቁልቢ… እነ ፍቅረ ሰላም… እና ሌሎች መሰል ጭፈራ ቤቶች የተኮለኮሉበት በተለምዶ ቤርሙዳ ሰፈር የሚባለው የሐዋሳ የጭፈራ መንደር አይሻለውም ነበርን?!… የሰፈር ሰላም መንሳት ምን ይባላል?!… ድንቄም ደራሲ እቴ!… እንዲህም አድርጎ ለወገን ተቆርቋሪነት የለ!… ቆሽቴ እርር ድብን አለብኝ…
ሂሳባችንን ከፍለን ለመውጣት ተጣራሁ… ያቺው አንድ ፍሬ ልጅ የልጅ ፈገግታዋን ይዛ ከች አለች… ጥቂት ላወራት ፈለግኩ…
እኔ: እናመሰግናለን… እንደው በቀን ብንመጣስ ምን ምን አላችሁ?!
እሷ: ሁሉም ነገር አለን…
እኔ: ቆንጆ ቡና አላችሁ?
እሷ: ውይይ ትኩስ ነገር የለንም…
እኔ: እንዴ ለምን?! … ”ይሄኔ ነው መሸሽ”… 
እሷ: አይ ለጊዜው ማሽናችን ተበላሽቶ ነው ይኖረናል…
እኔ: እሺ እንደው መልዕክት ብነግርሽ ለደራሲውና ለቤቱ ባለቤት ታደርሺልኛለሽ?
እሷ: ኧረ አዎ
እኔ: አረቄ ቤት ለመክፈት ደራሲ መሆን አያስፈልግም!… የመንደር ሰላም ለመረበሽ መጽሃፍ መቸርቸር አያስፈልግም!… ድርጅትህን የደራሲ የደራሲ ልታደርገው የማትችል ከሆነ ዝጋው!… ለወገን በቃላት ጋጋታ ያሰቡ ከመምሰል በፊት በተግባር ማሳየቱ ይቀድማል… በይልኝ አደራ!… ትነግሪዋለሽ ግን?…
እሷ: እንዴ አዎ!… እንዲሻሻል አይደል እንዴ?!… ሂሳቧን እየተቀበለችን… በክብር እየተሰናበተችን… አሳሳችኝ… በግምት 20 ዓመት የማይበልጣት እምቡጥ ናት… የልጅነት ወዟን በከንቱ ስማቸውና ገንዘባቸው አሳስተው ከሚቀራመቷት ክፉ አይኖች አንድዬ እንዲጠብቃት እየተመኘሁ ወጣሁ… መልካም ይግጠምሽ የኔ እህት!!!

ከወዳጄ ጋር እያወጋን ተመለስን… እሷም እንደኔው የጠበቀችውና የገጠማት አልጣጣም ብሏት ከምርቃቱ ጊዜ ወዲህ ዝር ብላ እንደማታውቅ ነገረችኝ… ˝ዛሬም ያንተን ስሜት ማወቅ ስለፈልግኩ እንጂ ባልመጣ ደስታዬ ነበር˝… ስትል ብስጭቷን አጠናከረችልኝ 
እንደተብሰለሰልኩ አደርኩ… ግን ቆይ ምን አግብቶኝ ነው የምቃጠለው?! ታዋቂ ሆነ!… ዝናውን ቢዝነስ ማድረግ ፈለገ!… እናም ጠጪ እስካገኘ ድረስ… ከልካይ እስካልገጠመው ድረስ… ያሻውን እያደረገ የቻለውን ያህል ገንዘብ ቢያግበሰብስስ?!… ስል አሰብኩ… ብሽቅ ደራሲ!… በበኩሌ ከመጀመሪያው ዴርቶጋዳ በቀር ሌሎቹ የ ”ቶ” ዲስኩሮች ባዶ እንቶፈንቶ እንደሆኑብኝ ሳስብ የበለጠ አበገነኝ… በተለይ ዣንቶዣራ የተባለው ቁጥር 3 ዴርቶጋዳ ለአንባቢውም ሆነ ለጥበብ ያለውን ንቀት ደህና አድርጎ ያሳየበት የልጅ ጨዋታ እንደሆነ ሲታወሰኝ ˝ድሮም ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃምየምትለኝ አያቴ ታወሰችኝ… እናም በጥበብ እንዲያድግና የተሻለ ነገር እንዲሰራልን ብሎም የሰፈር ሰላም የነሳበትን ባር ተብዬ የሰፈሩንም የደራሲንም ክብር በሚመጥን የተሻለ ቤት ይለውጥልን ዘንድ ልቦና እንዲሰጠው ዱዓ አደረግኩለት…
ለቁርስ ወደቀጠረኝና የህግ ባለሙያ ወደሆነው ወዳጄም ተጣደፍኩ… ስለ ዣንዣድ የታዘብኩትን እና የበገንኩበትን አወጋሁት… እህህ ብሎ ካደመጠኝ በኋላ አንገት የሚያስደፋ ነገር ጨመረልኝ…
እሱ: ቀድመህ ብትነግረኝ ኖሮ ድርሽ እንዳትል እነግርህ ነበር… የክስ መዝገቡ እኮ ገና አልተዘጋም!… አለኝ
እኔ: እንዴ የምን ክስ?!
እሱ: ያካባቢው ሰዎች የመንደራችንን ሰላም ረበሸ… በሰላም መተኛት አልቻልንም… ኧረ በህግ!… አንድ በሉን… በምሽት ያለቅጥ የሚከፍተውን ሙዚቃ ይቀንስልን… አልያም ድርጅቱን ይዝጋልን… ሲሉ የከሰሱበት መዝገብ ነዋ!… ባክህ ልጁ ዝናና ገንዘብ እንዳያስብ ሳያደርጉት አልቀሩም … ያሳፍራል!
የምሬን አፈርኩ!!!… አዘንኩ!… አቀረቀርኩ!… በዝና አልያም በንዋይ ፍቅር ደንቁረው ከሚያደነቁሩን ይታደገን ዘንዳም ጸለይኩ!!!…
ቱ በል!… !…
አለችው እናቱ …”
ብሎ እንዳለኝ ጸሃፊ
እንዳስተማረኝ ያ ገጣሚ
እውነት ጥበብን አታሚ
ህጸጽን በወግ ኮርኳሚ…
˝!…˝ በል እስቲ አንተ ሎጋ
˝!…˝ ባለ ነው ያኛው ለጋ
አገር ምድሩን ያንጋጋ
ከልሒቅ ተርታ የተጠጋ
የሰፈር ሰላም ያናጋ …
እናም ˝በል እስቲ …
ቶ ፊደል ነው የቃል አቻ
የቅንጣት ሚስጥር መፍቻ
የረቂቅ ጥበብ መግቻ
የዝና ጥማት ስልቻ
የንዋይ ማቆር ዘመቻ …
ቻ ቻ ቻ
ቻ ቻ ቻ
ከንቱ ከበር ቻቻ
ባዶ ወሬ ብቻ . . .
ልብ አይንሳው ብቻ !!!
_________//_________
አብዲ ሰዒድ

ምንጭ፦http://abdiseid.com/2013/03/25/xanxad/


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር