የኢሕአዴግ የሃያ-ሦስት ዘመን አገዛዝ

መወቃቀሱ ከልዩነትም አልፎ እንዳወዛገበ አነሆ ሃያ-ሦስተኛ ዓመቱን አለፈ። የሃያ ሦስት ዓመቱ ጥቅል ሒደት፤ የዉዝግቡ መሠረታዊ ምክንያትና የወደፊቱ ፖለቲካዊ ጉዞ እንዴትነት የዉይይታችን ትኩረት ነዉ።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አዲስ አበባን በዉጤቱም መላዉ ኢትዮጵያን የተቆጣጠረበት ሃያ ሠወስተኛ ዓመት ሊጠናቀቅ ያንድ ሳምንት ጊዜ ነዉ የቀረዉ። የኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ወይም የደርግ ዉድቀት በብዙ ሥፍራ በጠመንጃ ሐይል እንደሚደረገዉ ለዉጥ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብም እንደየስሜት፤ ፍላጎትና ጥቅሙ የተለያየ አንዳዴም ተቃራኒ ትርጉም ነዉ ያለዉ። ኮሚንስታዊዉ ወታደራዊ ሥርዓት (ደርግ) በመወገዱ የተደሰቱና የሚደሰቱ በርካታ ኢትዮጵያዉያን የመኖራቸዉን ያክል ኢሕአዴግ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ነፃነትዋን እንድታዉጅ ኢትዮጵያም ወደብ አልባ እንድትቀር በግንባር ቀድምትነት በመታገገሉ እስካሁን ድረስ የሚወቅሱት ብዙ ናቸዉ። የድርግ ዉድቀትና የኤርትራ ነፃ መዉጣት ረጅም ዘምን ያስቆጠረዉ የርስ በርስ ጦርነት ፍፃሜ መሆኑ ተነግሮ ሳያበቃ ኢትዮጳያ እስካሁን ድረስ እልባት ባልተገኘለት የድንበር ዉዝግብ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ገጥማለች።የሁለቱ ሐገራት ጦር አሁንም እንደተፋጠጠ ነዉ።
ኢሕአዴግ የመራና ያስተናገደዉ የሰኔ 1983ቱ የሠላምና የዴሞክራሲ ጉባኤ ከተደረገ ወዲሕ በሐገሪቱ የሕዝብ እኩልነት፤ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ የሰብአዊ መብት፤ የፕረስና የግለሰቦች ነፃነት መከበሩ ታዉጇል።
እነዚሕን እሳቤዎች መሠረት ያደረገ ሕገ-መንግሥትም ተደንግጓል። በምጣኔ ሐብቱ ረገድም ኢትዮጵያ እንደ ዘመኑ ፈሊጥ የምዕራቡ ዓለም የሚያቀነቅነዉ የነፃ ገበያ መርሕ እንደምትከተል ተደንግጓል።ኢትዮጵያን ላለፉት ሃያ-ሰወስት ዓመት የሚያስተዳድረዉ ኢሕአዴግና ደጋፊዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት፤ ሰብአዊ መብቱ የተከበረ፤ የፈለገዉን አስተዳዳሪ በድምፁ የመሾምና የመሻር ሥልጣን ባለቤት መሆኑን ይናገራሉ።ሐገሪቱ ከፍተኛ የምጣኔ ሐብት ዕድገት ማሳየቷን ሕዝቧም የዚሕ ዕድገት ተጠቃሚነቱን ይናገራሉ።
ተቃዋሚዎችና የሰብአዊ መብትና የፕረስ ነፃነት ተሟጋቾች ግን ተቃራኒዉን የሚናገሩት።ተቃዋሚዎችና የመብት ተሟጋቾች እንዲያዉም ኢሕአዴግ ሰብአዊ መብትን የሚረግጥ፤ የፕረስ ነጻነትን የሚደፈለቅ፤ የሐይማኖት ነጻነትን የሚያፍን፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፤ነፃ ጋዜጠኞችን፤ የሐይማኖት መሪዎችን፤ የሙያ ማሕበራት ተመረጮችን የሚያስር የምርጫ ዉጤትን በጉልበቱ የሚቀማ፤ የሐገሪቱን ሐብት ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ ብቻ የሚያቀራምት በማለት ይወቅሱል። መወቃቀሱ ከልዩነትም አልፎ እንዳወዛገበ አነሆ ሃያ-ሰወስተኛ ዓመቱን አለፈ።የሃያ ሰወስት ዓመቱ ጥቅል ሒደት፤የዉዝግቡ መሠረታዊ ምክንያትና የወደፊቱ ፖለቲካዊ ጉዞ እንዴትነት የዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር