መድረክ ሕይወታቸው ላለፈና ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ጠየቀ


የአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን  የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን መሠራትን አስመልክቶ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ
ዩኒቨርሲቲዎች ባደረጉት ሰላማዊ ሠልፍ ላይ በተፈጠረ ግጭት ሕይወታቸው ላለፈ ቤተሰቦችና ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሀብቶች፣ መንግሥት ካሳ መክፈል እንዳለበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ጠየቀ፡፡ 
መድረክ ‹‹ለሰላማዊ ተቃውሞ ጥይት ምላሽ ሊሆን አይገባም›› በሚል መሪ ቃል ግንቦት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. መነሻውን ከግንፍሌ ወንዝ ድልድይ አድርጐ በቤልኤር ሆቴል፣ በህንድ ኤምባሲ፣ በአዋሬ አደባባይና በአድዋ ድልድይ በማድረግ በድንበሯ እናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ሜዳ ላይ ባጠናቀቀው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ፣ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡
የመድረክ አባልና የፓርላማ ተመራጭ የነበሩት አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም መድረክ ለምን ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ እንደተገደደ ሲናገሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ራሱ ላወጣው ሕገ መንግሥት ባለመገዛት ኢሕገ መንግሥታዊነቱን አረጋግጧል፡፡ ትግላችን ኢዲሞክራሲያዊ ሒደቶች እንዲታረሙ ነው፡፡ በአገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ችግር የዲሞክራሲና የሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር እጦት ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
ሕገ መንግሥቱ ሲጣስ ‹‹መብቴ ተጥሷል›› ማለት ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን የገለጹት አቶ ገብሩ፣ የአዲስ አበባንና የልዩ ዞኖቹን የጋራ ልማት ትስስር ሽፋን፣ ሕዝብ ያልተወያየበትንና ያልተስማማበትን ለመተግበር መነሳት ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን የገዢው መንግሥት ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጭምር ያረጋገጡት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገብሩ፣ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያቀርቡለት የተለያዩ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ሰጥቶባቸው ቢሆን ኖሮ፣ የጠፋው የሰው ሕይወትና የወደመው ንብረት ሊተርፍ ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ያለፋቸውና በቀላሉ መፍትሔ ሊያገኙ በሚገባቸው ጉዳዮች ምክንያት፣ ሕይወታቸው ላለፈው ዜጐች ቤተሰቦችና ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሀብቶች ካሳ መክፈል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የተፈጠረውን አለመግባባት ወይም ግጭት በተለያዩ ዘዴዎች ማክሸፍ እየተቻለ አልሞ በመተኮስ ሕይወት ያጠፉትን ለፍርድ እንዲያቀርብም አክለዋል፡፡ ገለልተኛ አካል (አጣሪ ኮሚሽን) ተቋቁሞ ጉዳዩን በመመርመር ለሕዝብ እንዲያሳውቅም አቶ ገብሩ አሳስበዋል፡፡ 
ሰላማዊ ሠልፉን የታደሙ የመድረክ አባላትና ደጋፊዎች ‹‹አፈና ይቁም፣ ጥይትና እስራት እኛን ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሊያግደን አይችልም፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን የሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደታችንን እናካሂዳለን፣ በሕገወጥ መንገድ የሚደረጉ አፈናዎች ይቁሙ፣ አንከፋፈልም፣ ከፋፋዮችን እናወግዛለን….›› የሚሉና በእንግሊዝኛና በቁቤ የተጻፉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡ 
በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ከተገኙት የመድረክ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች የአረና ትግራይ ፓርቲ እንዲሁም የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ተወካይ አቶ ጐይቶም ፀጋዬ፣ ‹‹መንግሥት ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው የተለያዩ ሴራዎችን ከመሥራት ቦዝኖ አያውቅም፤›› ብለው፣ ይህ ተግባሩ የተነቃበት በመሆኑም ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣኑ እንዲወርድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹መሪዎች ጥሩ ሲሠሩና ሲያሠሩ የተወለዱበትን አካባቢና ቤተሰቦቸውን ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ይወክላሉ፤›› ያሉት አቶ ጐይቶም፣ መጥፎ ሥራ ሲሠሩ ግን ከራሳቸው በስተቀር ማንንም እንደማይወክሉ ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግም ይህንን ሊያውቀው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በሕዝብ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣ መንግሥት አለመኖሩንና ሕዝብ እንዲከበር ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ከፓርቲ ይልቅ ሕዝብ ሊከበር እንደሚገባ ኢሕአዴግ ማወቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሌላው ሰላማዊ ሠልፈኞቹ ያነሱት ነጥብና በአቶ ገብረ ማርያም የተነገረው ጉዳይ፣ በሕገ መንግሥቱ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ መሆኑን የሚደነግገውን ድንጋጌ ኢሕአዴግ በመደፍጠጥ ያለበቂ የካሳ ክፍያና ከመኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎችን እያፈናቀለ መሆኑን ነው፡፡ መንግሥት በዝቅተኛ የካሳ ክፍያ በቂ ያልሆነ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎችን አፈናቅሎ፣ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ እየቸበቸበ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ገብሩ ሕገ መንግሥቱን ባልጣሰ፣ ከሙስና በፀዳ ሁኔታና ባለድርሻን ባሳተፈ ሁኔታ ነዋሪዎች ተገቢ የሆነ ክፍያና በቂ የመኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ፣ የስልክና የተጋነኑ  የዋጋ ጭማሪዎች ላይ፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦትን መንግሥት በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡ 
የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱና ያላግባብ የታሰሩትም ካሳ እንዲከፈላቸው አቶ ገብሩ ጠይቀዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ሃይማኖትና መንግሥት አንዱ ባንዱ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ መደንገጉን የጠቀሱት አቶ ገብሩ፣ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል መንግሥት እንዲቆም እንዲያደርግና በቅርቡ ወጥተው ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኙት አፋኝ ሕጐች እንዲታረሙ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የደኅንነትና የፀጥታ ኃይሎች፣ መከላከያና ፖሊስ ሠራዊት ሉዓላዊነታችንን ጠባቂዎች፣ ታማኝነታቸው ለአገሪቱ ሕገ መንግሥት ብቻ መሆን አለበት፤›› በማለት አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ የኦፌዴን መሥራችና ለረዥም ዓመታት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሳም ተገኝተዋል፡፡ ሰላማዊ ሠልፉም ያለምንም ችግር ከጠዋቱ 5፡30 ሰዓት በሰላም ተጠናቋል፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር