ጥሬ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እያሽቆለቆለ ነው

-በውጭው ዓለም ከቡና ገለባ ምግብ ሊዘጋጅ ነው
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከቡና ኤክስፖርት ይገኝ የነበረው ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላርን ለመጠጋት የሚዳዳው ነበር፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ከ840 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከቡና ብቻ ተገኝቶ ነበር፡፡
በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ መላክ የተቻለው ቡናና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ 67 ሺሕ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀረበና ከ222 ሚሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ ያላለ ገቢ ተመዘገበ፡፡ 
የቡና ሽያጭ ለማሽቆልቆሉ የሚሰጡ በርካታ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ መምጣቱ ዋናው ምክንያት ተደርጐ ቢቆይም፣ በአገር ውስጥ የቡና ፍጆታ እየጨመረ መምጣት፣ ‹‹የጀበና ቡና›› መሸጫዎች መብዛት፣ ሌሎች ተወዳዳሪ አገሮች ከኢትዮጵያ የተሻለ የቡና መጠን ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣው የቡና ኤክስፖርት ገበያ ከሚጠበቀው በታች ገቢ እያስገኘ ቢሆንም ከግብርና ምርቶች አሁንም በቀዳሚነት ገቢ እያገኘ ደረጃውን ይዟል፡፡ 
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ጥሬ ቡና መጠን እያንገዳገዳት ቢሆንም፣ ከቀድሞ የስታር ባክስ ባልደረባና የሥራ ፈጠራ ባለቤት በኩል የተሰማው አስገራሚ የቡና ዜና አነጋግሯል፡፡ ዜናው ኢትዮጵያውያን የተቀባበሉት ሲሆን ከማኅበራዊ ድረ ገፆች፣ በቲዊተር ገጻቸው ከተቀባበሉት መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በበርካታ ተቋማት ተሳትፎ ያላቸው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ናቸው፡፡ ቡናን በምግብ መልክ በማዘጋጀት፣ ዱቄቱን ሲያሻዎ ዳቦ፣ ኩኪስ ወይም ሌላ ዓይነት ኬክ እንዲሠሩበት ወይም ግራኖላ፣ ቼኮሌትና ካራሜል የተባሉትን ዓይነት ኬኮች ለማዘጋጀት የቡና ገለፈት ተመራጭ መሆኑ ቢፈለሰፍም፣ ይህም ኢትዮጵያን የሚያካትት አይመስልም፡፡ 
ከቡና ገለፈት ወይም ገለባ ምግብ ለማዘጋጀት የተነሱት ዳን ቤሊቩ የቡና ባለሙያ ባይሆኑም በወንዞች ላይ ከፍተኛ የብክለት አደጋ እያደረሰ ያለውንና ከእጣቢ ጋር እየተደፋ የአካባቢ ጠንቅ የሆነውን ገለፈት ለምግብነት ለማብቃት፣ ከግሉቲን ነጻ ምግብ በቡና ዱቄት አማካይነት ለመሥራት ተቃርበዋል፡፡ ለሁለት ዓመታት የተመራመሩበት ይህ ሥራ በዚህ ወር በይፋ መጀመሩን በድረ ገጹ ያበሰረው ዘ ጋርዲያን ነበር፡፡ 
በመቶ ሚሊዮን ቶን የሚቆጠር ገለፈት ከቡናው ከተለየ በኋላ እንዳልባሌ ነገር በወራጅ ውኃ ተደፍቶ መቅረቱን ያስተዋለው መሐንዲሱ ቤሊቩ፣ ከዚህ ተረፈ ምርት የሚወጣው ምርት አካባቢ ላይ ያለውን ተፅዕኖና ብክለት ለመቀነስ የሚያስችለውን ሐሳብ አመንጭቷል፡፡ ከሌሎች የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር በመሆን መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን ከወዲሁ ከታዋቂ ሬስቶራንቶችና የምግብ ባለሙያዎች ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑ ተነግሯል፡፡ በኒካራጓ፣ በቬትናምና በሜክሲኮ ሰፊ የቡና ገበያ ካላቸው ሁለት ኩባንያዎች ጋርም ከወዲሁ የኢንቨስትመንት ስምምነት አድርጓል፡፡ 
ኮፊ ፍሎር የተባለው የቤሊቩ ኩባንያ ከሐዋይ፣ ከኒካራጓ፣ ከጓቲማላ፣ ከሜክሲኮና ከቬትናም ቡናዎች 160 ሺሕ ኪሎ ግራም ያህል ገለፈት በማጣራትና ወደ ዱቄትነት በመቀየር ለምግብ እንዲውል ያደርጋል ተብሏል፡፡ ሆኖም ይህ መጠን በየዓመቱ እስከ አምስት ቢሊዮን ኪሎ ግራም ቡና ገለፈት የሚመረት በመሆኑ የኩባንያው ዕቅድ እጅግ ጥቂቱን ድርሻ እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡ ቤሊቩ እንደሚናገሩት ምንም እንኳ ችግሩን ባይቀርፈው በአምስት ዓመት ውስጥ 100 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አቅራቢ የቡና ዱቄት ለምግብነት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ 
ከአዲሱ የቡና ዱቄት ገበያ ኢትዮጵያ በቀጥታ ተሳትፎ አይኖራትም፡፡ ይልቁንም የቡና ገበያ እየዋዥቀ ጥሬውን ቡና ሸጦ የውጭ ምንዛሪ ማግኘትም አስቸጋሪ የሆነበት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ከ2007 ዓ.ም. በኋላ በየዓመቱ ለዓለም ገበያ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው የቡና መጠን 700 ሺሕ ቶን ነበር፡፡ እስካለፈው ዓመት የታየው ውጤት ግን ከ300 ሺሕ ቶን ከፍ ሊል አለመቻሉን ነው፡፡ ይባስ ብሎም ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሊሸጥ የቻለው የቡና መጠን ከ66 ሺሕ ቶን ብዙም ከፍ አላለም፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ከ200 ሺሕ ቶን ቡና ተሸጦ በታሪክ ከፍተኛው ገቢ ተገኝቶ ነበር፡፡ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ብቻ ቡና 842 ሚሊዮን ዶላር በመገኘቱ ቡና ትልቅ ድርሻ የያዘበት ወቅት፣ በወቅቱ ከነበረው የዓለም ዋጋ ከፍተኛነት ጋር የሚያያዝ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ 
በቡናው ዘርፍ ላይ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት የተገኘው 222 ሚሊዮን ዶላር፣ ዝቅተኛነቱ ከታሰበውም በታች ነበር፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ አገሪቱ ልታገኝ የቻለችው አጠቃላይ ገቢ ግን 2.22 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቀሱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ናቸው፡፡ ሆኖም ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ግን 1.3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች የተምታታ መረጃ ይፋ ማድረጋቸው እንተጠበቀ ሆኖ አገሪቱ ላስገባችው ዝቅተኛ የወጪ ንግድ ገቢ ተጠያቂ ከተደረጉት አንዱና ዋናው ቡና መሆኑን አቶ ተክለወልድ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያስታወቁት ሐሙስ፣ ግንቦት 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ 
የቡና አፈጻጸም ማሽቆልቆሉን በማስመልከት ምክንያቱን ለማወቅ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ኃላፊዎችን ለማነጋገር ሞክረን ባይሳካልንም፣ አንጋፋው ቡና ላኪ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ግን በግላቸው ምክንያት ያሏቸውን ነጥቦች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዋጋው መውረድና ከሚያዝያ አጋማሽ በኋላ ድንገት ማንሰራራት በቀር የተለየ ምክንያት የለም ይላሉ፡፡ 
ትልቁን ረብሻ የፈጠረው የዘንድሮ ገበያ መውጣት የጀመረው ከሚያዝያ አጋማሽ መሆኑ ነው ያሉት መቶ አለቃ ፈቃደ፣ ለወትሮው የቡና ዋጋው እያንሰራራ መጨመር የሚጀምረው ከሰኔ ጀምሮ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ብለዋል፡፡ የብራዚል ቡና በውርጭ በመመታቱ ምክንያት በዓለም ገበያ ላይ አቅርቦቱ ያንሳል ተብሎ ይጠበቅ ስለነበር ገበሬው፣ አቅራቢውና ላኪው እጃቸው ላይ ይገኝ የነበረውን ቡና ሸጠዋል፡፡ ክምችት ያላቸው አንዳንድ ላኪዎች ግን የዋጋውን አካሄድ ለመገመት ዕድል እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ 
በተለምዶ በጥቅምት፣ በኅዳር፣ በታኅሣሥና በየካቲት ይዞ፣ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ድረስም ቡና በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚሸጥ ይታሰብ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ድንገት ወደ ላይ ያገረሸው የቡና ዋጋ ቀድሞ በዝቅተኛ ዋጋ የሸጠውን ላኪ ጉዳት ላይ እየጣለ መሆኑን መቶ አለቃ ፈቃደ አስታውቀዋል፡፡ ለግንቦት ወር የሚቀርበው ቡና በሚያዝያና ከዚያም በፊት ባለት ወራት ውስጥ አስቀድሞ የሚሸጥ በመሆኑ ድንገተኛ የዋጋው ጭማሪ ጉዳት በማድረስ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ 
ምንጭ፦ ethiopianreporter.com

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር