ፍትህ የተነፈገው የግንቦቱ ዕልቂት፤ ሎቄ!

Photos@Internet
Editor: Worancha Information Network
''...The Sidama people, like other peoples under this regime, are denied their legitimate right on their own land. They were massacred in cold blood when they demonstrated against forceful eviction from their ancestral land. Instead of investigating this atrocity committed by the regime’s special notorious unit known as Agaazi, as promised by the regime, the evidences were suppressed and the perpetrators were also promoted. One of the culprits of that atrocity is the president of the Southern Peoples’ Region at the time and the current Prime Minister of Ethiopia Hailemariam Desalegn....''

By Desalegne Mesa, May 10, 2014, Hawassa, Sidama
በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ከግንቦት ወር ጋር በተያያዘ አንድ አይነት አመለካከት(አሉታዊ) እንዳላቸው መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ግንቦትን ከወራት ሁሉ ክፉ፣ አደጋ በብዛት የሚከሰትበትና በባህሪዩም ደረቅ ወር (ምንም እንኳን ዝናብና ልምላሜ ይዞ ቢመጣም) አድርገው በአዕምሮአቸው ስለዋልና ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በአብዛኛው ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ የተለያዩ(በተለይም ቋምና ባህላዊ) ተግባራትን በዚህ ወር ውስጥ መፈጸም የማይፈልጉት፡፡ ለምሳሌ የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ ባለበት አካባቢ(ሲዳማ) በግንቦት ወር የመኖርያ ቤት መሠረት አይጣልም፣ ወጣቶች እይጋቡም(አይዳሩም)፣ አርብቶ አደሮች በግንቦት ወር ወስጥ ከብቶቻቸውን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ(ለግጦሽ ሲሉ) አያዘዋወሩም(Didoyinani) ተብሎ ስለምታመን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት አስመልክተው ምንም ነገር አይፈፀምም፡፡ ነገር ግን በዚህ (ከወሮች “ክፉ” በሆነ ወር) በሀገራችን የተከሰቱ ተግባራት በርካታ ቢሆኑም ለዛሬው ፅሁፌ ምክንያት የሆነኝን የኢህአዴግን በግንቦት መከሰትንና ከዚህ ወር ጋር ያለውን አጉል አፍቅሮተ መንፈስ ቅድሚያ መስጠት እፈልጋለው፡፡
እንደምታወቀው ኢህአደግ ለሀገራችን መዓት ይዞ የመጣው በግንቦት ወር ውስጥ ነው(ግንቦት 20/1983.)፡፡ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚያካህደውም ግንቦት ወር ውስጥ ነው፡፡ የኃይል እርምጃ ሊወስድ ከወጠነም ብዙን ጊዜ በግንቦት ውስጥ ወይም ወደ ግንቦት ወር ጠጋ ብሎ በግንቦት ጥላ ስር ሆኖ ይከውናል…፡፡ ምንም እንኳን ኢህአዴግ ሀገርቷን በጉልበት ሲቀራመታት የአንድ መንግስት መጥፋትና በሌላ የመተካት ቁምነገር መረዳት በሚያስችለኝ እድሜ ክልል ውስጥ ባልሆንም፣ አሁን ወደ ኋላ ዞር ብዬ ስገመግም ኢህአዴግ ሀገርቷን የተቆጣጠረበት ወር ግንቦት መሆን እንዲሁ በታሪክ አጋጣሚ የተገናኜ ሳይሆን ሕወሓት/ኢህአዴግ በዚህ ወር ውስጥ ከገባ ሀገርቷን በኃይል መቆጣጠርና ህብረተሰቡ በሚጠላው(ጥላ ቢስ) ወር መግባት አዋጭ እንደነበር ስለሚያስብም ጭምር ነው የሚል ጠንካራ ግምት ያሳድራል፡፡ ለዚህም ይሆናል በዚህ ወር መውሰድ የሚፈልገውን ማንኛውንም የጭካኔ ርምጃ ለመውሰድ የሚመርጠው፡፡ ድርጅቶችን ብሎም ብሔርና ብሔረሰቦችን ለመጨቆንና ለማፈን ሲፈልግም ፍላጎቱ በዚህ ወር(አካባቢ) እንዲሆን ማድረጉ ከወሩ ጋር የተቆራኘ ነገር እንዳለው ያሳብቅበታል፡፡
ይህንን ያህል ስለኢህአዴግና ግንቦት መቆራኘት፣ እንዲሁም ስለወሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን አሉታዊ አመለካከት ካልኩኝ ዘንዳ በዛሬው ፅሁፌ ለየት አድርጌ ትኩረት መስጠት የምፈልገው የኢህአዴግ የግንቦት ወር ተግባር በሲዳማ ያሳረፈውን ከትውልድ ወደ ትውልድ በደማቅ ተጽፎ የሚሸጋገረውን ጠባሳን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮችን ማስታወስ ነው፡፡ ይህንን ጠባሳ ላስታውስ የፈለኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ በፊታችን ግንቦት 16/09/2006.ም ስለ ሎቄ አልቂት (ግንቦት (16/09/1994.) በተመለከተ በሲዳማ ብሔራዊ የሐዘን ቀን በሲዳማ አርነት ንቅናቄ ስለታወጀና በዚህም ምክንያት በሲዳማ አርነት ንቅናቄ ዋና ጽ/ቤትና በሌሎችም በወረዳ ቅ//ቤቶች ታስበው እንደምውልና እልቂቱን አስመልክተው ድርጅቱ በዋናው ጽ/ቤት የሻማ የማብራትና አጠቃላይ ውይይት እንደሚደረግ መረጃ ስላለኝ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክቶ የነበረውን አጠቃላይ ድባብ ለመላው ፍትሕ ናፋቂ ለሆነው ኢትዮጵያ ህዝብ በድጋሚ ማስታወስ ስላስፈለገ ነው፡፡
ከላይ ከመግቢያው ላይ ለመግለጽ በሞከርኩት መልኩ በግንቦት ወር ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበትን እንቅስቃሴ ቢያድርግም ቅሉ በ”ክፉ ቀን” የሀገርቷን ሁለመና የተቀራመተው ክፉ የሲዳማ እናቶችንና አባቶችን ልጆቻቸውን በግፍ ነጥቆ ባዶ እጃቸውን ማስቀረቱ አልቀረም፡፡ ይሄ የመንጠቅ ተግባር በተለያዩ ሀገርቷ አቅጣጫ በተለያየ መልክ ሲፈጸም የሚናየውና የሚንሰማው ሀቅ ነው፡፡
በተለይ ለሲዳማዎች ግንቦት 16/1994.ም ከወትረውም በበለጠ ክፉ ቀን ነበር፡፡ ገና ከጅምሩ ክፉ ያሰበው የስልጣን ጥመኛው የኢህአዴግ መንግስት የሲዳማን ህዝብ በተለያየ መንገድ ለማዳከም ስራውን ጀምሮ ነበርና የማይፈነቃቅለው ቋጥኝ አልነበረም፡፡ ይህንን ሲዳማን የማዳከም ተግባሩን በ1983-4ዎቹ ክልሎች በሚዋቀሩበት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም ዘግይቶ የማዳከም አጀንዳውን እንደገና በግንቦት 1994.ም መባቻ ላይ በአዲስ መልክ ”ለ” ብሎ መተግበር ቀጠለ፡፡ የዚህ አጀንዳው ማዕከል የሆነው ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ የሀዋሳ ከተማ የደ/////መንግስትና የሲዳማ ዞን መናገሻ ከመሆኑም በተጨማሪ ከተማዋ ተጠርነቷ ለሲዳማ ዞን አስተዳደር እንደሆ በ1992.ም ስራ ላይ በዋለው በደ/////መንግስት ”ሕገ-መንግስት” በክልሉ ለሚገኙ ዞኖች በሰጠው ስልጣን ይደነግጋል፡፡ ይህንን ድንጋጌ በተሻሻለው በ1994.ም ”ሕገ-መንግስት” ሽረው የከተማይቱን ተጠርነት ለክልል እንዲሆን ከማድረጉም አልፎ የሲዳማ ዞን ከሀዋሳ ከተማ አንዲወጣ መዶለቱ ነገሩን እጅግ ክፉ፤ ከክፉም የከረፋ አደረገው፡፡ በዚህ አጀንዳ ዙርያ ”የሲዳማ ብሔረሰብ ተወካዮች” ነን ያሉትን ነገር ግን የኢህአዴግ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ትከሻ ላይ ወጥተው ውሳኔው ላይ የደረሰው ኢህአዴግ የሚያስፈራው አልነበረም/የለምና ጉዳዩ የሚመለከተውን የሲዳማን ህዝብ ለወጉ እንኳን ለማወያየት አልፈለገም፡፡
ይህ የኢህአዴግ ሴራ መረጃ የደረሰው የሲዳማ ህዝብ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄውን መጠየቅ ጊዜ ልሠጠው እንደማይገባ በማመን በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ አንድና ሁለት ላይ ሰላማዊ ሰልፍን፣ መሰባሰብንና ተቃውሞአቸውን አደራጅተው ስለማቅረብ በተመለከተ የተጠቀሱ መብቶችንና ግዴታዎችን መሠረት በማድረግ ተቃውሞውን ለማሰማት ሲወስንም ጊዜ አልፈጀበትም፤ ጭቁን የሲዳማ ህዝብ፡፡ በዚህ መሠረት ጉዳዩ ለሚመለከተው በ16/09/1994.ም መነሻውን ከሀዋሳ በስተደቡብ አቅጣጫ ልዩ ስሙ ቱሎ ተብሎ ከሚጠራበት ቦታ አድርገው መድረሻውን ደግሞ የሀዋሳ መስቀል አደባባይ ያደረገ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ቀደም ብሎ በጽሁፍ ገልጾ አሳወቁ፡፡ በዚህም መሰረት ከላይ በተጠቀሰው እለት ሴቱ፣ወንዱ፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ተማሪው፣ ነጋደውና ወዘተ ያካተተ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የብሔሩ አባላትና አጀንዳውን የደገፉ ሌሎች ከሲዳማ ጋር አብሮ የሚኖሩ በሰልፉ ተቀላቅለው የኢትዮጵያን ባንዲራና የተለያዩ ቅጠላቅጠሎችን ይዘው ጉዘዋቸውን ወደ መድረሻው አዳባባይ አደረጉ፡፡
ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እየገለፁ እስከ ታቦር ተራራ አቅራቢያ ወደለው በአካባቢው አጠራር ሎቄ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ሲደርሱ ለመቀጠል አልቻሉም፡፡ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቀው በታቦር ተራራ(ዱሜ) አናትና ዙሪያ በመሸገው በጠላት(ኢህአዴግ) ኃይል ሰልፋቸው ክፉኛ ተገታ፡፡ በጨካኝ(በክፉ) ወር የገባው ክፉ ዘመናዊ መሳሪያ ባነገቡ የኢህአዴግ ስርዓት ተላላኪዎች(ጦር ኃይል) በንፁሐን ህዝብ ላይ የተኩስ እሩምታ አስከፈተባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ከተረፈው ይልቅ የወደቀውንና የሞተውን መቁጠሩ የሚቀል ሆነ፡፡ ንፁሐን መብታቸውን የጠየቁ የሲዳማ ልጆች እንደፈንድሻ በጥይት እየተጠበሱ ብድግ ብሎ ወደቁ፤ ዳግምም አልተነሱም፡፡

በዚያን ጊዜ ከዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ ጋር በሀዋሳ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃት ምህርታቸውን የሚማሩ አያለ ወጣቶች አካላቸውንና ህይወታቸውን አተዋል፡፡ በታዓንምር የተረፍኩኝ አኔ ደግሞ በዛ ትምህርቴ ገፍቼ ዛሬ ከከፍተኛ ትምርት ተቋም ከወጣው በኋላ ተቀጥሬ የማገኘው ገቤ በቂ ካለመሆኑም በተጨመሪ በገቢ ግበር፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ፣ በአባይና ወዘተ ስለተሸለተ በቂ ባለመሆኑ ሳይማሩ ያስተማሩኝን ለመጦር ባልችልም ቤተሰቦቼ ለማዕረግ በመብቃቴ ብቻ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የክፍል ጓደኞቼን በኢህአዴግ የተነጠቁ አያሌ የሲዳማ እናቶችና አባቶች ደግሞ አንጀታቸው ግንቦት በገባ ቁጥር ልጆቻቸውንና የኢህአዴግን ጭካኔ የተሞላበትን ተግባር እያስታወሰ ይርገበገባል፤ አይኖቻቸው እረፍት አልባ እምባ ያፈሳሉ፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ ያንን መከራ የበዛበትን ጊዜ አምልጦ(ዛሬም ስለህይወቱ እርግጠኛ ሆኖ መኖር ባይችልም) ተማረና ዛሬ በሀገርቷ ካሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ውስጥ ተቀጥሮ የበኩሉን አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከጎኔ መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በጭካኔ ተገድለው ያለጊዜያቸው የተለዩን ወጣቶች ዛሬ በሕይወት ኖሮ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ለቤተሰቦቻቸው ደስታ መሆን ሲችሉ በአንጻሩ ደግሞ ምናልባት ለሀገራቸው የበኩላቸውን መወጣት እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡ ግን ምን ያደርጋል ተገደሉ፤ መብታቸውን ጠይቀዋላ!
ከዚህ በተጨማሪ አያሌ የሀገር ሽማግለዎች፣ ነጋዴዎች፣ ምሁራንና አርሶ አደሮች የዚህ ጭካኔ የተሞላበት የጠላት ርምጃ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከሁሉም አንጀትን የሚበላው በወቅቱ በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የነበረ አንድ ተማሪ የመጨረሻ እስትንፋሱን ተጠቅመው የተናገረው ነገር ከሁሉም አዕምሮ የማይጠፋ ሆኖ እስከ አሁን ዘልቀዋል፤ ለሚመጣውም ትውልድ በዳማቅ ተጽፎ የሚቀመጥ ነው፡፡ ይህ ወጣት በከባድና ዘመናዊ መሳሪያ ደረቱን ተመተው ወደ ይርጋለም ሆስፒታል ተወስደው ነበር፤ ይድናል በሚል በተሟጠጠ ተስፋ፡፡ ነገር ግን እንዳይተርፍ አድርገውታልና መሞቱ አልቀረም፡፡ ከመሞቱ በጣም ጥቂት ደቂቃዎችን ቀደም ብሎ እንባ እየተራጩ መትረፉን ለሚናፍቁት ወላጆቹ አንድ ነገር ሹክ ብሎ ለዘላለሙ አሸለበ፡፡ ”እኔ ልሞት ነው፡፡ የኔ መሞት ችግር የለውም፤ ነገር ግን ሀገራችንን አደራ” ብሎ ተናገረና ላይመለስ ከቤተሰቡ ተለየ!፡፡ በቃ ያለ ሀገር ከመኖር ለሀገር እየታገሉ መሞት ይሻላል ብሎ ወርቃማ መልዕክቱን ለትውልድ አውርሰው ሞተ( ይቅርታ እየኖረ ነው ሊበል እንጂ!)፡፡
በሌላ በኩል በቦርቻ ወረዳ ውስጥ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ በ2005.ም ተሞክረው በከሸፈው አካባቢና ማሟያ ምርጫ ምክንያት ሲንቀሳቀስ ያገኘው ባሌላ ተብላ የሚትጠራ አካባቢ ነዋሪ የሆነና በግንቦት 16 ቀን 1994.ም አንድ እጁን ተመተው የመቆረጥ አደጋ ያጋጠመው የዛን ጊዜ ልጅ ያሁኑ ወጣት ደግሞ “አኔ ለሲዳማ ህዝብ ነፃነት አንድ እጄን ሰጥቻለው፤ አሁን ደግሞ አስፈላጊ ከሆነ ሕይወቴን ለመስጠትም ዝግጁ ነኝ፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ በቆራጥነት ሊትመሩን ይገባል” ብሎ ለሲአን ከፍተኛ አመራሮች ማስጠንቀቂያ ያዘለች አስተያየት መሰንዘሩን አስታውሳለው፡፡ መውደቂያቸው ሳይታወቅ ተመተው በወቅቱ ቦቆሎ እርሻ(በዛሬው ቤቶች እንደ እንጉዳይ በፈሉበት ሎቄ) አካባቢ ሞቶ የአውሬ ራት የሆኑትን በርካቶችን ማን ያውቅና በመጨረሻና ስቃይ በተሞላበት አንደበታቸው ያስተላለፉትን መልዕክት መስማት ይችላል?
ሕይወታቸውንና አካላቸውን በግፍ ስላጡት ንፁሐን ሲዳማ ልጆች ማን ምን ተደረገ?የሰውን ህይወት ማጥፋት ከበረሃ ጀምሮ የለመደው ሕወሓት በግንባር ቀደምትነት የሚመራው ኢህአዴግ ስለጠፋው ህይወትና ስለጎደለው አካል አግባብነት ያለውን ምላሽ ልጆቻቸውን ለተነጠቁት ቤተሰቦችና ዜጋዋን በጭካኔ ላጣችው ኢትየጵያ መመለስ ሲገባው “የሞቱት ወሮ በሎች ናቸው፤ የመጡትም ከሌሎች አጎራባች ከተሞች ነው::” ብሎ በንፁሐን ሲዳማ ልጆች ደም ላይ ለመሳለቀ በሚቆጣጠራቸው ሚድያዎች በኩል ብቅ አለና ለቤተዘመዶቹ የተወጉበትን ቁስል ጨምሮ የሚያመረቅዝ መርዝ ጨመረ(መግለጫ ሰጠ)፡፡ ከዚህም ይባስ ብሎ የሟቾቹን ቤተሰቦች ከየለቅሶ ላይ አየለቃቀመ ወደ ወህኒ ቤት አጋዛቸው፡፡
ጭካኔ የተሞላበት የጥይት ድብደባ ሰለባ ሆኖ የሞቱትን ከሜዳ(የአሁኑ ቤቶች) ሰብስቦ በእቃ መጫኛ መኪና(ISUZU) ጭነው በሸራ ሸፍኖ(ገንዞ) ሀዋሳ በሲዳማ ዞን ፖሊስ መምሪያ ግቢ ውስጥ ካሳደረ በኋላ በነጋታው ቤተሰቦች እየቀረቡ የልጃቸውን ወይንም የዘመዳቸውን አስከሬን ከፖሊስ እጅ እየፈረሙና ሟቾቹም የሞቱት እራሳቸው በሰሩት ጥፋትና ወንጀል እንደሆነ እያመኑ እዲረከቡ ተገደዱ፡፡ ይህንን ድርጊት በጭካኔ የፈፀሙ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ማናቸውም ምንም አይነት ህጋዊና ድርጅታዊ እርምጃ አልተወሰደባቸውም፡፡ ይልቁንም በሰሩት ጭካኔ በተሞላበት ጀብዳቸው እየተደነቁ ከኢህአዴግ ከፍተኛ ስልጣን ሊያገኙ ቻሉ እንጂ፡፡ ቆይ ማንኛውም ዜጋ ከየትም ይምጣ፤ ወይም ምንም አይነት ወንጀል ይፈፅም በህግ ሳይፈረድበት መሞት አለበት ወይ??ሌሎች ደግሞ ከስልጣቸው አርፎ በስመ ነጋደነት በጥይት አካላቸውንና ዘመዶቻቸውን በጭካኔ አተው የቆሰሉትን የሟች ቤተሰቦችንና ሌሎችን የአካባቢውን ህብረተሰብ በዘረፋና ኑሮ ውድነት ቁስላቸውን ደጋግሞ በመነካካት እንዲያመረቅዝ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ማን ጠይቋቸው? “ጌታዋን የተማመነች ውሻ...”ነው ነገሩ፡፡ የንፁሐን ሲዳማ ልጆች ደም ጩሄትስ መቼ ይሆን ፍትህ የሚያገኘው?
የሲዳማ ህዝብ እየጠየቀ በየወቅቱ ነፍሱንና አካሉን የሚገብርበት ጥያቄስ ከምን ደረሰ? ምንስ እልባት አገኘ?ለመሆኑ የሲዳማ ህዝብ የጠውቀውና እስከ አሁን እየጠየቀ ያለው ጥያቄዎች ምን ምን ናቸው የሚለውን ማውቁና ስለአግባብነቱም በንፁህ ህሊና ውሳኔ መጠት አስፋላጊ ይሆናል፡፡ የሲዳማ ህዝብ ከመጀመሪያው ዘመናዊት ኢትዮጵያ ገዢ ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ሲያነሳ የነበረውና የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅም የተቀሩት ጥያቄዎች ሁሉ መሠረት ነው ብሎ የሚያስበው አንኳር ጥያቄ አስተዳደራዊ ነጻነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ ነጻነት ሲል የሲዳማ ህዝብ አያሌ ዘመናትን እየታገለና በደምና በነፍስ ጭምር ዋጋ እየከፈለ እስከዚህ መንግስት ደረሰዋል፡፡ ምንም እንኳን ከዚህ(ኢህአዴግ) ቀደም ብሎ የነበሩት አስተዳደራዊ ስራዓቶች የሲዳማን ህዝብ በክልሉ ውስጥ በመግባት ስልጣኑን በመቀማትና በመበዝበዝ ቢያስቸግሩም በነበረው ሲዳማ መልካዓ-መድር የመሸርሸር ብሎም አስተዳደራዊ ክልሉን የመቁረስ አባዜ አልተጠናወታቸውም፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የብዝበዛ አሰራሮችን እንዳለ የወረሰውን የኢህአዴግን ስርዓት ደግሞ ከሁሉ ለየት የሚያደርገው የጥንቱን የሲዳማን መልካዓ-ምድር በጉልበት የመቀማት፤ ከመቀማትም አልፎ የብሔሩን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና በህላዊ ነፃነት ጨምድደው መያዙ ነው፡፡ ይህ ተግባሩ በሌሎችም ኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ በስፋት የሚንፀባረቅ የክፋት አጀንዳው ነው፡፡ የነፃነትና እራሱን በራሱ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበርለት የሚፈልግ ህዝብም ነባሩን የነጻነት ጥያቀውን በአዲስ መልክ ከግንቦት 16/1994.ም ጀምሮ ከማንሳት ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ለዚህም “የሲዳማ ህዝብ አስተዳደራዊ ክልል ይቋቋም፤ በሀዋሳ ከተማ ላይ የሚሞከር ጣልቃ ገብነትና የመናጠቅ እርኩስ አጀንዳ ይቁም፤ ሀዋሳ የሲዳማ ህዝብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል ማዕከል ሆኖ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” እና ወዘተ እያለ የተቃውሞ ድምፁን እያሰማ ነበር፣ ይገኛልም፤ እያሰማም ይቀጥላል!፡፡ 
ነገር ግን በ”ክፉ” ወር በክፉ ኮቴ የኢትዮጵያን ምድር የረገጠው ኢህአዴግ የሲዳማን ህዝብ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎችን ገቢራዊ እስካሁን አላደረገም፡፡ የሲዳማ ህዝብም መጠየቁን አላቆመም፡፡ ይባስ ብሎ ኢህአዴግ በ1994 .ም የሀዋሳን ከተማ ተጠርነቷን ለክልል በመስጠት ለብዝበዛ ክፍት አደረገ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ(2004.ም ጀምሮ) ”ሜትሮፖሊታን ከተማችንን እንዴት እናስተዳድር?” በሚል የሲዳማን ህዝብ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አገልግሎቶችና ባህላዊ ተውፍቶች ረገድ የማዳከም መሰሪ ሴራና አጀንዳ ያረገዘውን ሰነድ አርቀው ሀዋሳን ለፌደራል የታጨች ከተማ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የሲዳማ ህዝብ ህገ- መንግስታዊ ጥያቄስ?
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ምን እየሰራ ነው?
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ ለሲዳማ ህዝብ መብት እየታገለ በዱር በገደል ያለፈና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለና እየከፈለም የሚገኝ የህዝቡ መሪ ድርጅት ነው፡፡ በየጊዜው ኢህአዴግ በሚደቅንበት እንቅፋቶች ውጣ ውረድ የበዛበትን ጉዞ እየተጓዘ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እራሱን ገምግሞና ፈትሾ በተሻለ መንገድ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን አቅጣጫ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ድርጅቱ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ (ነባር፣ ወቅታዊና አንገብጋቢ) ችግሮችን በጥልቀት ፈትሾና ለይቶ በማውጣት ህዝቡን ውጤታማ በሆነ ጎዳና ለመምራትና ለድል ለማብቃት በሚያስችለው ቁመና(አደረጃጀት ደረጃ) ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም መሠረት ድርጅቱ የህዝብ ወካይ እንደመሆኑ መጠን የሲዳማ ህዝብ ግንቦት 16/1994.ም ላይ ህገ-መንግስታዊ መብቱን በመጠየቁ ምክንያት ብቻ በገዢ ፓርቲ የተወሰደውን የእብድ ርምጃ ህግን በተከተለ መልኩ ለመጠየቅና የድርጊቱም ግምባር ቀድም ተዋናዮች ህግ ፊት ቀርቦ ስለፈፀሙት እንዲጠየቁ ጥያቄ ለማቅረብ የራሱን ስራ እየሰራና ዝግጅቱንም እያጠናቀቀ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቅዱስ ሀሳብ! በግፍ የተጨፈጨፉ የንፁሐን ደም የሚወጣ(ፍትህ የሚያገኝ) ከሆነ፡፡ ታዲያ ለዚህ ለተቀደሰ ሀሳብ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚትኖሩ የሲዳማ ምሁራንና ሌሎችም ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም በሙያችሁና በሌላም በሚያመቻችሁ መንገድ ለሲአን እንቅስቃሴ መስመር የሚያግዙ ግባዓቶችን በማቀበል የየበኩላችሁን ድርሻ እንዲትወጡ ፀሐፊው በዚህ አጋጣሚ የግሉን አስተያየት ይሰነዝራል፡፡

ፍትህና ነፃነት በግፍ ለተጨፈጨፉት/እየተበደሉ ላሉት ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች!!!
By Desalegne Mesa, May 10, 2014, Hawassa, Sidama


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር