የቡና ፈቃድ ኖሯቸው ኤክስፖርት አድርገው የማያውቁ 37 ነጋዴዎች ፈቃድ ተሰረዘ

-ለኤክስፖርት የተዘጋጀ ቡና ላይ የኮንትሮባንድ ንግድ ደርቷል
በቡና ንግድ ተሳታፊ ሳይሆኑ የቡና ፈቃድ አውጥተው ለዓመታት የተቀመጡና ምናልባትም አጭበርባሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ 37 ግለሰቦችን ፈቃድ መሰረዙን የንግድ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡
የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ሲያቀርቡ፣ የቡና ንግድ መቀዝቀዙንና ኮንትሮባንድ መስፋፋቱን፣ እንዲሁም ከቡና ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የንግድ ሚኒስቴር ምን እያደረገ እንደሆነ ተጠይቀዋል፡፡
የቡና ጉዳይ ድሮ በሚኒስቴር ደረጃ ይመራ ከነበረበት ወርዶ በአንድ ተቋም ውስጥ መመሸቁ እንደሚያሳስባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ከኮንትሮባንድ መስፋፋት በተጨማሪ የቡና ንግድ ሳይኖራቸው የቡና ፈቃድ ያወጡ መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
በቡና ንግድ ካልተሰማሩ ፈቃዱን ለምን እንደሚፈልጉት መገመት እንደሚቻል የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ዋነኛው መንግሥት ለቡና ንግድ የሚሰጠውን ትኩረትና ጥቅማ ጥቅም ለመቀራመት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በቡና ንግድ ዘርፍ ለሚሰማሩ መንግሥት ቅድሚያ የባንክ ብድርና የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ስለሚያደረግ፣ እነዚህ በቡና ንግድ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ ያወጡ ነገር ግን ኤክስፖርት አድርገው የማያውቁ ነጋዴዎች ይህንን ጥቅም ለመመዝበር አቅደው ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት የማጭበርበር ሥራ የሚሠሩ የቡና ንግድ ፈቃድ ይዘው የተቀመጡ ነጋዴዎች ፈቃድ ተሰርዟል፤›› ብለዋል፡፡
እነዚህ ነጋዴዎች የሚያገኙትን ብድር ተጠቅመው አራጣ የማበደር ተግባር ውስጥ  ተሰማርተው ሊሆኑ ይችላል የሚሉት አቶ ከበደ፣ የነጋዴዎቹን ማንነት ከመግለጽና ፈቃዳቸውን ከመሰረዝ ባለፈ የሚወሰድ ዕርምጃ ስለመኖሩ አልተናገሩም፡፡ 
የፓርላማው አባላት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቡና ዘርፍ ላይ ያካሄደውን ጥናትና ግኝቱን መረጃ በማድረግም የሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡
ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተመረጡ 15 ቡና ላኪዎች ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት  ውስጥ ወደ ውጭ አገር ኤክስፖርት ያደረጉት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በሕጉ መሠረት ብሔራዊ ባንክ አውቆት ስለመላኩ ለማረጋገጥ ቢሞከርም ማረጋገጫ እንዳልተገኘለት፣ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ ልታጣ እንደምትችል ሪፖርት ማድረጉን በመጠቆም፣ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እንዲያስረዱ ሚኒስትሩ ተጠይቀዋል፡፡
ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ችግሩ እንዴት ሊፈጠር ቻለ የሚለውን ሚኒስቴሩ እያጣራ መሆኑን የገለጹት አቶ ከበደ፣ በጥናቱ ውጤት መሠረት በሕግ የሚጠየቅ ካለ ይጠየቃል ብለዋል፡፡
‹‹ላኪዎች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከል ቡና ይገዛሉ፣ ከገዙት ቡና ለሚልኩት የቡና መጠን ኤልሲ ይከፍቱና የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ያገኛሉ፡፡ የብሔራዊ ባንክን የመላኪያ ፈቃድ ይዘው ሲሄዱ ነው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቡናው እንዲወጣ የሚፈቅደው፤›› በማለት የቡና አላላክ ሥርዓቱን አስረድተዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ተቋማት መካከል ማለትም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከል፣ በብሔራዊ ባንክና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መካከል በሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ወቅት ችግር ተፈጥሮ ሊሆን ስለሚችል፣ ይህንን ለማጣራት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ውስጥ 206,825 ቶን የቡና ምርት ወደ ውጭ በመላክ 822 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በተያዘው ዕቅድ ላይም ሆነ ባለፈው ዓመት በተላከው መጠን ላይ መድረስ አለመቻሉን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡
በሪፖርቱ መሠረት በአሥር ወራት የተላከው የቡና መጠን 136 ሺሕ ቶን ብቻ ሲሆን፣ የተገኘውም 489.3 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በመጠን 8.8 በመቶ ሲቀንስ በገቢ ደግሞ 15.2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ መዋዥቅ የተነሳ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የኤክስፖርት ቡና በሕገወጥ መንገድ በአገር ውስጥና ወደ ጎረቤት አገሮች እየወጣ መሆኑ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግዱን በመከላከል ረገድ የተደረጉ ጥረቶች ውስን መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቡናን ጨምሮ ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶችን ሕገወጥ ንግድ ለመቆጣጠር ከፌደራል እስከ ክልል የሚዘልቅ የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይልና ኮማንድ ፖስት መመሥረቱን አስረድተዋል፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር