ደቡብ ግሎባል ባንክ ወደ አትራፊነት መግባቱን ገለጸ

-የኮር ባንኪንግ ቴክኖሎጂ ግዥ ፈጸመ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሰማራት ይጠየቅ የነበረውን የተከፈለ 100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከማሳደጉ በፊት 15ኛው የግል ባንክ በመሆን የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው ደቡብ ግሎባል ባንክ 19 ወራት አስቆጥሯል፡፡
ከሌሎች የግል ባንኮች በተለየ በአንድ የአክሲዮን ሽያጭ ፕሮግራም በሚሊዮን የሚቆጠር አክሲዮን በመሸጥ በ138.9 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ የገባ ባንክ ነው፡፡
በ5481 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተው ይህ ባንክ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በመጀመርያው የሥራ ዓመት (10 ወራት) አትራፊ መሆን ባይችልም በአሁኑ ወቅት ግን ወደአትራፊነት እየገባ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡
የባንኩን የ19 ወራት የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ በተሰጠ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ ባንኩ መጋቢት 2006 ዓ.ም. 14.5 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ለማ እንደገለጹት፣ በመጀመርያው ዓመት ላይ ተመዝግቦ የነበረው ኪሳራ አሁን መለወጡንና በየወሩ እያተረፈ መጓዝ ጀምሯል፡፡ በመጀመርያው የሥራ ዘመንም ትርፍ ይገኛል ተብሎ ባይጠበቅም ደቡብ ግሎባል ባንክ ግን በአጭር ጊዜ ወደ ትርፍ መግባት ከመቻሉም በላይ አሁን እያስመዘገበ ያለው ትርፍ በ2006 በጀት መዝጊያ ጥሩ ትርፍ የሚያገኝ መሆኑን ያሳያልም ብለዋል፡፡ በመጋቢት 2006 ዓ.ም. ያስመዘገበው የትርፍ መጠንም አምና ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 223 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ 
ባንኩ ትርፍ ማስመዝገብ ከመጀመሩ ባሻገር በዋና ዋና የባንክ አገልግሎቱ እያደገ መምጣቱን የፕሬዚዳንቱ ገለጻ ያስረዳል፡፡ የባንኩ የሥራ እንቅስቃሴ በለውጥ ጎዳና ላይ ስለመሆኑም ዋና ዋና የተባሉ አስረጅዎችም አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብን ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው በ284 በመቶ ማደጉ አንዱ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ግኝትን በመተለከተም አምና በመጋቢት 2005 ዓ.ም. ከነበረው በ1,115 በመቶ አድጎ በመጋቢት 2006 ዓ.ም. 24.3 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ተገልጿል፡፡
የሰጠው ብድርም በተመሳሳይ መንገድ ዕድገት ያሳየ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከአምና በ276 በመቶ  ብልጫ ያለው ብድር በመስጠት መጋቢት 2006 ዓ.ም. ድረስ 302 ሚሊዮን ብር አበድሯል፡፡ ከዚህም ሌላ የባንኩ እሴት 165.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነና የተከፈለው ካፒታሉ ደግሞ 165.7 ሚሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል፡፡
ይህ ባንኩ ደረሰበት የተባለው ደረጃ ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህም በኋላ ይህንኑ ዕድገት ተከትሎ ይጓዛል ብለዋል፡፡ ባንኩ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ዕድገቱን የሚያሳይ ቢሆንም፣ በሥራ ሒደቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ሳይጠቁሙ አላለፉም፤ በተለይ የኔትወርክ ችግርና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ 
እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት ገለጻ፣ በባንኩ የ19 ወራት የሥራ ጉዞ እንደቁልፍ ሥራ ተደርጎ የተወሰደው ባንኩን በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ለመግባት የኮር ባንኪንግ ሲስተም ግዥ መፈጸሙ ነው፡፡              
ባንኩ ባወጣው ጨረታ መሠረት አሸናፊ ከሆነው ኩባንያ ፍሌክስ ኪውብ የኮር ባንኪንግ ግዥ አከናውኗል፡፡ ግዥው የተፈጸመው ኦራክል ፋይናንሻል ሰርቪስስ ከሚባል የህንድ ኩባንያ ነው፡፡ ግዥውን ለመፈጸም ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል ያሉት አቶ ወርቁ፣ ፍሌክስ ሲተምን ለመምረጥ የተፈለገው በርካታ የአገር ውስጥ ባንኮች እየተጠቀሙበትና ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ጭምር ነው፡፡ ባንኩ ገዛሁት ያለው ሲስተም በ115 አገሮች ውስጥ ባሉ 319 ባንኮች ውስጥ እየተሠራበት ነው ተብሏል፡፡ 
ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ ለማዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሚያስፈልጉ የሶፍትዌርና ተጓዳኝ ግዥዎች ባንኩ ወደ 21 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያወጣም ተገልጿል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ባንኩ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ሲሆን አዳዲስ አገልሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዘዋል ተብሏል፡፡ በተለይ ባንኩ በዕቅድ ከያዛቸው እንደ የኤጀንት ባንኪንግ ዓይነት አገልሎቶቹ ይህ ቴክኖሎጂ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡   
የሞባይል ወይም የኤጀንት ባንኪንግ ሲስተም በፍጥነት ተግባር ላይ ለማዋል እንደሚፈልጉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚሁ ሥራ በወጣ ጨረታ መሠረት የአቅራቢዎች ምላሽ በመሰብሰብ ላይ ነው፡፡ በኤጀንት ባንኪንግ ሥራ ላይ ትኩረት የተደረገው በቀላሉ ደንበኞች ጋር ለመድረስ መልካም አማራጭ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ባንኮች አትራፊ ሆነው እንደሚቀጥሉና ባንካቸውም የደረሰበት ውጤት ያሳያል ያሉት አቶ ወርቁ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚም ተጨማሪ ባንኮች ለመሳብ ዕድል ያለው ነው ይላሉ፡፡ አቶ ለማ አዳዲስ ባንኮች መፈጠር የሚኖርባቸውና አሁን ባሉት ባንኮች ብቻ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚፈለገውን ያህል የሚደግፉ ባለመሆናቸው ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ተጨማሪ ባንክ ይኑር በሚለው ጉዳይ አንዳንድ ብዥታዎች እንዳሉም አስታውስዋል፡፡ የአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮች ውድድር ጠንክሯል፣  እያደገ ነው፣ ስለዚህ ተጨማሪ ባንክ አያስፈልግም በሚለው አመለካከት አይስማሙም፤ ይህ አመለካከት ብዥታ ነው ይሉታል፡፡ ይህንን አመለካከታቸውን ለማጠናከር እንደመረጃ ያቀረቡት የኬንያን ባንኮችን  ነው፡፡
ከኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት በግማሽ በምታንሰው ኬንያ ውስጥ 43 ባንኮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን 19 ብቻ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ባንኮች መኖር ይገባቸዋል፤ አትራፊ መሆናቸውንም እያረጋገጥን በመሆኑ በተለይ ባለሀብቶች ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር