ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ ተመረጠች

-ውድድሩ አፍሪካና አውሮፓን አፎካክሯል
በዓለም አቀፍ የቡና ግብይት ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱት ቡና ገዥ ኩባንያዎችና አምራቾች በአባልነት የታቀፉበት ዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት፣ ኢትዮጵያ አራተኛውን ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ መረጠ፡፡
እ.ኤ.አ. በማርች 2016 የሚዘጋጀውን ኮንፈረንስ ለማስተናገድ የመጨረሻው ውድድር ላይ ቀርበው የነበሩት ኢትዮጵያና ጣሊያን ናቸው፡፡ ምርጫው በተካሄደበት  ለንደን ከተማ ተገኝተው የነበሩ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት እንደገለጹት፣ ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ልታሸንፍ ችላለች፡፡ 
በመጨረሻው ውድድር ላይ ከድምፅ ሰጪዎች መካከል ግዙፎቹ የአውሮፓ ቡና ገዥ ኩባንያዎች ድምፃቸውን ለጣሊያን ሰጥተው ነበር፡፡ አፍሪካውያንና ሌሎች ቡና አብቃዮች ደግሞ ለኢትዮጵያ ድምፅ በመስጠት ውድድሩ በአፍሪካውያንና በአውሮፓውያን መካከል እንዲሆን አድርገው ነበር ብለዋል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፉ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ብራዚል ድምጿን ለኢትዮጵያ በመስጠቷ ለኢትዮጵያ አሸናፊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡
ከመጨረሻው ውድድር ቀደም ብሎ ኮንፈረንሱን ለማዘጋጀት ከአፍሪካ ኮትዲቯር፣ ጋቦንና ኬንያ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሁሉም አገሮች የኢትዮጵያን የተወዳዳሪነት ጥያቄ በመቀበል ድምፃቸውን ሰጥተዋታል፡፡ ኮንፈረንሱ አፍሪካ ውስጥ መካሄዱ ትልቅ ዕድል ነው በማለት ለኢትዮጵያ ዕድሉ እንዲሰጣት አፍሪካውያኑ ድጋፍ እንዳሰባሰቡም በቦታው ከነበሩ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ለመረዳት ተችሏል፡፡ 
ከዓለም የቡና ድርጅት (አይሲኦ) መካከል 50 በመቶዎቹ የቡና ገዥ ኩባንያዎች የሚወከሉባቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ቡና አምራች አገሮች ናቸው፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ኮንፈረንስ ማዘጋጀት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጹት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር የቦርድ አባልና  የግሪን ኮፊ ባለቤት አቶ ታደለ አብረሃ፣ በተለይ አዘጋጁ አገር ከፍተኛ የቡና ገበያ እንዲያገኝ ዕድል ይሰጠዋል ይላሉ፡፡ ከኮንፈረንሱ ጠቀሜታ አንፃር በዓለም ቡና ገበያ ላይ ወሳኝ የሆኑና ቡና የሚገዙ ኩባንያዎች የሚመጡ በመሆናቸው አዳዲስ ገበያ ለማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ወቅት የሚተላለፈው ውሳኔ የቡና ገበያ አቅጣጫን የሚያመላክት በመሆኑ፣ በግብይት ውስጥ ያሉ ኩባንያዎችም ሆኑ አምራች አገሮች የሚወከሉበት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡ ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የቡና እርሻዎች የሚጎበኙበት መርሐ ግብር ይዘጋጃል፡፡ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ ልዑካን ከመላው ዓለም ተውጣጥተው የሚሳተፉበት በመሆኑ፣ ለአገሪቱ የገቢ ምንጭ በመሆን ጥቅም ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ኮንፈረንሱን እንድታዘጋጅ መመረጧን ተከትሎ የዓለም የቡና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የቤርቶ ሲልቫ በሰጡት አስተያየት፣ ቡና ወደ ቤቱ ተመልሷል ብለዋል፡፡ አዲ ቱሪ የኮትዲቯር ዋና ተወካይና የአፍሪካ ቃል አቀባይ ሲሆኑ፣ ‹‹የአፍሪካ ዋናዋ ቡና አምራች ኢትዮጵያ ስለሆነች ጉባዔውን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ብዙ ትግል አድርገናል፣ ተሳክቶልናልም፤›› ብለዋል፡፡
አቶ አብደላ ባገርሽ የኤስኤ ባገርሽ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው፣ የዓለም ፖሊሲ አውጪዎችና የማኅበሩ አባላት በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ብዙ ጥቅሞች አሉት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 
ከኢትዮጵያና ከጣሊያን ባሻገር ከደቡብ አሜሪካ አገሮች ኮሎምቢያ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባ ነበር ያሉት አቶ አብደላ፣ በለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በተደረገ ክትትል አማካይነት ኮንፈረንሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ጉባዔው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ ድጋፍና ክትትል ሲያደርግ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት ውስጥ ያላት ድምፅ 1.7 በመቶ ብቻ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር