የኢኮኖሚ ዕድገቱ በብዙኃን ኢትዮጵያዊያን የኑሮ ጫና ሲመዘን

በአሳምነው ጎርፉ
ያሳለፍናቸው ቀናት ኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ዓብይ ፆምን ተሻግረው የፋሲካ በዓልን በድምቀት ያከበሩበት ነው፡፡ በዓል ሲመጣ ደግሞ ሐበሻ ‹‹እንደ ቤቴ›› ሳይሆን ‹‹እንደ ጎረቤቴ›› በሚል ብሂል አቅሙን አሟጦና
ተበድሮ ለማድመቅና ‹ለመደሰት› እንደሚዳክር ይታወቃል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተዘገበውና በየአካባቢው ተዟዙሬ እንደተመለከትኩት ዘንድሮ የቁም እንስሳት፣ የቤት ዕቃውና ማስዋቢያው ብቻ ሳይሆን ከስኒ ረከቦት ሥር የሚጎዘጎዘው ቄጠማ ሳይቀር በፍጥነት ዋጋቸው አሻቅቦ ታይቷል፡፡ ተርፎት በቅንጦት ለሚኖረው ምንም ባይመስለውም፣ ብዙኃኑ ሕዝብና መካከለኛ ላይ ያለው ወገን የመግዛት አቅም አጥቶ ሲንፈራገጥ ታይቷል፡፡ በተለይ የደመወዝተኛው ችግር ደግሞ ይጎላል፡፡ እንግዲህ ይኼ ጉዳይ ነው በዚህ ርዕስ ላይ አንዳች ነገር ማለት እንደሚገባ ያነሳሳኝ፡፡ 
የኢኮኖሚ ዕድገቱ የገቢ መመጣጠን አሳይቷልን? 
በዚህ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን የሚክድ ካለ ጤነኝነቱ ያጠራጥራል፡፡ ስለዚህ ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡ የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ተከታዮች ‹‹ኒዮ ሊብራል›› የሚባለውን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ (የገበያ አክራሪነትም ይባላል) የሚተቹበት አንድ አባባል አለ፡፡ ‹‹የገቢ አለመመጣጠን በአብዛኛው የሚስተዋለው ባለሀብቶች ፖለቲካውን በጨበጡባቸው አገሮች ነው፡፡ ባለፀጋ ፖለቲከኞች ለመሠረታዊ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች ማለትም ለትምህርት፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለሕዝብ ትራንስፖርትና ለመሳሰሉት በቂ በጀት ለመመደብ ፈቃደኛ ስለማይሆኑ የታክስ ምጣኔውን በመቀነስ ጫናቸውን ከላያቸው ላይ ያራግፋሉ፤›› የሚል ነው፡፡
ይህን የሚቃወሙት የፖለቲካ ተንታኞች ግን የመንግሥትን በመሠረታዊ ልማቶች ላይ መሳተፍ አጥብቀው ባይቃወሙትም (በተለይ ዛሬ ዛሬ) ሁሉንም ለገበያው በነፃነት መልቀቅን ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ምንም ተባለ ምን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመዘገብ መንግሥት በተለይ በመሠረተ ልማቶች ማለትም በመንገድ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በትምህርትና በጤና ተቋማት፣ በቤቶች ልማት ፕሮጀክቶችና መሰል ሥራዎች አጠናክሮ ማከናወኑን ሊዘነጋ አይችልም፡፡ መንግሥት የውስጥ ገቢውን ብቻ ሳይሆን ትላልቅ ብድሮችና ዕርዳታዎችን አሰባስቦ ሥራ ላይ እያዋለም ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች የቀን ሥራ (ዝቅተኛ ገቢም ቢሆን) የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አንፃር ብዙ የተባለለትን ያህል ባይሆንም የግል ባለሀብቶችም እንቅስቃሴም እየታየ ነው፡፡ 
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት (ስማቸው እንዲገለጽ አልፈለጉም) በአገሪቱ ባለሁለት አኃዝ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት የመጣው ዜሮ ከሚባል ዝቅተኛ ደረጃ በመነሳት ነው ይላሉ፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ከአፍሪካ የመጨረሻ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላት አገር፣ በሕዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት ሲመዘን እዚህ ግባ የማይባል ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ከ30 ቢሊዮን ዶላር በታች ነበር የምታገኘው፡፡ ከዚህ ዝቅተኛ ደረጃ በፍጥነት ለመውጣት አሁን ያለው ቁርጠኝነት መታየቱ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙዎቹ አገሮችም ተረጋግቶ ማልማት ከተቻለ ይኼን ያህል መራመድ አይዳግትም ይላል፡፡ ይህ ማለት ግን የመንግሥትን ጥረት ማንኳሰስ እንዳልሆነ በመጠቆም፡፡
ተጨማሪ ለማንበብ ሪፖተር ጋዜጣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር