የሀዋሳ መስፋፋትና የሲዳማ ህዝብ ፈተና



ከማህበራዊ መረብ ላይ የተገኘ ጽሁፍ
ተጻፈ በደሳለኝ መሳ 
ምንጭ፦ Desalegne Mesa


ከቅርብ ዓመታት (1950ዎቹ) ወዲህ ከተመሰረተቱት ከተሞች አንፃር ሐዋሳ ጥሩ የሚባል እድገት ጎዳና ላይ እንዳለች የሚታወቅ እውነታ ነው፡፡ በተለይም ተፈጥሮ በለገሰቻት ውበት ምክንያት ሁሉም ሰው ለማለት በሚያስችል መልኩ ልቡ ወደ ሀዋሳ ሽፍተዋል፡፡ ነጋዴዎች ፣ ጎብኝዎች የመንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምርጫና መሰብሰቢያ አየሆነች መታለች አዳሬ-ሐዋሳ፡፡ ይህንን የህዝብ ፍልሰትንና ፍላጎት ለማስተናገድና ለማርካት ይመስላል የተለያዩ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች(የማን ናቸው?) መበራከት ጀምረዋል፡፡ የተጠቀሱት ሁሉ የከተማዋን ተጨማሪ ውበት ስለምሰጡ ጥሩ ናቸው፡፡ ከዚህም ያለፈ የተለያዩ ፀሐፊዎች ስለ ሀዋሳ ውበት፣ ሳቢነት፣ ሳብነቱን ተከተሎ እየተከሰቱ ያሉትን ወጣ ያሉ ተግባራትንና የሀዋሳ ሂሊውና የሆነው የሀዋሳ ሀይቅ ብክለትና ስለተደቀነበት ፈተና ጽፈዋል፤ ለሚመለከታቸው ይጠቅማል ያሉትን አስተያየቶችንም ለመሰንዘር ጥረት አድርገዋል፤ የሚሰማ ከተገኘ፡፡ ነገር ግን የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ ትኩረት ለመስጠት የሚፈልገው የከተማውን ያልተጠና መስፋፋትን ተከትሎ እተጎዳ ስላለው ህብረተሰብና ስለተደቀነበት አደጋ ይሆናል፡፡ 

ከላይ የተጠቀሱት የከተማይቱ መሳጭ ጎኖች ቢኖሩትም በዛው ልክ ደግሞ የህዝብ መከራ የሚያበዙ፣ ከአካባቢ ወጣ ያሉና የምዕራባውያን ባህል መበራከትና ነባሩን የአካባቢውን ባህልና ትውፍት በመዋጥ ረገድ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ይህ ወጣ ያለ ነገር እንዳይከሰት ለህዝብና ባህሉ የሚቆረቆር ስርዓት መገንባትና ስርዓቱን የሚመሩ ሰዎችም የአካባቢውን ባህልና ትውፍት በሰለጠነ መልኩ ለጎብኝዎችና ለአዲስ ከታሚ ህዝብ በማቅረብ የባእድ ባህልና አሰራሮች ቦታ እንዲያጡ ማድረግ ኃላፊነት ከሚሰማው የህዝብ መሪ የሚጠበቅ ተግባር ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ይህ ነገር በሀዋሳ ከተማ ተኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ በሌላ በኩል የአካባቢው ኅብረተሰብ በኢኮኖሚ እራሱን ችለው ለሌሎች ሀገር በቀል አገልግሎቶችን ማቅረብና መሸጥ በሚችል መልኩ ቀደም ተብሎ ሊቀረጽና ለከተሜነት እራሱን ያዘጋጀ ዜጋ በሂደት መፍጠርም ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ሳለ በዚህ ረገድም ምንም የሚታይ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ከተማ ያለቅጥ እየተስፋፋ ለ”ዘራፊዎች” በር እየከፈተ ይገኛል፡፡ የከተማው አመራር ለአካባቢው ህብረተሰብ ድንገት አካባቢው እንደተወረረ ያረዳና ከአርሶ አደርነት ወደ ከተሜነት እንደተሸጋገሩ በአንድ ገጽ ማስታወቂያ ያሳውቃል፡፡ ከዚህ በኋላ መሬት አይታረስም፤ አርሶ አደር የነበሩ “ከተሜዎችም” አርሶ በምግብ ፍጆታ እራሳቸውን ከመቻልና የተረፈውንም ለገበያ ከማቅረብ ፋንታ ሊሸምቱ ገበያ መውጣት ይጀምራሉ፡፡ በአንድ ጎጆ ስር የተሰበሰቡ የአርሶ አደር ልጆች እያደጉ ሲመጡና የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው መውጣት ቢፈልጉ የሚቻል አይሆንም ምክንያቱም በከተማ ታቅፈዋላ፡፡ አልፎም ህገ ወጥ ግምባታ ሰሪዎች ተብሎ የሚደርስባቸው እንግልት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አከባቡ በከተማ አስተዳደር ስር መታቀፉን ያወቁ የ”መሬት ነጋዴዎች” አካባቡን ይወሩታል፡፡ ገዝተው ይሸጣሉ፤ ሽጠውም ይገዛሉ፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሀዋሳ በሁሉም አቅጣጫ በፍጥነት እየተስፋፋች ትገኛለች፡፡ አሰፋፉ ደግሞ ቅድመ ጥናት ያልተደረገበትና ወሰን ያልተበጀለት ሲሆን አዲስ ጎብኚዎችና ለመኖር በሚወስን ሰው ብዛት ብቻ ድንገት የሚለጠጥ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ የከተማው አስተዳደር ለዚህ አፋጣኝና ዘላቂ መፍተሄ በመስጠት የከተማዋን ወሰን ከማበጀት ይልቅ “ነጋዴዎች” እና አዲስ ከታሚው ኅብረተሰብ ሄዶ የሰፈረበትን በመከታተል ብቻ የሀዋሳ ክልል እያደረገ የራሱን የፋይናንስ ምንጭ አማራጮችን ያሰፋል፡፡ ለዚህ ጠሩ ማሳያ የሚሆነው ያለአካባቡ ህብረተሰብ ፍላጎት ተከልለው በ”አዲሱ ሊዝ አዋጅ” መሠረት እየተሸነሸኑ ለጨረታ የሚቀርቡና ከህዝብ ዘርፎ መንግሥትን የማበልጸግ ስራ እየተሰራባቸው ያሉት የሃላዴ፣ የዳቶ ኦዳሄና የቡሹሎ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡በተጨማሪም ከዚህ በፊት ከሀዋሳ ክልል ውጪ የነበሩ አካባቢዎችን ድንገት የከተማው አካል በማድረግና ”ለልማት ተፈልገዋል” በማለት አርሶ አደሮችን ያግድና መሬቱን ጦሙን ያሳድረዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ወጣቶች ከወላጆቻቸው በሚያገኙት ቁራጭ ቦታ ላይ የራሳቸውን ጎጆ እንዳይቀልሱ ይከለክላል፡፡ በዚህም ምክንያት የሀዋሳ አካባቢ አርሶ አደሮች ሞፈርና ቀንበራቸውን በተሰቀለበት ከተው ሰንበተዋል፡፡ የሲዳማ የባህል ሽማግሌዎች ቁጭ ብሎ ከሚዳኙበት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ቦታዎች(Gudumaale) ከመገፋታቸውም አልፎ ቡሉኳቸውንና በትራቸውን አስቀምጠው ያለወትሯቸው በጉልበት ሥራ የሚተዳደሩና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ በስቃይ የሚገፉ ሆነዋል፡፡ ለዚህም ያልታደሉ አቅም የለላቸው አዛውንቶች ወደ ከተማይቱ ተበትነው የሰውን እጅ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ግጭቶችን በባህላዊና ቀለል ባሉ መንገዶች ያለምንም ወጪ መፍታት በሐዋሳ አካባቢ እየቀረ መተዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የሚካሰስ፣ የሚፋታና ለሙስና የታጋለጠ(ፍርድን በብር የምያገኝ) እየሆነ መተዋል፡፡


ወጣቶች ወደ ከተማ ገብቶ በሙያቸው ተወዳድረው እንዳይቀጠሩ በቂ ቅድመ ማዘጋጃ ነገርና የሙያ ትምህርት ደረጃ ስላላደረሷቸው ጎዳና ተዳዳሪነትና የወጣት ተጧርነት እጣፋንታቸው እየሆነ መተዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መንግስትና ተባባሪዎቻቸው ከከተማው በሚገኝ ገቢ ላይራቡ ጠግበዋሉ፡፡ እንዳይታረስ የተከለከለው መሬት እየተቆረሰ በልማት ሰበብ ታልፎ ለ”ለባለሀብቶች” ይሰጥና በቅጡ ለምቶ እንኳን መሬታቸውን ለተነጠቁት ቅድምያ የስራ እድል ሳይፈጥሩ ታጥሮ ይቀመጣሉ፡፡ መሬቱን በመቸርቸር ጥቂት የመንግስት አፈቀላጠዎች በሀብት ላይ ሀብት ፣ በቤት ላይ ቤት እየደራረቡ መኖራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎችም መዘዞች ዋናው ምክንያት ለህዝብ ያልቆመና የህዝብ ድምፅ ለመስማት ፍቃደኛ ካለመሆኑም በላይ በሙስና የተጨማለቀ የመንግሥት ስርዓት ሀገርቷን ጨምድደው በመያዙ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ለከተማ ልማትና እንዱስትሪ ያለው መረዳትና ፖልሲ ከከተማ ያለቅጥ መስፋፋትና የጥቂት ሀብታሞች ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች መበራከት የዘለለ አለመሆኑ ነው፡፡ የሀዋሳ ያልተጠና መስፋፋትና አደጋ ለሌሎች የሲዳማ ዞን ከተሞችም እየተረፈ እንዳለ ለማንም በተለይም በቅርበት ለሚከታተለው ሰው ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ ወዶ ገነት ካላት የተፈጥሮ ሀብትና ኢኮኖሚ ምንጭነቷ በርካታ የስራ አጦችን በማስተናገድ እፎይታ መፍጠር በሚችል መልኩ እራሱን የቻለና የተደራጀ ከተማ መፈጠር ይቻል ነበር፡፡ ላኮ፣ ሞሮቾ፣ ዶረ ባፋኖና ቱላም እንደዝሁ፡፡ ግን ምን ያደርጋል አልሆነም፡፡

ምን ቢሆን? ወጣቱን፣ አዛውንቱንና ሌሎችን የአካባቢውን ነዋሪ ባህል ፣ አኗኗርና እኮኖሚ በማይጎዳ መልኩ ከተማ መስፋፋት የሚችልበትንና የራሱ የሆነ ህጋዊ ወሰን(definite city boundary) ቢኖረውና በዚህ ወሰን ውስጥ ብቻ ማደግ(ወደላይና ወደ ጎን) የሚችልበትን አሰራር በጥልቀት በመፈተሽና ተግባራዊ ማድረግና አጎራባች ከተሞችም እራሳቸውን ችለው እንዲቆጠቁጡ ማድረግ ቢቻል የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

ወጣቱንና አምራች ኃይል ብሎም ሁሉንም የአካባቢውን ኅብረተሰብ ወደ ከተሜነት የመሸጋገርያ ጊዜ በመስጠት ከግብርና ውጭ ሌሎችን የገቢ ምንጮችን እንዴት መፍጠር እንደምችሉ በማስተማርና ቀድሞ በማዘጋጀት በተለይም ወጣቱ ክፍል በሙያ የበለጸገ ሆኖ ወደ ከተማ በመግባት ተወዳደሪ የሚሆንበት አሰራር በጣም ትኩረጥ ተሰተው መጤን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የተቀሩትን ኅብረተሰብ ክፍሎችን (ያልተማሩትን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንና የባህል አባቶችን) የነበረውን ባህላዊ ስርዓታቸውን፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውንና የገነቡትን ማህባራዊ ህይወታቸውን ሳያፈርሱ (ሳይለቁ) እርሻቸውን እያረሱ እና ባህላዊ ስርዓታቸውን እየከወኑ የሚኖሩበት ቦታ በማዘጋጀት ማስፈርና በከተማው ውስጥ ደግሞ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበትን ቤት መስሪያ ቦታ በመስጠት የከተማውን እድገት እንከን የለሽና የነገ እጣፋንታው የጥቂቶችን እጅ የሚመለከቱ ሰዎች የበዙባት ከተማ ከመሆን ማዳን ይቻላል፡፡ ማን ይችላል? ህዝባዊ መንግስት፡፡ አለ? የለም፡፡ ምን ይሻላል? ታግለው ህዝባዊ መንግሥት ማቋቋም ነዋ!! ቸር እንሰንብት!

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር