ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስና መዘዙ

ጽሁፉ ተገኘ ከ ኢዜኣ

 በእንዳለ ደበላ ሀዋሳ ኢዜኣ ተጻፈ

ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የማህጸን በር ካንሰር በሽታ መንስኤ ነው። ቫይረሱ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የጀመሩ ሴቶችን በቀላሉ የሚያጠቃ ነው።�
በቫይረሱ የተጠቃች አንዲት ሴት ምንም ዓይነት ምልክት ሳታሳይ ከ10 እስከ 20 ዓመት ድረስ ልትቆይ ትችላለች።
አንዲት በዚህ ቫይረስ የተጠቃች ሴት ሰውነቷ በሽታን የመከላከል አቅም በሚዳከምበት ጊዜ ቫይረሱ ወደ ማህጸን ካንሰር የመቀየር እድሉ የሰፋ ይሆናል።
ይህ ቫይረስ ወደ ካንሰርነት ከተቀየረ ምንም መድሃኒት የሌለው በመሆኑ በማህጸን በር ካንስረ የተያዘች ሴት መጨረሻዋ ሞት ይሆናል። ይህን የሞት አደጋ ለማስቀረት ደግሞ ያለው ብቸኛ አማራጭ ማንኛዋም የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመረች ሴት ቅድመ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ በማድረግ ምልክቱ ከተገኘባት ህክምና በመውሰድ ቫይረሱ ወደ ካንሰርነት ደረጃ እንዳያድግ ማድረግ ብቻ ነው።
ብዙዎቻችን የህመም ስሜት ካልተሰማን በስተቀር የቅድመ ጤና ምርመራ ህክምና የማድረግ ልምድ አላዳበርንም። የሚሰማን የህመም ስሜትም ቢኖር እንኳን ካልተባባሰና ጉዳቱ ከፍ ካላለ በስተቀር በሀኪም ለመታየት አንፈልግም።
የሚሰማን ህመም ተባብሶና ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ መንቀሳቀስ ሲያቅተን በድጋፍ ወደ ህክምና ማዕከላት እንሄዳለን።
በዚህም ሳቢያ በቀላሉ ሊድን የሚችለው ህመም ብዙ ስቃይ አብዝቶብንና ኪሳችንን አራቁቶ ጉዳታችንን በአካልም ሆነ በኢኮኖሚ ያባብሰዋል።
ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ቢያንስ በዓመት አንደ ጊዜ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ማድረግ እንዳለብን የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የህክምና ባለሙያዎችን ምክር የሚሰሙ ግን ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ ጥቂቶች በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ሰምተው ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው በሽታ አይደፍራቸውም።
ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ ምክንያት የሆነኝ በቀላሉ መዳን የሚችለውና በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ምክንያት የሚከሰተው የማህጸን በር ካንሰር ነው።
የማህጸን በር ካንሰር ማንኛዋም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የጀመረች ሴት ልትጠቃበት የምትችልበት በሽታ ነው።
በሽታው ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ከአስር እስከ ሃያ ዓመታት በሰውነት ውስጥ መቆየት የሚችልና ወደ ካንሰርነት ደረጃ ከደረሰ መዳን የማይችል ገዳይ በሽታ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ለዚህ በሽታ የበለጠ የተጋላጭ የሆኑት ደግሞ የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ በየጊዜው የማያደርጉ ሴቶች በለጋ ዕድሜያቸው የግብረስጋ ግንኙነት የጀመሩ ከተለያየ ወንዶች ጋር ግንኙነት የሚፈጽሙ ሴቶችና ከተለያየ ሴቶች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ ጓደኛ ያላቸው ሴቶች ዋነኛ ተጠቂዎች ናቸው።
በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት በሽታ የመቋቋም ኃይላቸው የቀነሰና ኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸውና የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅምን የሚቀንሱ መድኃኒቶች የሚወስዱና በቅርብ ቤተሰብ ውስጥ የማህጸን በር ካንሰር መኖርና ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።
ኤች አይ ቪ/ኤድስ በደማቸው የሚገኝ ሴቶች በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመያዝና ቫይረሱ በሰውነታቸው የመቆየት እንዲሁም ኢንፌክሽኑ ወደ ካንሰርነት የመለወጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።
ወይዘሮ ዘነበች ትሮሬ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝባቸው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናቸው።
በአንድ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በመታመማቸው በአልጋ ላይ ከመዋላቸው ባለፈ አገግመው ሲነሱ ሙሉ አካላቸውን ለማንቀሳቀስ ተቸግረው በክራንች በመታገዝ ነበር መጠነኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት።
ወ/ሮ ዘነበች የደረሰባቸውን የጤና ችግር ምንነት ለማወቅ ባደረጉት ምርመራ የኤች አይቪ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ በመታወቁ የቫይረሱን መጠን ለመቀነስ የሚያስችለውን መድሃኒት መውሰድ ይጀምራሉ።
መድሃኒቱን መውሰድ ከጀመሩ በኋላ ጤንነታቸው እየተስተካከለ በመምጣቱ ይጠቀሙበት የነበረውን ክራንች በመጣል ዛሬ በሞተር ሳይክል ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ በኤድስ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በመርዳት ላይ ይገኛሉ።
ወ/ሮ ዘነበች ቫይረሱ በደማቸው ከመኖሩ ጋር በተያያዘ ለማህጸን በር ካንሰር አምጭው ለሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ተጋላጭ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ባደረጉት ምርመራ ከሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ነጻ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
እንደሳቸው ገለጻ ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች በማህጸን በር ካንሰር ከመጠቃታቸው አስቀድሞ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው በማስተባበር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሴቶች የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ወ/ሮ ቀመሪያ ከድር በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በአንድ አጋጣሚ ሰዎች ስለ ማህጸን በር ካንሰር ሲያወሩ በመስማታቸው በውስጣቸው ፍራቻ ያድርና ምርመራ ለማድረግ ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ያመራሉ።
ከቤታቸው ሲወጡ ተመርምረው ራሳቸውን ለማወቅ ቢሆንም ሆስፒታል ሲደርሱ ግን ፍራቻ ያድርባቸውና ተመልሰው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ ከሁለት ቀናት በኋላ በነጻ ይሰጥ የነበረው የማህጸን ካንሰር ቅድመ ምርመራ ፕሮግራም ከመጠናቀቁ አንድ ቀን አስቀድሞ ምርመራ ለማድረግ ዳግም ወደ ሆስፒታል በመሄድ ይመረመራሉ።
ምርመራው ከባድ መስሎኝ ነበር የሚሉት ወ/ሮ ቀመሪያ የነበረኝ ፍርሃት የተሳሳተ እንደነበር የተረዳሁት ከተመረመርኩ በኋላ ሲሆን በምርመራው የማህጸን ካንሰር በሽታ ምልክት በኔ ላይ በመገኘቱ ህክምናውን መከታተል እንዳለብኝና ህክምናውን በማድረግ ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆን እንደምችል ተገልጾልኝ ህክምናውን በማድረግ በድጋሚ ታይቼ ነጻ መሆኔን ማወቅ በመቻሌ እፎይታ ተሰምቶኛል ይላሉ።
ዛሬ ባደረግኩት ህክምና ነጻ መሆኔ እስከ መጨረሻው ነጻ መሆን እንዳልሆነ ተገልጾልኝ ከአምስት አመት በኋላ ድጋሚ ምርመራ ማድረግ እንዳለብኝ ተገልጾልኝ ዛሬ ሌሎችን ምርመራ እንዲያደርጉ እያስተማርኩ ነው ብለዋል።
በሸካ ዞን የማሻ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሀገሬ ደሳለኝ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ሰብለወርቅ አባተና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ አለምኘት ግርማን በበሽታው ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤን በተመለከተ ባነጋገርኳቸው ወቅት እንዳሉት ስለበሽታው ብዙም ግንዛቤ እንደሌላቸውና ካንሰር ገዳይ በሽታ መሆኑን ከማወቅ ባለፈ አስቀድሞ በመመርመር መከላከል እንደሚቻል አያውቁም።
በሽታውን ለመከላከል የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር  በመተባበር እየሰራ ይገኛል። ቢሮው ከፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ጋር በመሆን ላለፉት ሶስት ዓመታት በይርጋለም ወላይታ ሶዶና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የማህጸን በር ካንስር በሽታ የምርመራና ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
በእነዚህ ዓመታት በተከናወነ የምርመራና የህክምና አገልግሎት 2 ሺህ 444 ሴቶች ተመርምረው ከነዚህ ውስጥ የካንሰር ምልክት የተገኘባቸው 200 ሴቶች ታክመው መዳን ችለዋል።
ምልክቱ ተገኝቶባቸው ህክምና ያገኙ ሴቶች ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ተመልሰው ምርመራ የሚከናወንላቸው ሲሆን ያልተገኘባቸው ሴቶች ከአምስት ዓመት በኋላ ተመልሰው ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጾላቸዋል።
በደቡብ ክልል አንድ ሚሊዮን 756 ሺህ 914 ሴቶች ለበሽታው ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ስለሚጠበቅና እነዚህን ሴቶች ከበሽታው ለመታደግ አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ በመሆኑ ላለፉት ሶስት ዓመታት በሶስቱ ሆስፒታሎች ብቻ ይሰጥ የነበረው ህክምና በዲላ ጂንካ ጊዶሌ ተርጫ አርባምንጭ ሚዛን አማን ሆሳዕናና ቡታጅራ ሆስፒታሎች መሰጠት ተጀምሯል።
በሆስፒታሎቹ የሚሰጠው የምርመራና ህክምና አገልግሎት ቀላል ሲሆን ማንኛዋም የግብረስጋ ግንኙነት የጀመረች ሴት መመርመር እንደምትችልና የበሽታው ምልክት የተገኘባት ሴት ህክምናውን እዛው መጀመር የምትችልበት ነው።
የማህጸን በር ካንሰር ምልክት የተገኘባት ሴት በሽታው ወደ ካንሰርነት ደረጃ ከማደጉ በፊት በህክምና መዳን የሚቻል መሆኑን በማወቅ ሁሉም የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመሩ ሴቶች በተለይ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸው በሙሉ ቅድመ ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ከበሽታው ማዳን እንደሚችሉ ለመጠቆም እወዳለሁ። ቸር ይግጠመን።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር