ከበጀት አጠቃቀም ግድፈት በተጨማሪ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣትም መላ ይፈለግለት

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለፓርላማው ባቀረበው ሪፖርት፣ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የበጀት አጠቃቀም ግድፈትና ብክነት መኖሩን አስታውቋል፡፡
ይህ በተደጋጋሚ የሚታይ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን በመጠቆም ፓርላማው አፋጣኝ የሆነ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ በመንግሥት በጀት የሚያዝላቸው ብዙዎቹ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በዕቃ ግዥዎችና በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ደንብና መመርያ እንደሚጥሱ ስም ዝርዝራቸው ተጠቅሶ ተገልጿል፡፡ የአገር ሀብትን ከጥፋት ለመታደግ ሲባልም በአስቸኳይ ዕርምጃ ይወሰድ ዘንድ ለፓርላማው ጥሪ ቀርቧል፡፡
ይህ በባለሙያዎች ከፍተኛ ጥንቃቄና ሙያዊ ትንተና የቀረበ ሪፖርት በፓርላማውም ሆነ መንግሥትን በሚመራው አስፈጻሚ አካል ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው ጥርጥር የለውም፡፡ ከበጀት አጠቃቀም ግድፈትና ከብልሹ አሠራር በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ተንሠራፍቶ ያለው ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር ነው፡፡ ከብቃት ማነስ በተጨማሪ ግድ የለሽነትና የአገልጋይነት መንፈስ መጥፋት በየቦታው ተንሠራፍቷል፡፡
በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሥነ ምግባር መርሆዎች በሚያማምሩ ኅብረ ቀለማት በተዋቡ ሰሌዳዎች ላይ በግልጽ ቦታ ላይ ተጽፈው ቢታዩም፣ እነዚህን መርሆዎች የሚቀናቀኑ በርካታ እኩይ ተግባራት ይፈጸማሉ፡፡ የመንግሥት ፖሊሲዎችን በአግባቡ እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸው የተወሰኑ ወገኖች ለዜጎች ቅሬታና ምሬት ምክንያት እየሆኑ ናቸው፡፡ አገልግሎት ፈላጊዎች ወደተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ሲመጡ ግብር ከፋይ ዜጎች መሆናቸው፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸውና ጥያቄዎቻቸውም በአግባቡ መስተናገድ እንዳለበት ሊታወቅ ሲገባ እንግልት ነው የሚጠብቃቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በብዙዎቹ ተቋማት የሚታየው የአገልግሎት ሰጪነትን ኃላፊነትና ግዴታ ያለማወቅ ችግር ነው፡፡ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ በተለያዩ ሕጎችና እነዚህን ሕጎች ለማስፈጸም በወጡ መመርያዎችና ደንቦች መሠረት የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚገባቸው ዜጎች ጉቦ ይጠየቃሉ፡፡ አንሰጥም የሚሉ ካሉ ደግሞ ጥያቄያቸው መልስ ሳያገኝ ለወራትና ለዓመታት ይንከባለላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር መጋፈጥ የማይችሉ ደግሞ መብታቸውን አሳልፈው በመስጠት የሕገወጥ ድርጊት ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ በአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ምሥጉን አመራሮችና ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ ተገልጋዩን ሲያስደስቱ በኔትወርክ በተደራጁ ኃይሎች ከሥራቸው እንዲወገዱ ይደረጋሉ፡፡
በአንዳንድ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ጉቦ መቀበልም ሆነ መስጠት የማያሸማቅቅ ድርጊት እየሆነ ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት በመስፈኑ ምክንያት በተቋማቱ ግቢና ከግቢ ውጪ ጉዳይ በጉቦ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ያለኃፍረት ይታያሉ፡፡ በሌሎች ቅን ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ላይ ጫና የሚያሳድሩ በርካታ ግድፈቶች ሲፈጸሙ ጠያቂና ተጠያቂ አለመኖሩ ያሳስባል፡፡ 
በፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት ላይ እንደታየው በርካታ ገንዘብ የሚወጣባቸው ዕቃዎች ግዥ የሚፈጸመው በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው የፋይናንስ ሕግ መሠረት አይደለም፡፡ ለበርካታ ግንባታዎች ጨረታ ሳይወጣ የኮንትራክተርና የአማካሪ ድርጅት መረጣ ተካሂዶ በሕዝብ ገንዘብ ይቀለዳል ተብሏል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ እየሆኑ ያሉት ደግሞ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነት የተሰጣቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ በብዙዎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚፈጸመው የበጀት ብክነትና ዘረፋ በተጨማሪ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚታየው ብልሹ አሠራር ያሳፍራል፡፡
በመምህራንና በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቅጥር፣ ምደባ፣ ዕድገት፣ ዝውውርና በመሳሰሉት ጉዳዮች በተለይ በአንዳንዶቹ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታየው ብልሹ አሠራር ከማሳዘን አልፎ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የተሰጣቸውን በጀት ከማዝረክረካቸውና ኦዲት ካለማስደረጋቸው አልፎ፣ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ መሰናክል የሚሆኑ ድርጊቶች እየተፈጸሙ አቤት ሲባል አዳማጭ የለም፡፡ በቡድን የተደራጁ የተወሰኑ ኃይሎች የትምህርት ተቋማቱን ተቆጣጥረው ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ ተቆጪ ከሌለ ምን ማድረግ ይቻላል?
ከትምህርት ተቋማቱ ውጪ ያሉ ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ  የሚታየው ሌላው ችግር ከኃላፊነት መሸሽ ነው፡፡ ትጉሃን ባስገኙት መልካም የሥራ አፈጻጸም ራሳቸውን ጀግና አድርገው እዩኝ እዩኝ ለማለት ማንም የማይቀድማቸው፣ ችግር በሚያጋጥም ጊዜ ደግሞ ለመደበቅ አንደኛ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ አዛዥና ታዛዥ መኖሩ ግራ እስኪያጋባ ድረስ ለሕዝብ አቤቱታ ውሳኔ የሚሰጥ አይኖርም፡፡ በመፈራራትና ከተጠያቂነት ለማዳን በሚል አጉል ሰበብ ራሳቸውን ከኃላፊነት የሚያሸሹ እየበዙ ናቸው፡፡ በራስ የመተማመን መንፈስ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን የሚችሉ ደፋሮች መኖር ሲገባቸው በፍርኃታቸው ምክንያት መወሰን የማይችሉ ተበራክተዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ እንዳለ የማያውቁ የሚመስሉ ኃላፊዎችን በየቦታው ማየት ላያስገርም ይችላል፡፡ ከሥራ ይልቅ በግድ የለሽነት ከቢሮ ቢሮ ሲዞሩ የሚውሉ፣ በስብሰባ ሰበብ ቢሮአቸውን ዘግተው የሚጠፉ፣ በተሰጣቸው የኃላፊነት መጠን ከመወሰን ይልቅ አቤቱታዎችን የሚያከማቹ፣ የአገልግሎት ጠያቂ ዜጎች መብት በሕግ የተከበረ መሆኑን የማይረዱ፣ ወዘተ አሉ፡፡
ለዚህም ሲባል ነው ከበጀት አጠቃቀም ግድፈት በተጨማሪ ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ግድፈት መላ ይፈለግለት የምንለው፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ ሸክም የሚሆኑ ወገኖች ጉዳይ አንድ መላ ሊፈለግለት የግድ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ጠቅላላ ሕዝቡ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ ኃይሎች ምክንያት መንገላታት የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ኃላፊነታቸውን ዘንግተው ሕዝቡን የሚያማርሩ መላ ይፈለግላቸው፡፡ ሕዝብ በፍትሐዊ መንገድ አገልግሎት ማግኘት ስላለበት ተገቢው ዕርምጃ ይወሰድ!  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር